የኦነግ አዛዡ ጃል መሮ ‹ብቻዬን ብቀር እንኳን ትግሌን እቀጥላለሁ› ማለቱ ተሰማ

0
591

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሠራዊት አባላት ትጥቅ በመፍታት ወደ ካምፕ እየገቡ ነው ቢባልም የምዕራብ ኦሮሚያ የኦነግ ጦር አዛዥ ነው የሚባለው ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) ይህን እንደማይቀበል ተናገረ፡፡

ጃል መሮ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው የስልክ ቃለ ምልልስ በመንግሥትና በኦነግ መካከል እርቅና ስምምነት እንዲመጣ እየሠራ ካለው ኮሚቴ ጋር ተገናኝቶ ለመምከር አለመቻሉን በመግለፅ ትጥቅ ፈትቶ ካምፕ ለመግባት እንደማይፈልግ ተናግሯል።

“ወደፊት መራራ ትግል ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ያለው መሮ “ብቻዬን ብቀር እንኳን ትግል ማድረጌን እቀጥላለሁ እቅዴም ይሄው ነው” በማለት ነው ለቢቢሲ የተናገረው፡፡

“ከዚህ የተለየን ጦር 5 በመቶ እንኳ አይሆንም። 95 በመቶ አሁንም እንደታጠቀ ነው የሚገኘው” ብሏል፡፡

የእርቅ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ካምፕ ከገቡት ውስጥ የሆኑት የግንባሩ ጦር የሞራል እና ፖለቲካ መምህር ታፈሰ ኦላና በመሮ በኩል ያሉት ወታደሮች እየተመለሱ እንዳልሆነ አረጋግጠዋል። አክለውም ‘መሮ መመለስ አይፈልግም፤ ስልክ እየደወለ ጸያፍ ቃል እየተናገረን ነው’ ሲሉ ለወሬ ምንጩ ተናግረዋል። መሮ “የኦሮሞን ምድር የጦር አውድማ ማድረግ ነው የሚፈልገው” ሲሉም ከሰዋል።

መሮ እያስፈራራ ነው በሚል ለቀረበበት ወቀሳ “የምን ማስፈራራት ነው። መሳሪያ ይዘን እያየናቸው እኮ ነው እየሄዱ ያሉት። ምርጫቸው ነው። ማንም ማንንም አላስፈራራም” ሲል መልሷል፡፡

የእርቅ ኮሚቴው አባላት የኦነግ የጦር አመራሮችን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት የጦሩ አመራሮች ፍቃደኛ ባለመሆናቸው አለመሳካቱን ተናግረዋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here