ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ይዞታ በሌላቸው ግለሰቦች ሥም ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ወስደዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩ ሦስት ተከሳሾች ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ በዛሬው ዕለት ታዘዘ።
ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ግለሰቦቹ በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቦሌ አራብሳ በሚባለው አካባቢ፤ ባለይዞታ ባልሆኑ ግለሰቦች ስም ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ወስደዋል ተብለው በመጠርጠራቸው ነው።
ተጠርጣሪዎቹ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ገረመው ግዛቸውን ጨምሮ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት የካሳ ይዞታ ማረጋገጥና ማጽደቅ ዘርፍ ሰራተኞች የነበሩ 21 ተከሳሾች ናቸው።
በ1ኛ ተከሳሽ አማካኝነት በቦሌ አራብሳ አካባቢ በውሃና ፍሳሽ ተቋም ለሚሰራ ውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት ሥራ ይዞታ ከሌላቸው ግለሰቦች ጋር በዘመድና በጥቅም በመተሳሰር የመሬት ይዞታ እንዳላቸው ተደርጎ ሥም ዝርዝር መግባቱ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም ግለሰቦቹ በይዞታ ባለቤትነት በሀሰት የተመዘገቡ ቤተሰብና የተለያዩ ግለሰቦችን ውክልና በመውሰድ ይዞታ በማረጋገጥ፣ የይዞታ ካሳ በማጽደቅና ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተገባ ካሳ ገንዘብ በመውሰድ ተከሰዋል፡፡
ዐቃቤ ሕግም እንደተሳትፎ ደረጃቸው የካቲት 30 ቀን 2014 የከባድ ሙስና ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረበባቸውን ክስ ለማንበብና ያልቀረቡ ቀሪ 18 ተከሳሾች እንዲቀርቡ የሰጠውን ትዕዛዝ ውጤት ለመጠባበቅ ዛሬ ተሰይሞ ነበር።
ሆኖም የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ሥራ አስፈጻሚ ገረመው ግዛቸውን ጨምሮ 18ቱ ተከሳሾች ችሎት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
ለዛሬ እንዲያቀርባቸው ትዕዛዝ የተሰጠው ፖሊስ መጥሪያው መጋቢት 12 ቀን 4014 የደረሰው መሆኑን ጠቅሶ፤ የጊዜ እጥረት ስላጋጠመው ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁ በችሎቱ ተገልጿል።
ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ ያልቀረቡ 18 ተከሳሾችን ፖሊስ ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አቃቤ ሕግ በበኩሉ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የነበሩት 14ኛ ተከሳሽ በቀለ ገረሱ፣15ኛ ተከሳሽ ጫላ አለሙና 19ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ አለሙ ዋስትና በሚያስከለክል አንቀጽ መከሰሳቸውን በመጠቆም ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ጠይቋል።
በመሆኑም ሦስቱም ተከሳሾችን ከዛሬ ጀምሮ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩና በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያቸውን በጽሑፍ እንዲያስገቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በቀጣይም ፖሊስ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ለመጋቢት 28 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4



