የአዲስ አበባን ወንዞች በ29 ቢሊዮን ብር ለማልማት የሚያስችል ፕሮጀክት ተጀመረ

0
727

የአዲስ አበባ ወንዞችንና የወንዝ ዳርቻዎችን በ29 ቢሊዮን ብር እና በሦስት ዓመት ለማልማት ታስቦ የተጀመረው ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፉን “የቤተ መንግሥት አካባቢ የከተማ መናፈሻ” ሥራ በሚል አስተዋውቋል።

በከተማ አስተዳደሩና በፌደራል መንግሥት ትብብር ይካሄዳል የተባለው ይኸው ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፉን ከእንጦጠ እስከ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት አድርጓል። ይህም ኹለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ይፈጃል የተባለ ሲሆን ወጪውም በከተማ አስተዳደሩ እንደሚሸፈን ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ተናግረዋል።

ምክትል ከንቲባው አክለውም ‹‹ለፕሮጀክቱ እውን መሆን ሐሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)›› ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ይሁንና አዲስ አበባ በታኅሣሥ 2008 ለተመሳሳይ ዓላማ በየአምስት ዓመቱ ፕሮጀክቱን እያደሰና እያሰፋ የሚሔድን ‹‹የአዲስ አበባ የወንዞች፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት›› ማቋቋሟ ይታወሳል። በአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሥር የተቋቋመው ፕሮጀክት ፅሕፈት ቤቱ ከወንዞች ባሻገር የወንዝ ዳርቻዎችን እስከ 50 ሜትር በማልማት ለመናፈሻና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ የመሥራት ኃላፊነት ተሰጥቶትም ነበር።

በዚህ መሰረት የተፋሰስ ልማትንና ወንዞችን የማጽዳት ሥራውን የጀመረው ጽሕፈት ቤቱ በወንዝ ዳርቻዎች ላይ የተሰሩ ቤቶች በርካታ መሆን ለልማት የሚነሱትን ምትክ ቤት ለማስጠት አንዱ ፈተና እንደሆነበትም ሲናገር ከርሟል። በዚህም በወንዝ ልማት ምክንያት ሰዎችን ምትክ ቦታና ቤት ሰጥቶ ለማስነሳት ከተማዋ ካለባት የመኖሪያ ቤት እጥረት አንፃር እንዳዳገተው ማሳወቁ ይታወሳል።

በተያያዘ ጽሕፈት ቤቱ በ2009 ጎንደር ላይ በተካሔደው 7ኛው የከተሞች ፎረም የአዲስ አበባን ወንዞችና ዳርቻዎች እንዴት ሊያለማ እንዳቀደ የሚሳይ የተንቀሳቃሽ ምስል ንድፍ (አኒሜሽን) ለታዳሚያኑ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል።

ባሳለፍነው ሐሙስ እንደአዲስ ሊተገበር ይፋ የሆነው የአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች ልማት ፕሮጀክት አዲስ አበባን ለኹለት ከፍለው በሚፈሱ ወንዞች ላይ ሲያተኩር፣ ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ወንዝ ያለውን 56 ኪሎ ሜትር ወንዝ የሚሸፍን መሆኑ ተነግሮለታል።

በሦስት ዓመት ትግበራው አራት ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የተነገረለት ፕሮጀክት ድልድዮች፣ ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ አረንጓዴ ቦታዎች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውሃ ትራንስፖርት እና የንግድ ማዕከላትን እንደሚያካትት እቅድ ተይዞለታል።

ፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ ከተማን የአረንጓዴ ሽፋን አሁን ይገኝበታል ከሚባው ዜሮ ነጥብ ሦስት ወደ ሰባት በመቶ ከፍ ያደርገዋል የሚል ተስፋንም አሰንቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here