ብሔራዊ ባንክ አዲስ የወርቅ ግብይት ስትራቴጂ እያዘጋጀ ነው

Views: 375

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየዓመቱ እያሽቆለቆለ የመጣውን የወርቅ ገቢ ለማሻሻል እና ሕገወጥ የወርቅ ግብይቱን ለመቆጣጠር አዲስ የወርቅ ግብይት ስትራቴጂ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ።

አዲስ በሚዘጋጀው የወርቅ ንግድ ስትራቴጂ ላይ የወርቅ ግብይት ዋጋ ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግና እንዲሁም ወርቅ በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር የሚወጣበትን ወሳኝ ቦታዎች መቆጣጠር አንዱ የእቅዱ አካል እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በአገሪቱ የማዕድን ሃብት ለማልማት የሚስችል የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በሚዘጋጀው በዚህ የዐስር ዓመት መሪ ዕቅድ ውስጥ ኢትዮጵያ ለምታገኘዉ የወጪ ንግድ ገቢ ዋነኛ በሆነው የወርቅ ምርት ላይ እየታየ ያለውን የምርትና የገቢ መቀነስ ለመቅረፍ ታስቦ አዲስ የወርቅ ግብይት ስትራቴጂ በመዘጋጀት ላይ እንዳለ አስታውቀዋል።

በዝግጅት ላይ ያለው ዕቅድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣውን ሕገ ወጥ ትስስርን የሚቀንስ እንደሆነ ሳሙኤል አስረድተዋል። በሚኒስቴሩ የማዕድን ግኝት ሥራዎች ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክትር በትሩ ኃይሌ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ አዲሱ ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ደግሞ አገሪቱ ከዓመት ወደ ዓመት በተለይም በሕገ ወጥ የወርቅ ዝውውር ምክንያት የምታገኘው ዓመታዊ ገቢ በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የወርቅ ሀብት ባለባቸው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ቦታዎችን በራሳቸዉ ፈቃድ ከልለው ያለዉን የወርቅ ሀባት በሕገ ወጥ መንገድ እየተጠቀሙ እንደሆነ ተጠቅሷል። በሕገ ወጥ መንገድ ያመረቱትንም ወርቅ ለሕጋዊ የወርቅ ግብይት ስርዓት ስለማያቀርቡ በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጣ በማድረጋቸው አገሪቱ ልታገኘው የሚገባትን ገቢ እያሳጣት ነው።

ይህንን ሕገ ወጥነትን ለማስቀረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ማዕድን ሚኒስቴር ዕቅዱን በማዘጋጀት በጋራ እየሠሩ መሆኑን በትሩ ገልጸዋ።
ሌላኛው አዲስ የሚዘጋጀዉ መሪ ዕቅድ የወርቅ ግብይት ዋጋ ላይ ማሻሻያን በሚመለከትም በትሩ ኃይሌ ሐሳባቸውን ሲገልጹ፣ ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው የወርቅ መገበያያ ዋጋ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ወርቅ አምራቾች አርኪ ባለመሆኑ፣ ከባህላዊ ወርቅ አውጭዎች እስከ ትልልቅ ወርቅ አውጭ ድርጅቶች ድረስ ያመረቱትን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አቅርበው አይሸጡም ሲሉ ተናግረዋል።

በወርቅ ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ትልልቅ ድርጅቶች ብሔራዊ ባንክ ከአምራቾች ከሚገዛው ወርቅ ዋጋ ላይ ዐስር በመቶ የሊዝ ተብሎ መቆረጡ ምርታቸውን በሕገ ወጥ መንገድ እንዲያዘዋውሩ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ወርቅ በሚመረትባቸዉ አካባቢዎች ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ቅበላ ቦታ አለመኖሩም፣ ለሕገ ወጥ ዝውውሩ እንደተጨማሪ ምክንያት ይጠቀሳል። ስለሆነም ወርቅ አምራቾች በሚኖሩበት አካባቢ የወርቅ ቅበላ ቦታዎች ይዘጋጃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቅርቡ በመንግሥት ይፋ በሆነው የአገር በቀል የኢኮኖሚ አጀንዳ ላይ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ወርቅን ጨምሮ የማዕድን ዘርፍ ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ታቅዷል።

እየተዘጋጀ ያለው የዐስር ጫመት መሪ እቅድ በዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ዕድል ለመፍጠር ያስችላልም ተብሏል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት ከወጪ ንግድ ለማግኘት ከተያዘው እቅድ አንጻር በውጭ ምንዛሬ ገቢ ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ገቢ ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ውስጥ ወርቅ አንደኛው መሆኑን፣ የ2012 ግማሽ ዓመት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተገልጿል።

ብሔራዊ ባንክ ባወጣው የ2012 ግማሽ ዓመት ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ከወርቅ የውጪ ንግድ ያገኘችው ገቢ 27.9 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ካለፈዉ 2011 ተመሳሳይ ግማሽ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ72.3 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com