ከቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ 300 ዝሆኖች ወደ ኤርትራ መሰደዳቸው ተገለጸ

0
999

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙ ከ300 በላይ ዝሆኖች ወደ ኤርትራ መሰደዳቸውን ፓርኩ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በፓርኩ ውስጥ ሲኖሩ የነበሩ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው እንስሳት እንደተሰደዱና በተለይም ዝሆኖች ለገበያ ጥቅም ሲባል ለሕገ-ወጥ አደን እየተጋለጡ ስለመሆናቸው የቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ ሕግ የማስከበር ቡድን መሪ ሻምበል ባርኮት ደሴ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከ300 በላይ ዝሆኖች በፓርኩ ውስጥ ይገኙ እንደነበር ያስታወሱት ሻምበል ባርኮት፣ ሰሞኑን ግን ወደ ፓርኩ ቢያቀኑም እንዳላገኟቸውና ወደ ኤርትራ መሰደዳቸውን ጠቁመዋል። እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፣ የሚሞቱትና የሚሰደዱት ዝሆኖች ብቻ ሳይሆኑ በፓርኩ ይኖሩ የነበሩ ሌሎች እንስሳትም ጭምር ናቸው። በፓርኩ ከ42 በላይ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ይኖሩ ነበር ያሉት ቡድን መሪው፣ ከእነዚህም መካከል የሆኑት የደጋ አጋዘኖች አሁን ላይ ቁጥራቸው ስለተመናመነ ዘራቸው ወደ መጥፋት ደረጃ ደርሷል ሲሉ ገልጸዋል።

ቁጥራቸው ስለ መቀነሱ ሲገልጹም፣ ከአሁን በፊት በፓርኩ ውስጥ በአንድ አካባቢ እንኳ ከ40 እስከ 50 የሚሆኑ አጋዘኖች ተሰባስበው ያገኙ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ረዥም ርቀት ተጉዘው አንድ አጋዘን ብቻ እንዳገኙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከእነዚህ በተጨማሪም 200 የወፍ፣ ዘጠኝ የተሳቢ እንስሳት፣ እንዲሁም አምስት የአይጥ ዝርያዎች በፓርኩ ውስጥ ይገኙ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ እየተሰደዱ ነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ከፓርኩ ሠራተኞች ያገኘችው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የፓርኩ እንስሳት ከመሰደዳቸውም በላይ እየታደኑ እየተገደሉ መሆናቸውን ነው።

ይህን አስመልክቶም ቡድን መሪው፣ “በፓርኩ ስንዘዋወር የወዳደቁ ቅሪት አካላትን አግኝተናል። የተሽከርካሪ ችግር ስላለብን ወደ ውስጥ ስላልገባን እንጂ በእርግጠኝነት ብዙ ዝሆኖች ሞተዋል። አንድ ዝሆን ሞቶ አግኝተናል” ብለዋል።
ለእንስሳቱ መሰደድም አራት ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳሉ ሻምበል ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ እነዚህ ድርጊቶች መደራራባቸውም ለመተካት የሚያስቸግሩንን እንስሳት ወደማጣት እያደረሰን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ቡድን መሪው ለእንስሳቱ መሰደድና ሞት በመጀመሪያ ደረጃ የጠቀሱት ምክንያት በፓርኩ ውስጥ ያለው መሬት መታረስ ነው። ከፓርኩ ውጭ ብዙ ያልታረሰ መሬት እያለ ከፓርኩ ውሰጥ ያለው ሠፊ መሬት ታርሶ ነው የከረመው የሚሉት ሻምበል፣ ይህም የሆነው አርሶ አደሮቹ አዲስ መሬት ብዙ ምርት ያስገኛል ብለው ስለሚያስቡ ነውም ብለዋል። ጨምረውም በአካባቢው ያሉ ሰዎች ቦታውን እየተከፋፈሉና ደኑን እየመነጠሩት መሆኑን ነው የጠቆሙት።
ይህ ድርጊትም እንሳስቱ እንዲሰደዱ ከማድረጉም ባሻገር፣ ወደ 53 አካባቢ የሚሆኑ የዕፅዋት ዝርያዎች ላይም ጭፍጨፋ እንዲካሄድ ማድረጉን ነው ጨምረው የተናገሩት።

ኹለተኛው ምክንያት ተብሎ የተነሳው በፓርኩ ውስጥ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት መኖሩን ተከትሎ የሚደረገው ቁፋሮ ነው። ፓርኩን የሚቆጣጠረው የጥበቃ አካል ስለሌለ ማንኛቀውም ሰው ወርቅ ለማውጣት እከከ ፓርኩ ውስጥ ገብቶ እስከ አምስት ሜትር ድረስ እንደሚቆፍርና በዚህ ወቅትም እንስሳቱን አድነው ለምግብነት እንደሚያውሏቸው ነው ሻምበል ያመላከቱት።

በጦርነቱ ምክንያት በየመሥሪያ ቤቱ የነበሩ የፓርኩ ሠራተኞች መበተናቸውና ፓርኩ ከተቋቋመበት ከ1999 ጀምሮ የነበሩ ተሸከርካሪዎችና ሌሎች ንብረቶች በሕወሓት ታጣቂዎች መዘረፋቸው፣ የተለመደው የጥበቃ አገልግሎት እንዳይኖር ማድረጉን እና እንስሳቱም እንዲማናመኑ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል፣ በተለይም የዝሆን ጥርስ በከፍተኛ ዋጋ ስለሚሸጥ በፓርኩ ውስጥ የሚካሄደው ሕገ ወጥ አደንም ለእንስሳጹ ሞትና መሰደድ ሌላ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

አዲስ ማለዳ ከዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት የሞከረች ሲሆን፣ መሥሪያ ቤቱ በሕገ ወጥ አደን እና በሌሎች ምክንያቶች የእንስሳቱ ቁጥር እየተመናመነ መሆኑን አምኖ፣ የቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክን በተመለከተ መረጃ ስለሌለው ማጣራት እንደሚያደርግ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

በ1999 የተመሠረተው ፓርኩ በኢትዮጵያና በኤርትራ ድንበር አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ 2174 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አለው።


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here