በአዲስ አበባ ዙሪያ ቡራዩ ከተማ አስተዳደር ሥር በፍሊደሮ (መልካ ገፈርሳ) ቀበሌ የሚኖሩ ከ200 በላይ አባወራዎች፣ ከ13 ዓመት በላይ የኖርንበት ቤታችን ጉቦ በሚቀበሉ ቀበሌ ሠራተኞች ሊፈርስብን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ነዋሪዎቹ አያይዘውም፣ መንግሥት የቆመ ቤት እንዳይፈርስ አዲስም እንዳይሠራ ባለበት ወቅት የቀበሌ ሠራተኞች በራሳቸው ተነሳሽነት ጉቦ እየተቀበሉ ቤታችንን ለባለሀብት እየሸጡት ነው ብለዋል።
ልጆች ወልጄና ቤተሰብ መስርቼ በቦታው ከ14 ዓመት በላይ ኖሬያለሁ ያሉና ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ አባወራ፣ ተፈናቅዬ የት እንደምኖርና ምን እንደሚሻል አላውቅም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የቀበሌ አመራሮች በተደራጀ መልኩ ነው ይህን የሚፈጽሙት ያሉት አባወራው፣ የመንግሥት ትዕዛዝ ቢሆን ኖሮ በስብሰባ ቀናት እና እሁድ ቅዳሜ አይመጡም ነበር ነው ያሉት። ወደ ቡራዩ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሔደን ስናመለክትም፣ እዚያው ቀበሌ ይጨርሱላችሁ ይሉናል፤ በዚህም እርስ በርሳቸው የተያያዙ ናቸው በማለት ተናግረዋል።
ቤታችን ቆሞ በላያችን ላይ ባለሀብቶችን አምጥተው ይደራደሩብናል፤ ያለንም አይመስላቸውም፤ የሚሰማን አካል የለም ወይ ሲሉም ጠይቀዋል።
ሌላኛው ነዋሪ እንዲሁ፣ ምንም አያመጡም በማለት መኖሪያችንን አፍርሰው ሜዳ ላይ ሊበትኑን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ማንም ሰው ቤት ገዝቶ መኖር ሲጀምር 10 ሺሕ ብር ለቀበሌ ከፍሎ የልማትና የጥበቃ ደብተር ይሰጡታል፣ በመቀጠልም ውኃና መብራት ይገባለታል። የጣራና ግድግዳ ግብርም ይከፍላል፤ ልማት ያለማል፤ የመከላከያ፤ የትምህርትና የሕክምና ደረሰኝ ይቆርጣል። በዚህ ኹኔታ ለብዙ ዓመት ኖረናል። ዛሬ ሊያፍርሱብን የሚያስፈራሩን የመንግሥት ትዕዛዝ ሆኖ ሳይሆን በራሳቸው ፈቃድ ነው ብለዋል።
የምትሄዱበት ሒዱ ነው የሚሉን፤ እነሱም በልተው ለመሔድ ነው ይህን የሚያደርጉት ሲሉ ገልጸዋል።
ቅሬታቸውን ያሰሙ ሌላኛው ግለሰብ በበኩላቸው፣ የቀበሌ አመራሮች ባለሀብት አደራጅተው ብር ይቀበሉና እኛን አፈናቅለው ገንዘብ ያለውን እያስገቡ ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ መልኩ ቤታችሁ ለልማት ይፈለጋል ተብሎ የፈረሰባቸው ነዋሪዎች ከጊዜ በኋላ ብር ሰጥተው መልሰው እንደተረከቡም ቅሬታ አቅራቢዎች አመላክተዋል። የቀበሌ አመራሮቹ ከኃላፊነታቸው ሲወርዱ የሕዝብና የመንግሥት ኃብት ዘርፈው መሆኑንም አንስተዋል።
ቤታችን ካርታ ባይኖረውም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉት ቤቶች ከ75 በመቶ በላይ የጨረቃ ቤቶች ናቸው። ዕርምጃ መውሰድ ካለበትም መንግሥት እንጂ የመንግሥትን መዋቅር ሽፋን አድርገው ለራሳቸው ጥቅም ግለሰቦች መሆን እንደሌለባቸው አመላክተዋል።
በቀበሌው ከ6 ሺሕ በላይ አባወራዎች እንደሚኖሩና ቤታችን ሊፈርስ ነው በማለት ቅሬታ ያቀረቡት አብዛኞቹ ከ13 እስከ 20 ዓመት የኖሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የመልካ ገፈርሳ ቀበሌ አስተዳደር ዋና ኃላፊ በላይ ታከለ ከነዋሪዎች የተነሱትን ቅሬታዎች መሠረት በማድረግ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ማብራሪያ፣ ውኃ ወይም መብራት ያላቸው፣ የጣራና ግድግዳ ግብር የሚከፍሉ ነዋሪዎች ቤት አይፈርስም። ይልቁንስ ካርታ እንዲሠራላቸው ነው አቅጣጫ የተቀመጠው ብለዋል።
ምንም ዓይነት ቅሬታ እንዳልደረሳቸው ኃላፊው ገልጸው፣ ምናልባትም ጨለማን ተገን አድርገው መሬት የሚሸጡ ሕገ-ወጥ ደላሎች ይህን ድርጊት ፈጽመውባቸው እንዳይሆን ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም፣ ቀበሌ አስተዳደሩ መሬት ለባለሀብት የመስጠት ሥልጣን እንደሌለው ጠቅሰው፣ ነዋሪዎች ሥጋት ከሆነ ያላቸው በቀጣይ ተወያይተን ለችግሩ ዕልባት ይሰጣል ነው ያሉት።
ኃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ፣ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያቀረቡ ነዋሪዎች ኃላፊው በላይ ታከለ ‹‹እናንተ ካላፈረሳችሁት እኛ የሚያፈርስ ኃይል ይዘን መጥተን ቤታችሁን እናፈርሰዋለን›› ሲሉ በራሳቸው አንደበት ዝተውብናል፤ በዚህ ሕገ-ወጥ ተግባር ራሳቸውም ተዋናይ ናቸው በማለት ይከሷቸዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014


