የፌደራል ፖሊስ ኢትዮጵያን የሚመስል መዋቅራዊ አደረጃጀትና ሥያሜ አዘጋጅቶ በመካከለኛ ደረጃ ለተመደቡ አመራሮች የመሪነት ሥልጠና መስጠቱን አስታወቀ።
በፌዴራል ፖሊስ በዋና ክፍል የተመደቡት መካከለኛ አመራሮች በተመደቡበት የሥራ መስክ በታማኝነትና በቅንነት ሕዝብን እንዲያገለግሉ ቃለ-መሃላ በመፈፀም፣ አዲሱን ተቋማዊ መዋቅር፣ አደረጃጀትና የትራንስፎርሜሽን መሪ ሚናን በሚገባ ተረድተው የተቋሙን የ10 ዓመት ዕቅድ ለማስፈፀም የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ወስደዋልም ተብሏል።
መኮንኖቹ በኹሉም የተቋሙ አደረጃጀቶች ሥር የዋና ክፍል ኃላፊዎች ሆነው ለኃላፊነት ሲመደቡ፣ በአዲሱ መዋቅር የሰው ኃይል አደረጃጀትን መሠረት አድርጎ የምልመላው መስፈርት የማዕረግ ቀደምትነትን፣ የሥራ ልምድን፣ የትምህርት ደረጃንና ኢትዮጵያን የሚመስል የፖሊስ ተቋም ለመገንባት፣ የሴቶች ተዋጽዖና ኅብረ-ብሔራዊነትን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ ተመላክቷል።
ሠልጣኞች በሥልጠና ቆይታቸው በሪፎርም ምንነት፣ የተቋሙን የ10 ዓመት ዕቅድ፣ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ በንብረት አያያዝ፣ በበጀት አጠቃቀም፣ በማቋቋሚያ ረቂቅ ዐዋጅ፣ በፖሊስ ዶክትሪንና በአመራር ክህሎት ማሳደግ ላይ ግንዛቤ አግኝተዋል ተብሏል።
በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና በቀጣይም እስከ ታችኛው የአመራር እርከን ድረስ እንደሚሰጥ ተመላክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014


