የአውራ ጎዳናው ውዝግብ

0
710

አውራ ጎዳና ሲባል ዋና መንገድ እንደሆነ ነበር አብዛኞቻችን የምናውቀው። ከሠሞኑ ግን አውራ ጎዳና የምትባል አነስተኛ ከተማ መኗሯን እየሠማን እንገኛለን። ይህች ቀበሌ መነጋገሪያ የሆነችው የኢትዮጵያ ኹለቱ ትልልቅ ክልሎች የሚቃረን መረጃን አካባቢዋን በተመለከተ ካወጡ በኋላ ነበር።

መጀመሪያ ስለቦታው የተነገረው በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ማንነታቸው የማይታወቅ ታጣቂዎች ገብተው ጥቃት ማድረሳቸውን የተመለከተ ዘገባ ከወጣ በኋላ ነው። ምን ያህል ጥፋት እንደጠፋ ዝርዝሩ ሳይነገር ትንሽ ዘግይቶ በአካባቢው ታጣቂዎችና ሚሊሻዎች አማካኝንት የተፈጠረ ነው ተብሎ፣ ወሰን ጥሰው የገቡት ላይ ዕርምጃ እንደተወሰደና የተወሰኑት መያዛቸውን የሚያመላክት መረጃ ይፋ ተደርጓል።

ስለጥቃት አድራሾቹ ማንነት ቀስ እያለ በምስል የወጣ ማስረጃ ይፋ መደረግ ሲጀምር፣ ከኦሮሚያ ክልል እንደመጡ የሚያመላከት ዩኒፎርምና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ትተው ሔደዋል በሚል የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት እጅ እንደሚኖርበት ሲነገር ውሎ አደረ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኦሮሚያ ክልል ጉዞ ላይ የነበሩ የፀጥታ ኃይሎቼ ላይ ዕርምጃ ተወስዶብኛል ሲል መግለጫ ያወጣል። ምስራቅ ሸዋ ፈንታሌ ወረዳ ይልና ያች ተሰምታ የማትታወቀውን አውራ ጎዳናን ይጠቅሳል። ይህን ተከትሎ ብዙዎች ግራ እየገባቸው የቦታውን ምስል በአማርኛ ከተፃፈ እንኳን ደህና መጣችሁ ከሚል የመግቢያው መቀበያ ጋር በማድረግ የእምዬን ለአብዬ ብለው ግርምታቸውን ሲገልፁ ነበር።

የአማራ ክልል ባለሥልጣናት በአማራ ክልል ውስጥ ማንነታቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች ጥቃት እንደከፈቱ ሲናገር፣ የኦሮሚያዎቹ ደግሞ በጉዞ ላይ የነበሩ የፀጥታ ኃይሎቹ እንደተገደሉበት የሚያወሳ ተቃራኒ የሆነና አንድ ተመሳሳይ ቦታ ላይ የይገባኛል ጥያቄ የሚያስነሳ የሚመስል መግለጫ አውጥቷል።

የሸንኮራ ወረዳ አስተዳደር ጥቃቱ የተፈፀመው በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ፣ አሞራ ቤት ቀበሌ፣ አውራ ጎዳና ከተማ በተባለ ስፍራ እንደሆነ ሲናገር፣ የኦሮሚያ ክልል ደግሞ ጥቃቱ የተፈፀመው በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ ፈንታሌ ወረዳ፣ ቆርኬ/አውራ ጎዳና በሚባል ቦታ ነው ብሏል እያሉ ብዙዎች ውዝግቡን ተቀባብለውታል።

ልክ እንደቦታው የታጣቂዎቹ ማንነት ላይም የተለያየ ሐሳብ ተቀምጧል። ኦሮሚያ ክልል ጉዞ ላይ የነበሩ የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች እንደሆኑ ከመናገር ውጭ ከየት ወዴት ለምን ተልዕኮ እየሔዱ እንደነበረ ምንም አላለም። ቦታው በተለምዶ ለጥቃት የተጋለጠ እንደሆነ ቢታወቅም እንዲህ ዓይነት እርስ በርሱ የሚጣረስ መረጃ በመንግሥት አካላት መውጣቱ ምን ያስከትል ይሆን በሚል በብዙዎች ላይ ሥጋት አሳድሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here