መንትዮቹን አትለያዩዋቸው

0
1031

በኢትዮጵያ በሕዝቦችና በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የተነሱ ግጭቶች በታሪክ ተመዝግበው ይገኛሉ። እነዚህ ግጭቶች የግጦሽ መሬትን ጨምሮ ዛሬ ላይ ቀላል በሚመስሉ እንዲሁም ደግሞ በሌሎች መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት የተነሱ ናቸው። አሁን ላይ እየተስተዋሉ ያሉት ግጭቶች፣ ጦርነት፣ አሰቃቂ ግድያና የእርስ በርስ መጫራረሶች ግን ከወትሮው በተለየ ጥላቻና የበቀል መንፈስ የሚታይባቸው ሆነዋል። ፖለቲካው ይህን አጋጣሚ ለባለሥልጣኖች ወንበር ማደላደያ ያደረገው ይመስላል። በዚህ መካከል ተዉ! ይበቃል! ወደ ሠላም እና ዕርቅ የሚል ቸግሯል። ሰናይ ከሃያ ኹለት ይህን ነጥብ በማንሳት ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

የትግራይና አማራ ሕዝቦች በኃይማኖት፣ በባህል፣ በታሪክና ሥነልቦና አንድ የሆኑና እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ኹሉ ከአንድ ማህፀን እንደወጡ መንትያ ሕዝቦች ናቸው። መንትያ ሆነው የሚወለዱ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ ባህሪ/ጠባይ ይኖራቸዋል። እነዚህ ሕዝቦችም ከሚለያዩዋቸው ጊዜያዊ ችግሮች ይልቅ የሚያቀራርቧቸው በርካታ ዘመናት የተሻገሩ የጋራ ዕሴቶችና ተመሳሳይ መፃዒ ዕድል አላቸው። ፍላጎታቸውም አንድ ዓይነት ነው። ኢትዮጵያ በአንድነት፣ በኅብረት፣ በኃይማኖትና ባህል ተጠብቃ፣ ከድህነት ተላቅቃ በሠላም እንድትኖር የምንጊዜም ምኞታቸው ነው። በወገናቸው ደስታ የሚደሰቱ፣ ያላቸውን ተካፍለው ለዘመናት የኖሩ፣ ዝቅ ብለው የእንግዳ እግርን አጥበው የሚቀበሉና የሚያከብሩ፣ ፍቅርን ያስተማሩ ሕዝቦች ናቸው።

እነዚህ ኹለት ሕዝቦች ኢትዮጵያን ከመሠረቱና ካቆሟት ሕዝቦች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ገፀ በረከት በኅብረት ይጠቀማሉ፤ ተጠቅመዉም ያመሰግናሉ እንጂ ወደ ግጭት የሚወስዳቸው፣ ከወገናቸው የሚያስበልጡት የለም። የራሳቸው ያልሆነ መውሰድን የሚጠየፉ፣ በባህላቸው የሚኮሩ ሕዝቦች ናቸው። ያለ ፍትሕ የተወሰደ መሬት ካለም (መቼም መሬቱ ከኢትዮጵያ ተነቅሎ አይሄድም) በሕግ ይጠይቃሉ፤ በውይይት ይፈታሉ። ደግሞም የኹለቱን ሕዝቦች የቆየ ታሪክና የጋራ ዕሴት በሚያጠፋ መልኩ ለመፍትሔው መሥራት ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም። ከመሬት በላይ ሰው ይበልጣል። መሬት ያለ ሰው ዋጋ የለውም።

የፖለቲካና የሐሳብ ልዩነት ካለም በውይይትና በምክክር ይፈታል እንጂ፣ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጠብመንጃ መፈታት የለበትም። ጦርነት ምርጫ መሆን የለበትም። ይሁን እንጂ በኹለቱም ወገን ያሉ ሊኂቃን ለራሳቸው ጥቅም፣ ለፖለቲካ ሥልጣናቸው ሲሉ ክቡሩን የሰው ሕይወት ለማይተካ መሬት ወይም የፖለቲካ አስተሳሰብ የበላይነት ለማስፈን አሳልፈው ይሠጣሉ፤ ሠጥተዋልም። ለዘመናት ተፋቅሮና ተዋዶ ክፉ ደጉን አብሮ ያሳለፈ፣ በጋብቻና በዕምነት የተዋሃደ ሕዝብን በእልህና ወኔ እንዲነሳሳ በማድረግ ዘላቂ ቅራኔ እንዲፈጠር ሠርተዋል፤ አሁንም እየሠሩ ይገኛሉ።

ያ ሕዝብ ስላለው መልካም ቁርኝት እና ዝምድና እንጂ ስለ መሬትና አጥር አስቦት የማያውቀውን እንዲያስብ በማድረግ ሊኂቃን እንዲመቻቸው ሲባል ወንድም ወንዱሙን እየገደለ ይገኛል። ይህ ትክክልም ተገቢም ባለመሆኑ መቆም አለበት። እስከ አሁንም ውደመት እንጂ ሌላ ትርፍ አልተገኘም።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዱን ከሌላው መነጠል የማይቻል፣ ለዘመናት አብሮ የኖረና የሚኖር፣ በጋብቻም ሆነ በሌሎች ማኅበራዊ መስተጋብሮች የተዋሃደ፣ የጋራ ባህልና ዕምነት ባለቤት ነው። እንደዛው ኹሉ የአማራ እና የትግራይ ሕዝብን ለመለያየት፣ አንዱን ከአንዱ ለመነጠል በማይቻልበት ደረጃ ደርሶ ነበር። ከዚህም ባለፈ ስለአትንኩኝ ባይነት፣ ስለ ክብርና ኩራት፣ ገበናን የዚህ ነው የዚያ ነው ሳይባባሉ በመሸፋፈን ችግሮችን በጋራ ማለፍ የኹለቱም ሕዝቦች መገለጫ ነው። ተስፋን ይዘው መከራን በመተጋጋዝ ያለፉ ሕዝቦች ናቸው። አሁንም ተስፋ ሠንቀው እየተጓዙ የነበሩ ሕዝቦች ቢሆኑም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠረው ችግር ግን ይህን ተስፋቸውን የሚያጨልም ሆኗል።

ኢትዮጵያዊነትም ብዙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተዋሃዱበት ነው። ኢትዮጵያዊነት ከብሔረሰባዊ ማንነት ከፍ ያለ ዕሳቤ ነው። ዜግነት ነው። ዓለም የሚያውቀን በብሔራችን አይደለምና።

በአንድ አገር ሕዝቦች መካከል የሚፈጠር መቃቃር እንዲሁ በቀላል የሚታለፍ አይደለም። ትናንት የነበረው ታሪካችን መጥፎም ይኹን መልካም የጋራችን ነው። እንደውም የእኛ ታሪክ ነው ብለን ወገባችንን ይዘን የምንከራከር ሕዝቦች መሆን ነው ያለብን። ካለፈው ታሪክ መልካሙን ይዘን፣ መጥፎውን እንዳይደገም ለመማሪያ እንዲሆን ብቻ ነው መጠቀም የሚገባው።

ግጭት እንኳን በአንድ አገር ሕዝቦች ይቅርና ከጎረቤት አገር ቢሆንም አስፈላጊ እንዳልሆነ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አስተማሪያችን ነው። የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት አብዛኛው ማኅበረሰብ ባይቀበለውም፣ እንደ አሁኑ በዝምታና በቸልተኝነት በመታለፉ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል። በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት አልፏል፤ ንብረት ወድሟል፤ ሕዝብ ተፈናቅሏል፤ ባልና ሚስት ተለያይተዋል፤ ልጆች ያለ ወላጅ ቀርቷል። ይህ ኹሉ መከራ ካለፈ በኋላ እንዴት አንድ ሕዝቦች የነበርን፣ የተዛመድንና የተዋለድን ደም እስከ መፋሰስ እንደርሳለን? የሚሉ ሐሳቦች በየአቅጣጫው ሲደመጡ ነበር። ምንም እንኳ ሕዝቦችን በሚፈለገውና በሚጠበቀው ደረጃ ማቀራረብ ባይችልም፣ በመጨረሻም በዕርቅ ተፈትቷል።

‹የፈሰሰ ውኃ…› እንደሚባለው ብዙ ጉዳትና የሰው ሕይወት ከጠፋ በኋላ አስፈላጊ አልነበረም ብሎ የሚሟገት ሰው ሳይሆን የጠፋው፣ ጥፋቱ ከመጀመሩ በፊት መደረግ የለበትም በሚል የጸና አቋም ጉዳቱን ማቆም የሚችል ኃይልና አስተሳሰብ አለመኖሩና አለመፈጠሩ ነው። ቢፈጠርም ሠላም ለማምጣት የአንድ ወገን ተሸናፊነትን የሚጠይቅ መሆኑ ግድ ስለሆነ ይህን ማን ያድርገው? ማንስ ይሸነፍ? አንድ አካል እንዳይጎዳ ሲባል አውቆ መሸነፍ የዘመናዊነት ምልክት ነውና አልደረስንበትም። ዛሬም ይህ መጥፎ ታሪክ እርስ በእርስ ባደረግነው ጦርነት ተደግሟል። ይህ በጣም አሳዛኝ ነው። ከትናንት መማር አለመቻላችንን ልናፍርበት ይገባል።

በዓለማችን ይኹን በአገራችን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ለማስቀረት የሚደርግ ቅስቀሳ በጣም አናሳ ሲሆን፣ በኹለት አገራት ይኹን በአገር ውስጥ በሚፈጠር የእርስ በእርስ ጦርነት የተነሳ ክቡር የሰው ሕይወት እንደሚጠፋ እና ሌሎች ውድመቶች እንደሚደርሱ ይታወቃል። ያም ሆኖ በስሜትና በጀብደኝነት የሚገባባት አጋጣሚ በጣም ብዙ ነው። ከዚህ አዙሪት መውጣት አለብን።

በአገራችን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በተፈጠረው የመከፋፈል ፖለቲካ የሕዝቦች ግንኙነት ከማሻከሩ በላይ፣ በተለይ ከአማራና ትግራይ ሕዝብ አብራክ የወጡ ልጆች፣ አብረው ያደጉና አብረው የኖሩ፣ እርስ በእርሳችው እንዲቃቃሩ ተደርገው ወደ እሳት እየገቡ ነው። ‹አንተም ተው! አንቺም ተይ!› የሚል ጠፍቶ አፍላ ወጣት በስሜት ተገፋፍቶ የወገኑን ደም አፍሷል፤ እያፈሰሰም ይገኛል። በዚህ ምክንያት የደረሰው ሰብዓዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውስ ከኢኮኖሚና ሰብዓዊ ኪሳራው በላይ የገዘፈ በመሆኑ ይህንን ማከም የግድ ይላል።

አገራችን ትላልቅ ሰዎች ያፈራች፣ ሕዝቧ አማኝና ፈሪሃ እግዝአብሔር ያለው መሆኑ የሚታወቅ ነው። ይኹን እንጂ በአገራችን ከገበሬ እስከ ምሁር፣ ከምዕመናን እስከ ጳጳስ፣ ከሕዝብ እስከ ባለሥልጣን ፅንፍ ይዘዉና ዋልታ ረገጥ ሆነው ከመመልከት እና ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ፣ በኹለቱም ሕዝቦች ሥር እየሰደደ ስላለው ቂምና ቁርሾ ያስተዋለ የለም። የእሳት ራት እየሆኑ ስላሉ አዳጊዎችና ወጣቶች ትኩረት ነፍገናል።

ከኹለቱ ሕዝቦች የወጡ መሳፍንቶች ሆኑ የፖለቲካ ልኂቃን በጣም ረጅም የሆነ የታሪክ ሒደት ውስጥ አንዴ ሲጋጩ ሌላ ጊዜ ሲተባባሩ፣ ሆኖም ግን ሳይለያዩ ቆይተዋል። ነገር ግን በዚህ መካከል የኹለቱንም ህዝቦች ባህል፣ ታሪክ እና ቁርኝት የሚያውቁ ብዙ ትላልቅ ሰዎችን አፍርተዋል። የእነዚህ ትላልቅ ሰዎች ሚና ዛሬ ምንድን ነው? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። መልሱ ምንም ነው። ለመፍትሔው ግን አሁንም አልረፈደም።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?› በሚል መጽሐፋቸው በአንድ መንፈሳዊ ቤት ከተናገርኩት ብለው ያስቀመጡት ሐሳብ እንዲህ ይላል፤

‹‹በየቀኑ የጭካኔ ወሬ እንሰማለን። ወጣት ለወደፊት መዘጋጀትን ትቶ፣ ለኹለት ተከፍሎ እርስ በእርሱ ለመጫረስ ተነስቷል። ለበለጠ ግድያና መጨራረስ ጩኸት እንሰማለን፤ የእናቶችና የሚስቶችን ጩኸት እንሰማለን፤ የሐዘን ልብሳቸውንም እናያለን፤ የሞትን አደጋ በየአቅጣጫው እናያለን። የፍቅር አለመኖር እንሰማለን፤ እናያለን። የተስፋን አለመኖር እናያለን፤ እንሰማለን። ሐዘን እንሰማለን፤ እናያለን።››

‹‹ከዚህም በላይ ንዴትም፣ ተስፋ ቢስነትም፣ ሐዘኑም ይሰማናል። ሕይወት አጠራጣሪ እና በቀላሉ የሚጠፋ ሆኗል። ከማየትና ከመስማት ውጪ ምንም አናደርግም። ይህ ምንም ያለማድረግ ውሳኔና በሕብረተሰብ ኑሮ ውስጥ ያገባኛል የሚል ስሜት መጥፋት፣ ግልፅ የሆኑ የወላጆች፣ የአስተማሪዎችና የኃይማኖት መሪዎችን የመንፈስ ውድቀት የሚያመለክት ነው። ለግፍ፣ ለበደልና ለጥቃት እንድንገብር፣ ግፍን በደልንና ጥቃትን እየሠማንና እያየን ምንም እንዳናደርግ የሚያደርገን ምንድን ነው?››
አሁንም እየታየ እና እየሆነ ያለው ሁኔታ ይኸው ነው። ገላጋይ ያጣ ፀብ፣ የባሰ እስኪመጣ መጠበቅ፤ ጥግ ሆኖ መፍረድና ዝምታ የበዛበት ጩኸት፤ ይህ ተገቢ አይደለም።

በዓለም ታሪክ ጦርነት መፍትሔ ሆኖ አያውቅም። ጦርነት የአንድ ሕብረተሰብ ሕይወት ወደ አዘቅት የሚጎትት፣ የማይደርቅ ቁስልና ትዝታ ጥሎ የሚያልፍ፣ ቁጭትን የሚያስከትል ነው። ነገር ግን ጦርነትን እንደ ትልቅ ጀግንነት፣ ገዳይነትን እንደ ትልቅ ክብርና የማዕረግ ምንጭ አድርጎ ለሚያስብ አካል፣ ሕዝብን መጠቀሚያ በማድረግ ተረማምዶ ሥልጣን ላይ መቀመጥ እንደ ባህል እየተወሠደ ነው። ይህም ተገቢ አይደለም።

የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ፣ የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት ከመሆኑ አንፃር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖርና የመሥራት መብት አለው። ሕዝብን የሚያገናኝ ድልድይ አንድና አንድ ብቻ ነው፤ የሕዝብ ፍላጎት። እሱም ምርጫው የፖለቲከኞች ሳይሆን በሚመለከተው ሕዝብ ፍላጎት ብቻ የሚወሠን ጉዳይ ነው።

የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መሠረቱ የሕዝቦች ሉዓላዊ ሥልጣን እንጂ፣ የሌላ ኃይል ፍላጎት ሊሆን አይችልም። ከዚህ ውጪ ሊሆን የሚችለው ፖለቲካ ነው። ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ብዙ ዘመናት በፍቅር የተሳሰረ ሕዝብ መጠቀሚያ መሆን የለበትም። ማንኛውም አካባቢ ወደዚህ ቢካለል ወይም ወደዛ ቢካለል ሕዝቡም፣ ተራራውም፣ ሸንተረሩም፣ ወንዙም ተነስቶ አይሄድም።

የአማራ ሆነ የትግራይ አርሶ አደር መሠረታዊ ጥያቄ ምርቱን ማሳደግ፣ ከድህነት መውጣት፣ ልጆቹን ለወግ ለማዕረግ ማድረስና የመሳሰለው ነው። እንጂ ፖለቲከኞች ለግጭት እንደ ምክንያት የሚጠቀሙባቸው አስተሳሰቦችን ለሕዝቡ ቢተዉለት፣ ሕዝቡ ራሱ መፍታት የሚችል ነው። አብሮ የሚኖር ስለሆነ ወንዙን ተራራውን ሆነ ዛፉን ያውቀዋልና።

ምንም እንኳ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በፖለቲካው የሚታዩ ክፍተቶች ማኅበረሰቡ ላይ እየተንፀባረቁ ቢሆንም፣ እነዚህ ኹለቱ ሕዝቦች ግና ከሠላማዊ ግንኙነታቸው በዘለለ፣ አንዳቸው የአንዳቸው ምርት ከመገበያየት በዘለለ፣ በሀዘናቸውም ሆነ በደስታቸው የሚጠያየቁና ባለመልካም ሰብዕና ሕዝቦች ለመሆናቸው ምስክር አያስፈልግም። ኹለቱም ሕዝቦች የጠነከረ ትስስር ያላቸው፣ በፍቅርና በመተጋገዝ የኖሩ ናቸው።

ፖለቲከኞች ለሥልጣን ሽኩቻቸው ከሚያነሱት የመሬት ይገባኛል ሆነ ከፖለቲካ ትርክት በላይ፣ ጥቂት የማይባል ትግራዋይና አማራ በጋብቻ ተሳስሮ የልጅ ልጅ ያየ ነው። በእምነትና ባህል አንድ ነው። አሁን ያለው የተካረረ አስተሳሰብና ደም መቃባት ለእነዚህ ወገኖች ምን ስሜት ይፈጥር ይሆን? ቤተሰብ በመሠረቱና ሠላማዊ ኑሮ እየመሩ ባሉት አካላትስ ምን ዓይነት ስሜት እየፈጠረ ይሆን? ቤተሰብ የአገር መሠረት ነው እያልን መከፋፈልን እየፈጠርን እንደሆነስ?

የኢትዮጵያ አንድነት እንዲረጋገጥ ሥር መሠረት የሆነውን ቤተሰብ እያወቅንም ሆነ ሳይታወቀን እያናጋን ስለሆነ ይህን ተግባር ማስወገድ አለብን። ለዚህ ደግሞ በኹለቱ ኢትዮጵያዊ መንትያ ሕዝቦች አሁን እየተፈጠረ ያለው አደገኛ ሁኔታ መሠረታዊና የማይቀለበስ ችግር ከማምጣቱ በፊት መፍትሔ ለማበጀት መሠራት አለበት። የእስከ አሁኑ ይበቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here