“በረመዳን ጾም ምስክር አሰማም ላይ የመከራከር አቅም አይኖረኝም”:- የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ኡመር

0
601

ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ኡመር በረመዳን ጾም ምስክር አሰማም ላይ የመከራከር አቅም አይኖረኝም ሲሉ ቀጠሮ እንዲቀየርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠየቁ።

የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ኡመርን ጨምሮ 17 ተከሳሾች በ2010 በሱማሌ ክልል በጂጂጋ ከተማና በተለያዩ ዞን እና ቀበሌዎች ተከስቶ ከነበረው የዕርስ በዕርስ ግጭት ጋር ተያይዞ ዓቃቢህግ የሽብር ወንጀል ክስ መስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ተከሳሾቹም ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ገልጸው የሰጡትን የእምነት ክህደት ቃል ተከትሎ፤ ከሳሽ ዓቃቢ ህግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ከ50 በላይ ምስክሮች አቅርቦ በኹለት ዙር አሰምቶ ነበር።

ተከሳሾቹ ቀደም ሲል በኹለት ዙር የዓቃቢ ህግ ምስክርን የሰማውና መዝገባቸውን ይመለከት ለነበረው 2ኛ የፀረሽብርና ህገመንግስታዊ ችሎት በየካቲት 14 ቀን በነበራቸው ቀጠሮ ከኛ ጋር ታስረው የነበሩ ሌሎች ግለሰቦች ተፈተው እኛ በመታሰራችን የሥነ ልቦና ጉዳት ስላደረሰብን አሁን ባለንበት ሁኔታ ምስክር የመስማት ፍላጎት የለንም ሲሉ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው ይታወሳል።

አቤቱታቸውን መርምሮ ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀሪ የዓቃቢ ህግ ምስክር ለመስማት ተለዋጭ ቀጥሮ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን፤ በዛሬው ቀጠሮ ግን በመዝገባቸው ላይ የተሰየመው 1ኛ የፀረሽብርና ህገመንግስታዊ ችሎት ነው።

በዚህ ችሎት የቀረቡት ኹለት ዓቃቢ ህጎች ከዚህ በፊት መዝገቡን በሌላ ዓቃቢ ህግ እጅ እንደነበረ ጠቅሰው፤ የትኛው ምስክር በየትኛው ተከሳሽ ላይ ይሰማል የሚለውን የምስክር ቁጥርና በእያንዳንዱ ሥም ጭብጥ ለማዘጋጀት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከሳሽ ዓቃቢ ህጎች ከምስክሮች ደህንነት አንጻር ከመጋረጃ በስተጀርባ የሚሰሙ ምስክሮች ዝርዝር ባይገለጽ የሚል ሀሳብ አንስተዋል።

የተከሳሽ ጠበቆች በኩላቸው ከዚህ በፊት በመዝገቡ 22 ምስክር ከተሰማ በኋላ ከመጋረጃ በስተጀርባ የምስክር አሰማም በተመለከተ በይግባኝ እስከ ሰበር ድረስ ጉዳዩ ታይቶ ትዕዛዝ የተሰጠበት መሆኑን አንስተው፤ በድጋሚ ከመጋረጃ በስተጀርባ በሚሰማ ምስክር ዝርዝር መገለጽ የለበትም ተብሎ በዓቃቢ ህግ የተነሳው ጥያቄ አግባብ እንዳልሆነ ሀሳብ ተሰተውበታል።

ዓቃቢ ህግ ህጎቹ ምስክሮችን ማንነት ለይቶ በቁጥር ለመቅረብ እና ምስክሮችም ከሩቅ ቦታ የሚመጡ መሆናቸው ተከትሎ፤ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በማመላከት የአንድ ወር ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የተከሳሽ ጠበቆችም ከሳሽ ዓቃቢ ህግ ከዚህ በፊት ከ50 በላይ ምስክሮችን ያሰማበት መዝገብን ማን በማን ላይ መሰከረ የሚለውን ለመለየት ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ያቀረበው ምክንያት ተቀባይነት የሌለውና ምክንያታዊ አደለም ሲሉ ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ጠበቆቹ የዓቃቢ ህግ መስሪያ ቤት ክስ ሲመሰርት ምስክር በየትኛው በማን ላይ ይመሰክራል የሚለውን እንደሚያውቅ በመጥቀስ ይህን ሳያውቅ ክስ ይመሰርታል የሚል ዕምነት የለንም ሲሉ በመከራከሪያ ነጥባቸው ጠቅሰዋል።

ዓቃቢ ህግ እጁ ላይ የፖሊስ ምርመራ መዝገብ እንዳለው የጠቀሱት ጠበቆቹ፤ በፖሊስ ምርመራ መዝገብ ላይ በያንዳንዱ ምስክር የተሰጠ ምስክርነት ቃል መኖሩን በማብራራት በዚህ መነሻ የትኛው በየትኛው ይመሰክራል የሚለውን አጭር መግለጫ መስጠት ለዓቃቢ ህግ ቀላል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ነገር ግን ዓቃቢ ህግ በትጋት አለመስራቱንና ትኩረት ሰቶ የያዘው መዝገብ አለመሆኑን ማሳያ ነው ሲሉ የተከሳሽ ጠበቆች ዓቃቢ ህግ ምስክር በቁጥር ለይቼ ለመቅረብ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ያቀረበው ጥያቄን በመቃወም ተከራክረዋል።

“በተለያዩ ጊዜያት ዓቃቢ ህግ በተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ተከሳሾቹን በእስር ላይ ለማቆየት ነው የሚፈልገው” ያሉት ጠበቆቹ የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ ፍርድ ቤቱ ጠበቅ አድርጎ ሊቆጣጣር ይገባል ሲሉ የ1ኛ ተከሳሽ አብዲ መሀመድ ኡመር ጠበቃ ሀሳብ ሰንዝረዋል።

በፍርድ ቤቱ በኩል ግን የተፋጠነ ፍትህ መስጠት ሥራው መሆኑን እና የተቀመጠውም ለተከሳሾች የተፋጠነ ፍትህ የማሰጠት መሆኑን ማብራሪያ ተሰቷል።

የችሎቱ ዳኞች በበኩላቸው ዓቃቢ ህግ ካስቆጠራቸው ከ200 በላይ ምስክሮቹ መካከል ማን በማን ላይ መሰከረ፣ ማንስ ቀረ የሚለውን ለመለየት የሚቸገር ከሆነ መዝገቡን ተመልክተው በማን ላይ መሰከረ ማንስ ቀረ የሚለውን ለይተው ለመስጠት ለመተባበር ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህ መልኩ ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ ዓቃቢ ህግ ምስክር በቁጥር ለይቶ ተዘጋጅቶ ለመቅረብ የአንድ ወር ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ያቀረበው ጥያቄን ውድቅ በማድረግ የቀጠሮ ጊዜ በማሳጠር ለመጋቢት 26 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።

አብዲ መሀመድ ኡመር ከ19 ተከሳሽ ጋር በመሆን ረመዳን ጾም እንደሚገባ በመግለጽ በዚህ በጾም ወቅት ደግሞ ምስክር ሲሰማ ለመከራከር እንደሚቸገር አቅም እንደማይኖረው በመጠቆም ከጾም በኋላ ምስክር እንዲሰማ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው መጠየቁን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።

ቀሪ 15 ተከሳሾች ግን በዚሁ በተያዘው ተለዋጭ ቀጠሮ በጾሙ ምስክር እንዲሰማላቸው እንዲሚፈልጉ የገለፁ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም የምስክር አሰማሙን በተቻለ መጠን እያሳጠረና እያፋጠነ እንደሚመለከትላቸው ምላሽ ሰጥቷል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here