ለነባር እና ለአዳዲስ የኃይማኖት ቴሌቪዥን አመልካቾች ፈቃድ መስጠት ተጀመረ

0
681

ለነባር እና ለአዳዲስ የኃይማኖት ቴሌቪዥን አመልካቾች ከመጋቢት 23/2014 ጀምሮ ፈቃድ መስጠት እንደተጀመረ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ገለጸ።
ባለሥልጣኑ በኃይማኖት ብሮድካስት ረቂቅ መመሪያ ዙሪያ ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በነበሩት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኀን ፖሊሲ እና ሕጎች መሠረት የኃይማኖት ተቋማት የኃይማኖት ብሮድካስት እንዳያቋቁሙ ሕጋዊ ዕውቅና እና ፈቃድ እንዳያገኙ ተከልክለው መቆየታቸው ይታወሳል።
የኃይማኖት ብሮድካስተሮች በሕግ ዕውቅና እንዲያገኙ፣ የመገናኛ ብዙኀን ፖሊሲውም ሆነ የዐዋጅ ማሻሻያ በመደረጉ ባለሥልጣኑ ፈቃድ አውጥተው እንዲንቀሳቀሱ አስፈላጊውን ኹሉ እንደሚያደርግ ተናግሯል።
በሕብረተሰቡ ዘንድ የኃይማኖት መርሃ ግብርን በቴሌቪዥን ለመከታተል ካለው ፍላጎት ጋር በተያያዘ፣ ከመጋቢት 23/2014 ጀምሮ ለነባርም ሆነ ለአዳዲስ የኃይማኖት ቴሌቪዥን ፈቃድ አመልካቾች ፈቃድ መሥጠት መጀመሩ ታውቋል።
ከዚህ ቀደም በተካሄደ ጥናት መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ50 በላይ የኃይማኖት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሥርጭት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ጣቢያዎቹ ኃይማኖታዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ለተከታዮቻቸው አማራጭ የመገናኛ ዘዴ በመሆን እያገለገሉ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል፣ ጥቂት የሚባሉ በኃላፊነት ስሜት እና በጥንቃቄ የማይንቀሳቀሱ የኃይማኖት ሚዲያዎች በመኖራቸው ከሕብረተሰቡ የሚደርሱ ቅሬታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል። ከቀረቡ ቅሬታዎች ውስጥም ከሕግ፣ ከሞራል፣ ከጤና ጋር የሚቃረኑ ንግግሮችን የማሰራጨት እና ሌሎች ኃይማኖቶችን መንቀፍ ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here