ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ትምህርት ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በጦርነቱ አካባቢ ለነበሩ መምህራን የሥነ ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ /psychosocial) ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።
ሥልጠናው መምህራኑ ከሥነ ልቦና ጫና ተላቀው ውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራ ለመስራት የሚያስችል ነው ተብሏል።
የትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር የሙያ ፈቃድ ዳይሬክተር ካሳነሽ አለሙ፤ ሥልጠናው መምህራን በጦርነት ከደረሰባቸው የሥነ ልቦና ጫና ተላቀው፣ የመማር ማስተማር ሥራን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።
ዳይሬክተሯ ሠልጣኞች ከሥልጠናው በኋላ በየትምህርት ቤቶቻቸው የተማሪዎችን ሥነ ልቦና ወደ ነበረበት ለመመለስ ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ሠልጣኞች ከስልጠናው በኋላ በየዞናቸው ሄደው የአሰልጣኞች ሥልጠና እንደሚሰጡም ተገልጿል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ መኳንንት አደመ በበኩላቸው፤ ሥልጠናው በጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ መገንባት ብቻ ሳይሆን የደረሰውን ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ለማከም ከፍተኛ አስተዋፆኦ አለው ብለዋል።
ሥልጠናውም በክልሉ በኹለት ማዕከላት በባህርዳር እና ደብረ ብርሃን ከተሞች እንደሚሰጥ የተገለፀ ሲሆን፤ ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ስልጠና ለ3 ሺህ 500 መምህራን መሰጠቱም የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






