በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሕክምና የሥነ ልቦና ድጋፍ አገልግሎት ሊሰጥ እንደሆነ ተገለጸ

0
502

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነትና በምዕራብ ወለጋ ባለው የፀጥታ ችግር ተፈናቅለው በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ዜጎች እየተሠጠ ያለው የሕክምና አገልግሎት እና የሥነ-ልቦና ዕገዛ ላይ ክፍተቶች መስተዋላቸውን የገብርሔር የጤናና ማኅበራዊ ልማት ማኅበር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ባለፈው አንድ ዓመት ጦርነት በተካሄደበት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሁም የፀጥታ ችግር በተስተዋለባቸው በኦሮሚያ ክልል (ምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ) እንዲሁም በከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ሕፃናት፣ ነፍሰ-ጡርና አጥቢ እናቶች የሚሰጡ የሕክምና እንዲሁም የሥነ ልቦና ዕገዛ ላይ ክፍተቶች መኖራቸው የገብርሔር የጤናና ማኅበራዊ ልማት በጎ አድራጎት ማኅበር የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ትግስት ሽፈራው (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ማኅበሩ ክፍተቶችን ባተስተዋለባቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሀን ከተማ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞን፣ በአፋር ክልል፣እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሚገኙ የተለያዩ የመጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ሰዎች 180 የሚሆኑ ወላጅ አልባና ተጋላጭ የሆኑ አዳጊዎችን፣ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን እና ተቋማትን በማስተባበር የመድኃኒት፣ የሕክምና ቁሳቁሶችን፣ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ማሰራጨቱ ተጠቁሟል።
አስተባባሪዋ አክለውም፣ ማኅበሩ በየወቅቱ በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች ያሉበትን ኹኔታ እና ደኅንነታቸውን የሚገመግም ሲሆን፣ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የሕክምና፣ የሥነልቦና አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው ተፈናቃይ እናቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋዊያን እና ለቁስለኞች አገልግሎት መስጠቱን ይቀጥላል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በጦርነቱ የተጎዱ ጤና ተቋማትን መልሶ ከማቋቋም ባለፈ ያለውን ክፍተት ለመሙላትና የማኅበራዊ እና ሥነ ልቦና ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here