“በሸዋ እንደዚህ የሚያምር ልጅ አይቼ አላውቅም” የተባለላቸው

0
1121

ቢትወደድ እንዳልካቸው መኮንን “መልካም ቤተሰቦች” በሚል ርዕስ ጽፈውት ስለግል ሕይወታቸው እና ስለሚያውቋቸው ሰዎች ሕይወት ታሪክ የጻፉበትን መጽሐፍ ያነበቡት ብርሃኑ ሰሙ፥ እነሆ ቅምሻ በአጭሩ ይላሉ።

 

 

ከኹለት ሳምንት በፊት (ሰኞ ጥር 20 ቀን 2011) በብሐራዊ ቴአትር በተሰናዳ የኪነ ጥበብ መድረክ ላይ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድንገት ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት “ሳይጻፍለት ወይም ሳይጽፍ በዓለም ዝነኛና ታዋቂ የሆነ ሰው አታገኙም” የሚል ኃይለ ቃል ሰንዝረው ነበር። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር፣ የኅትመት ውጤቶች ፋይዳ፣ ዘላቂነትና ዋጋ፣ ኃያልነት ከማመልከቱ ባሻገር የጸሐፊያንን አስተዋፅዖ ታላቅነት ጠቋሚም ነበር። በጸሐፊያን አማካኝነት ታሪካቸው ሕያው ሆኖ ከቀረበላቸው ኢትዮጵያዊያን ባለታሪኮች መሐል የቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ቤተሰቦች አንዱ ናቸው።

ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው “መልካም ቤተሰቦች” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ታሪክ፣ በቁም ጽሕፈት ተሰናድቶ፣ በ1949 በአሥመራ ከተማ “ኩሪየረ ኤርትሬዮ ማኅበር” ይባል በነበረ ማተሚያ ቤት የታተመ መጽሐፍ ሲሆን፥ 106 ገጾች አሉት። የመጽሐፉ ትረካ የግለ ሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ዘዴ ቢታይበትም፣ አጨራረሱ ከ“ግሉ” እየራቀ፣ የሌሎችን ታሪክ በመንገር የሚጠናቀቅ ነው። ደራሲው በዚህ መጽሐፋቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን ታሪክ (አብዛኞቹ ቤተሰቦቻቸው ቢሆኑም) ሕያው አድርገውበታል። ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው በንጉሥ ኃይለሥላሴ ዘመን ከመንግሥት ሥራቸው ጎን ለጎን የሥነ ጽሑፍ ተሰጥዖዋቸውን ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ የዘመኑ ባለሥልጣናት አንዱ ነበሩ።

የ53 አንጋፋና ቀደምት የኢትዮጵያ ደራስያንን የሕይወትና የሥራ ታሪክን የያዘውና፣ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ተሰናድቶ በ2000 ለሕዝብ በተሠራጨው አጀንዳ ላይ፥ ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው በሰሜን ሸዋ፣ በተጉለት አውራጃ አዲስጌ መንደር፣ በ1883 መወለዳቸው፣ ከዳግማዊ ምኒልክ እስከ ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በተለያየ የኃላፊነት ቦታዎች አገራቸውን ማገልገላቸው፣ ከ20 በላይ መጻሕፍትን አዘጋጅተው በማሳተም ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት አስተዋፅዖ ማድረጋቸው፣ ከድርሰት ሥራዎቻቸው መሐል “አርሙኝ”፣ “የድሆች ከተማ”፣ “ሐሳብና ሰው”፣ “ሣልሳዊ ዳዊት”፣ “የፍቅር ጮራ”… የተባሉትን መጻሕፍት ማሳተማቸውን አመልክቷል።

በቀድሞ አጠራር በሰሜን ሸዋ፣ ተጉለት አውራጃ ውስጥ የሚገኘው አዲስጌ መንደር መልክዓ ምድሩ፣ የአየር ንብረቱ፣ ተራራው፣ ወንዙ፣ ምንጩ፣ ምን እንደሚመስል በማስተዋወቅ ነው የ“መልካም ቤተሰቦች” ትረካ የሚጀምረው። በዘመኑ ተፈጥሮን፣ አእዋፋትን፣ የቤትና የዱር እንስሳትን ለመጠበቅና ለመንከባከብ በኅብረተሰቡ ውስጥ ይነገሩ የነበሩ ተረኮችና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ምን ይመስሉ እንደነበር ከቀረቡ ምስክርነቶች መሐል፦
“በዚያች መንደር ውስጥ አዳም አባታችን ዕድሜህ እንዲረዝም የሰማይ ወፎችን አትግደሉ ብሎናል በማለት አንድም ልጅ በወፎች ላይ ድንጋይ የሚወረውር የለም። ይልቁንም ኹለቱ እህትማማቶች ለወፎች አሥራት አውጥተው እህል ስለሚበትኑላቸው ከቤተሰቦቹ ጋር ተላምደው ከእልፍኝ ውስጥ ይገቡ ነበር። ከዚህ በተቀር የመንደር ውሻ የወለደች እንደሆነ ቡችሎቹ ዓይናቸውን ከፍተው ራሳቸውን ለመርዳት እስኪችሉ ድረስ የተለመደ ደንበኛ የአራስ ጥሪ ይሰጥ ነበር።”

ለተፈጥሮ፣ ለቤትና ለዱር እንስሳት ይህን መሰል እንክብካቤ ከተደረገ ለሰው ልጅ ምን ያህል ክብር ሊሰጥ እንደሚችል አንባቢ መገመት አያቅተውም የሚሉት ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው “ኹለቱ እህትማማቶች” የሚሏቸው አያታቸውንና የእናታቸውን አክስት ሲሆን “የሕዝብ እናቶች” ብለውም ይጠሯቸዋል። ትልቋ መድፈሪያሽ ድብነህ ሲባሉ ትንሿ ቆንጂት ድብነህ ናቸው። ወይዛዝርቱ በአዲስ አበባ ቤተ መንግሥት በርካታ ልጆችና የልጅ ልጆች ነበሯቸው። ቆንጂት ድብነህ የራስ ተሰማ እናት ሲሆኑ ለመኮንን እንዳልካቸው አያቱ ናቸው።

ኸለቱ “የሕዝብ እናቶች” ከገንዘብ ይልቅ ለሰው ልጅ ክብር ይሰጣሉ፣ የየራሳቸው ቤት፣ ንብረት፣ ገንዘብና ማኅተም… ቢኖራቸውም፥ ሁሉም ነገራቸው የጋራ ነበር። ከአያት ቅድመ አያት በወረሱት ጥናታዊ ቤቶች የሚኖሩት “ኹለቱ እህትማማቾች” ሰከንድ በሌለው ጥንታዊ የግድግዳ ሰዓት እና በአውራ ዶሮም ታግዘው በየዕለቱ ማልደው በመነሳት የጋራ ጸሎት የማድረግ ልምድ ነበራቸው።

ባለታሪኮቹ በመንግሥት ሥራ ላይ (በተለይ አገርን ከጠላት በመከላከል ላይ እያሉ) ብዙ ልጆች ሞተውባቸዋል። በዚህ ምክንያት ጌትነት ሰልችቷው፣ የባለፀግነት ኩራትን አስወገደው፣ ከድሀ ጋር መኖር የሚያስደስታቸው ሆነዋል። እንግዳ መቀበል፣ የቤተሰቡንና ያገልጋይ ልጆች በእኩል ደረጃ በማሳደግ የሚደሰቱ ነበሩ፣ ልጆች በአካባቢያቸው የሚሰጠውን የቄስ ትምህርት ሲያጠናቅቁ አዲስ አበባ ወዳሉ ዘመዶቻቸው (ባለሥልጣናት) ዘንድ ይላካሉ። “የእትማማቶቹ ቤት ድሆች ማስተዳደሪያ ቢሮ ይመስላል” የሚሉት መኮንን እንዳልካቸው በዘመኑ አዲስ አበባ “ቤተመንግሥት ሔዶ መማር ዩኒቨርስቲ እንደመግባት ይቆጠራል”ም ብለዋል።

 

“የእትማማቶቹ ቤት ድሆች ማስተዳደሪያ ቢሮ ይመስላል” የሚሉት መኮንን እንዳልካቸው በዘመኑ አዲስ አበባ “ቤተመንግሥት ሔዶ መማር ዩኒቨርስቲ እንደመግባት ይቆጠራል”ም ብለዋል።

 

ቀዳሚውን የልጅነት ዕድሜዬን በዚህ ዓይነቱ አካባቢ፣ ቤተሰብ፣ ባሕልና ስርዓት ውስጥ ነው ያሳለፍኩት የሚሉት የ“መልካም ቤተሰቦች” መጽሐፍ ደራሲ፣ ከትውልድ መንደራቸው ወደ አዲስ አበባ የመጡት በ1892 ሲሆን፥ ምክንያቱ አጎታቸው ራስ ተሰማ ናደው በ1891 እናታቸውንና አክስታቸውን ለመጠየቅ አዲስጌ በሔዱበት አጋጣሚ “የእህቴን ልጅ ከተማ ልውሰደው ብለው ጠይቀው” ስለተፈቀደላቸው ነበር። ልጅ መኮንን እንዳልካቸው ከአያታቸው (ቆንጅት) ጋር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የመጀመሪያ መዳረሻቸው ደብረ ሊባኖስ ነበር።

መኮንን እንዳልካቸው ከትውልድ መንደራቸው ወጥተው ደብረ ሊባኖስ ሲደርሱ፥ ከልጅነት አዕምሯቸው በላይ የሆነ፣ በቀላሉ ሊረሱት የማይችሉትና ፍርሐት ከሚፈጥር ገጠመኝ ጋር ተገናኙ። “አንድ ቀን ሞግዜቴ ጠበል ለማስጠመቅ ባንዲት ጠባብ ስርጥ መንገድ በደን ውስጥ ይዞኝ ሔደ። ጥቂት እንደተጓዝን አትጋፊኝ ከሚባለው ቦታ አንድ ሰፊ ዋሻ የሰው አፅም የተከማቸበት ደረስን። እኔም አይቼ የማላውቀውን የሰው አፅም በማየቴ ደነገጥሁ። ፈርቼም እንቀጠቀጥ ጀመር። ሞግዚቴም ካንዲት የእንጨት ሳጥን አጠገብ እጅ ነስቶ ቆሞ ፀሎት ያደርግ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሞግዚቴ ‹አትፍራ ይህ ቦታ የብዙ ሰዎች አፅም መከማቻ ነው። ይህም የምታየው ሳጥን የጌታዬ ያባትህ የባላምበራስ እንዳልካቸው አፅም ያለበት ነው› አለኝ።”

ሞግዚቱ ለልጅ ዕድሜና ዕውቀት ይመጥናል አይመጥንም ብሎ ሳይል, ባላምበራስ እንዳልካቸው (ወላይታ) ለዘመቻ ሔደው በጦርነት ላይ እያሉ መሞታቸውን፣ ከጦርነቱም ከባድነት የተነሳ አስከሬናቸውን ማምጣት ስላልተቻለ በወቅቱ በዚያው አካባቢ መቀበራቸውን፣ ከዓመታት ቆይታ በኋላ አፅማቸው ደብረ ሊባኖስ ገዳም መጥቶ እንዲያርፍ መደረጉን ለልጅ መኮንን ተረከለት። ያየሁት ነገር ፍርሐት ፈጥሮብኝ ውስጤ ቀርቶ ነበር የሚሉት “የመልካም ቤተሰቦች” ደራሲ “ቀን ቀን ከልጆች ጋር በማውካትና በመጫወት ቢረሳኝም፥ ሌሊት በሕልሜ አጥንቶቹ ሁሉ ተሰብስበው እየመጡብኝ እባንን ነበር” ብለው ጽፈዋል።

ጥቅምት 12 ቀን 1892 ከደብረ ሊባኖስ ወደ አዲስ አበባ መጡ። በዕለቱ ዐፄ ምኒልክ በአዲስ አበባ አልነበሩም። አዲስ ከተማ ለመመሥረት ወደ ኮረማሽ መሔዳቸውን ስለሰሙ ቆንጂት የልጅ ልጃቸውን ይዘው ወደዚያ ሔዱ። በከተማ ቆይታቸው የተለያዩ ባለሥልጣናት ቤት እና ዐፄ ምኒልክ ዘንድ መቅረብ የቻሉት ልጅ መኮንን ወደ ከተማ ያደረጉት የመጀመሪያ ጉዞ ብዙም አስደሳች አልሆነላቸውም።

በደብረ ሊባኖስ ገዳም አይተው ድንጋጤና ሽብር የፈጠረባቸው የአፅም ምስል ውስጣቸው ቀርቶ ነበር። በአዲስ አበባ እቴጌ ጣይቱ “በሸዋ እንደዚህ የሚያምር ልጅ አይቼ አላውቅም” ብለው ሲያደንቋቸው ቢሰሙም፥ በየቦታው “ሰው እንዳያየው” በሚል ባይነ ርግብ ተሸፍኖ መጋረጃ ውስጥ መቀመጡም አሰልችቷቸው ነበር። በባላገርነታቸው ምክንያት የከተማው ልጆች ሲስቁባቸውና ሲያላግጡባቸው፣ ተድላና ችግሩን ሲያመዛዝኑ ጭንቁ ስለበዛባቸው የልባቸው መሻት ወደ ገጠር በመመለሱ ላይ አመዘነ። አያታቸው ቆንጂትንም “እባክሽ እማማ አገራችን እንሒድ” ብለው አጥብቀው ለመኑ። በእንቅልፍ ልባቸው መባነኑና የመደንገጡ ችግር ስለተባባሰባቸው ወደ ትውልድ መንደራቸው መመለሱ የግድ ሆነ።

የቤተ መንግሥትን ሕግና ስርዓት ለመማር ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የመጡት ከ3 ዓመት በኋላ መስከረም 7 ቀን 1895 ሲሆን፥ በዚህ ወቅት የነበረውን ሁኔታ ሲገልጹ “አያቴ ወይዘሮ ቆንጂትም የአድዋን የሰባተኛው ዓመት የሚከበርበትን ትልቅ በዓልና ሰልፍ ስለአጋጠማቸው ልጃቸው ራስ ተሰማ ሰልፉን እንዲያዩ ስለለመኑዋቸው እስከ የካቲት 23 ቀን ድረስ ቆዩ” ልጅ በመሆኔ ምክንያት የበዓሉ ዕለት ሰልፉን ወጥቼ ባላይም በጣም ደማቅ እንደነበር ሰምቻለሁ የሚሉት መኮንን እንዳልካቸው፣ በዕለቱ አጎታቸው ራስ ተሰማ ናደው ከቤት ሲወጡ ምን ይመስሉ እንደነበር ሲገልጹ፥ “አጎቴ የክብር ልብሳቸውንና የራስ ወርቃቸውን አሥረው ሲወጡ አይ ነበር” ብለዋል።

ዐፄ ምኒልክ ከታመሙ በኋላ አትክልትና የትናንሽ በግ ሥጋ ብቻ እንዲበሉ በሐኪም እንደታዘዘላቸው የሰሙት “የኹለቱ እህትማማቾች” ወንድም ልጅ አንተሌ፣ የግል ጤና ችግር የነበረባቸው ቢሆንም፥ “ሞቴን ከምኒልክ ያስቀድመው” ብለው እየፀለዩ ለንጉሠ ነገሥቱ ምግብ የሚቀርቡ በጎችን ለማራባት ይተጉ እንደነበር፣ ራስ ተሰማ ናደው ሲሞቱ ብዙ ወዳጅ ዘመድ ሳይሰማ ቀብራቸው የተፋጠነው “ጠላቶቹ ደስ አይበላቸው” በሚል ምክንያት መሆኑን፣ የልጅ ኢያሱ ምኒልክ እና የራስ ተፈሪ መኮንን ወዳጆች ፍጥጫና ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክን በማንገስ የተፈታበት ሒደት ምን ይመስል እንደነበር፣ ከእልፈታችን በኋላ ቋሚዎች እርስ በእርስ እንዳይጣሉበት በሚል ዓላማ፣ በኑዛዜያቸው “አሽከሮቻቸውን” ባለድርሻ ስላደረጉ፣ የብድርና የልግስና ማስታወሻ ያኖሩበትን ሰነድ ስላቃጠሉ ቤተሰቦች ታሪክ ያዩትንና ያለፉበትን ምስክርነት በ“መልካም ቤተሰቦች” ያቀረቡት ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ከዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዘመን ተማሪዎች አንዱ ነበሩ።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here