ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 12 ትምህርት ቤቶች ላይ ምርመራ ተጀመረ

Views: 269

የኢትዮጵያ ንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ያለ አግባብ የተማሪዎች የትምህርት ቤት ክፍያ ጨምረዋል በተባሉ 12 ትምህርት ቤቶች ላይ ምርመራ ጀመረ።

ከፍተኛ ችግር አለባቸው ተብለው በተለዩና በአዲስ አበባ በሚገኙ 12 የግል ትምህርት ቤቶች ላይ የወላጆች ኮሚቴ እና የተማሪ ወላጆች ባቀረቡት ቅሬታ መሰረት፣ ጥናት ተደርጎ ምርመራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አልቃድር ኢብራሂም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ አልቃድር ገለጻ፣ ምርመራዉ ሲጠናቀቅ ባለሥልጣኑ ትምህርት ቤቶቹን ወደ ሕግ እንደሚያቀርብና በሕጉ መሰረት እርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዉ አክለውም በአዋጁ መሰረት ትምህርት ቤቶቹ ላይ እንደየ ጥፋታቸዉ ከዓመታዊ ገቢያቸው ከአምስት እስከ ሰባት በመቶ ሊቀጡ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚኖርም ተናግረዋል።

ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙ በአዲስ አበባ የሚገኙ ከአንደኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ መረጃ ያሸሹብኛል በሚልም ሥማቸውን ለአዲስ ማለዳ ከመግለጽ ተቆጥቧል።

ሌላኛው የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዘላለም ላስበው፣ ባለሥልጣኑ ከዚህ በፊት ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር ተገቢ ያልሆነ የተማሪዎች ክፍያ ጭማሪ በማድረግ እና ሌላም ተጨማሪ ወንጀል የተገኘባቸው ትምህርት ቤቶች ምርመራ ተደርጎ በፍርድ ቤት በኩል በሕግ እንዲጠየቁ መተላለፋቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውሰዋል።

የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ከሚተገብራቸው አንዱ በአዋጅ የተቀመጡ መብቶች እንዴት መከበር አለባቸው የሚል ሲሆን፣ በዚህም የሸማቾች መብቶች ተጥሰው ሲገኙ ተግባሩ ወንጀል በመሆኑ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራ ይገኝበታል። ይህ ከኹለት ዓመት ወዲህ ጀምሮ በወንጀል የመጠየቅ ኃላፊነት ከባለሥልጣኑ የሥራ ድርሻ ውስጥ በመነሳቱ፣ በአሁኑ ሰዓት ባለሥልጣኑ አስተዳደራዊ እርምጃን የሚጠይቁ ሥራዎችን ብቻ እንደሚያከናውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጠቁመዋል።

በመሆኑም ባለሥልጣኑ የሸማቾችን መብት ከመጣስ አንጻር ወንጀል ሆነው የሚገኙ ድርጊቶች በፌዴራል ፖሊስ እንደሚመረመሩ እና ክሱን ደግሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንደሚመሰርት ጠቅሰዋል። ባለሥልጣኑም መረጃዎችን አጠናቅሮ የማቅረብ ኃላፊነት ብቻ እንዳለው ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ ጉዳያቸው በምርመራ ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችም የምርምራ ውጤቱ እንደተጠናቀቀ ለሕግ ቀርበው ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለጊዜው ግን የምርመራ ሂድቱ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ባለሙያዎች ትኩረታቸውን ለጊዜው ቫይረሱን ወደ መከላከል ስላደረጉ፣ ለጊዜው መቆሙንም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ባለሥልጣኑ በአዋጅ ከተቋቋመባቸው ዋና ዋና አላማዎች መካከል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማጎልበት የገበያ ግልጽነትን በማሳደግ ጸረ ውድድር የሆኑ የንግድ አሠራሮችንና ተገቢ ያልሆኑና አሳሳች የንግድ ተግባራትን በመከላከልና ፍትሃዊ ውሳኔ በመስጠት የሸማቹንና የንግዱን ማኅበረሰብ መብትና ጥቅም ማረጋገጥ እንደሆነ የሚታወቅ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com