በስምንት ወራት ከጨርቃ ጨርቅ ገበያ ከ121 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ መገኘቱ ተገለጸ

0
1006

ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ21 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል

በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ከጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ገበያ ከ121 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በዚህም፣ ከሐምሌ 1/2013 እስከ የካቲት 30/2014 ባሉት ስምንት ወራት ውስጥ፣ የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ 121 ሚሊዮን 157 ሺሕ 35 ዶላር ማግኘት መቻሉን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ባንቲሁን ገሰሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ21.56 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ተመላክቷል።

በተያዘው በጀት ዓመት ስምንት ወራት ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 136 ሚሊዮን 943 ሺሕ 300 ዶላር ቢሆንም፣ ማግኘት የተቻለው ግን የዕቅዱን 88.5 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል። ይህም በሥራ ሒደት ወቅት በሚያጋጥም የመብራት መቆራረጥ፣ በግብዓት አቅርቦት ችግርና ሌሎች ምክንያቶች የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል ተመላክቷል። በተጨማሪም በዘርፉ የአመራር ብቃት ማነስ፣ የሠራተኛ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን፣ የረዥም ጊዜ የገበያ ልምድ አለመኖር እንደ ችግር የሚጠቀሱ መሆናቸው ተጠቅሷል።

በየካቲት ወር ብቻ 20 ሚሊዮን 139 ሺሕ 94 ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ማሳካታ የተቻለው 15 ሚሊዮን 234 ሺሕ 98 እንደሆነ ነው የጠቀሱት። ይህም የተገኘው ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ26.93 በመቶ ብልጫ መኖሩን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ወደ ውጭ ገቢያ ከሚላኩት ውስጥ ክር፣ ጨርቅ፣ ልብስ፣ ባህላዊ አልባሳት፣ ድር እና ማግ የሚገኙ ሲሆን፣ ወደ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ኬንያ እና ሌሎች የአፍሪካ አገራት በመላክ ገቢው እንደተገኘም ጨምረው ገልጸዋል። እነዚህ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች የሚላኩትም ከሐዋሳ፣ አዳማ፣ ቦሌ ለሚ፣ ኢስተርን፣ ኮምቦልቻ፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ሌሎች ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከሚያመርቱ አካላት ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያ ከአጎዋ (The African Growth and Opportunity Act /AGOA) ገበያ በመታገዷ ምክንያት የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ክፉኛ ሊጎዳ ይችላል የሚል ሥጋት ቢኖርም፣ ዳይሬክተሩ ግን በዚህ የተነሳ ምርት ያቆሙ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች አለመኖራቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም በሚመለከታቸው አካላት በኩል አማራጭ ገበያዎችን የመፈለግ ሒደቶች እንዳሉ ጠቁመዋል።

የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ያለው ድርሻ የላቀ ከመሆኑም በላይ፣ በዜጎች ላይ የሚፈጥረው የኢንዱስትሪ ባህል የጎላ መሆኑ ይጠቀሳል። ዘርፉ በተጨማሪም ብዙ ችግሮች ቢኖሩበትም ያንን ተቋቁሞ በማደግ ላይ ያለ መሆኑ እና በዚህም አገሪቱ በቀጣይ ወደ ከባድ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገለጻል።

በ2014 የምርት ዘመን ኢትዮጵያ ከጨርቃ ጨርቅ ገበያ 223 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንድታገኝ ዕቅድ ተይዟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 176 መጋቢት 10 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here