መነሻ ገጽዜናወቅታዊኧረ የዘይት ያለህ!

ኧረ የዘይት ያለህ!

የኑሮ ውድነት ሲነሳ አሁን ላይ በማኅበረሰቡ አንደበት ቀድሞ ሲነገር የሚሰማው ‹‹ኧረ ዘይት!›› የሚል ማማረር የበዛበት ድምጽ ነው።

የዘይት ጉዳይ ምንም እንኳ የኑሮ ውድነት በተነሳ ቁጥር ከቤት ኪራይ፤ ከትራንስፖርት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተዛምዶ ሕዝቡን እያማረረ ያለ ችግር ከሆነ ቢቆይም፣ ምናልባት ዋጋው ቢጨምር እንጂ አሁን ላይ የተስተዋለውን ያህል ዋጋው ከመናር አልፎ ከመጥፋት ደረጃ አልደረሰም ነበር።

ሠሞኑን ግን ዘይትን በተመለከተ ማኅበረሰቡ እያማረረ ያለው የዋጋ ጭማሪው ላይ ብቻ ሳይሆን ይባስ ብሎም ባለመገኘቱ ነው። በዘርፉ የተጠኑ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከውጭ አገር ማስገባቱም ሆነ በአገር ውስጥ ዘይት ማምረቱ አልተቋረጠም።
ማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት በ2013 ዘይትን በተመለከተ ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመግዛት አቅም ዕድገት ኹለት በመቶ ሲሆን፣ የምግብ ዘይት ፍላጎት ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ ከ74 ሺሕ ቶን በላይ፣ እንዲሁም በዓመት ደግሞ 888 ሺሕ 679 ነው።

ማሌዢያ የፓልም ዘይት ቦርድ ስለ ፓልም ዘይት ዋጋ በ2013 ባወጣው ጥናታዊ መረጃ መሠረት፣ ባለፉው 11 ዓመት ውስጥ ወደ አገር ውስጥ የገባው አጠቃላይ የምግብ ዘይት ቁጥሩ እየጨመረ እንደመጣ ያሳያል።

ለአብነትም በ2003 ከ258 ሺሕ ቶን በላይ፣ በ2004 እስከ 2006 ከ315 ሺሕ እስከ 389 ሺሕ ቶን በላይ፣ ከ2007 እስከ 2009 ከ477 ሺሕ እስከ 519 ሺሕ ቶን በላይ መሆኑን በጥናቱ ማረጋገጥ ተችሏል። ከዚያም በኋላ በ2010 427 ሺሕ 797 ሺሕ ቶን ዘይት ወደ አገር የገባ ሲሆን፣ በ2011 እና በ2012 ደግሞ የገባው የዘይት መጠን ከ742 ሺሕ ወደ አንድ ሚሊዮን፣ ከዚህም አልፎ በ2013 ወደ አንድ ሚሊዮን 217 ሺሕ 903 ነጥብ አራት ከፍ ብሏል።

ይህ ከውጭ የሚገባ የዘይት መጠን ቢሆንም በአገር ደረጃም ቢሆን በአገር ውስጥ የሚገኙ አምራች ፋብሪካዎች ዘይት ማምረታቸውን ቀጥለዋል። ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ ገበያ ላይ የዘይት ዕጥረትና የዋጋ ጭማሪ ዕየታየ የመጣ ሲሆን፣ ከሠሞኑ ደግሞ ምርቱ ከመጥፋት ደረጃ ላይ ደርሷል። የአቅርቦት መጠኑ በየዓመቱ የሚጨምር ከሆነ ምናልባትም የዋጋ ጭማሪ ቢያሳይ እንጂ ታዲያ ጭራሹን የዘይት መጥፋት ምክንያት ከምን የመነጨ ነው? የሚለውን ጥያቄ በርካቶች እየተከራከሩበት ነው።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ “ዘይት ከዕጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ አሳይቶ በዚሁ ከፍተኛ ዋጋ ለመግዛት አቅርቦት አለመኖሩ፣ በአገር ውስጥ ከገባ በኋላ ብዙ አሻጥር ስለሚሠራበት ነው” ባይ ናቸው።

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካካል የአካል ጉዳተኛ የሆኑትና ካለቻቸው አነስተኛ ቁርስ ቤት በሚያገኙት ገቢ አራት የቤተሰብ አባላቸውን እንደሚያስተዳድሩ የገለጹት ጥላሁን በላይ፣ “የዘይት ነገር አማሮኛል። ችግሩ ደግሞ የአቅርቦት ዕጥረት ብቻ ሳይሆን ዘይቱ ስለሚደበቅ፣ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ አሻጥር ስለሚሠራበት ነው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አክለውም፣ “ለዚህም ማኅበረሰቡ እየተቸገረ ከሳምንታት በፊት በመጋዘን ተከማችቶ የተገኘው ዘይት የአሻጥሩን እውነተኛነት በማያሻማ መልኩ የሚገልጽ ነው” ብለዋል።

“ሲፈልጉ ያወጡታል፤ ሲፈልጉ ይደብቁታል” ያሉት የቤተሰብ አስተዳዳሪው፣ ባለፈው ሳምንት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዘይት ለማግኘት በሔዱበት ወቅት ዘይት ቢገኝ እንኳን በክፍፍሉ ወቅት የነበረው አሠራር ፍትሐዊ እንዳልነበር በአካል የተመለከቱትን መስክረዋል።
“እኔ የአካል ጉዳተኛ በመሆኔ ቢሮ ውስጥ ገብቼ ተራ እየጠበኩ ነበር” ያሉት ቅሬታ አቅራቢው፣ ባለሥልጣናቱ እየገቡ እንደፈለጉ ሲወስዱ ዐይቼ “ይህ አሠራር ትክክል አይደለም ብዬ እውነትን በማጋለጤ ወረፋ ጠባቂውን አነሳሳህብን የሚል ወቀሳ ሲነሳብኝ በጣም ነው ያዘንኩት” ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ ኹኔታውን የገለጹት።

በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፣ ለዘይት አቅርቦት ችግር እንደምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል በነጋዴዎች በኩል የሚስተዋለው ዘይት የመደበቅ ተግባር ነው።
የኢትዮጵያ የአንድ ወር የምግብ ዘይት ፍጆታ 86 ሚሊዮን ሊትር እንደሆነ ይነገራል። ታዲያ አስተያየት ሰጭዎቹ የሚሉት ይህ በየወቅቱ የሚደበቀው ዘይት የሚያስፈልገውን ፍጆታ ለማግኘት መሠናክል መሆኑንም ጭምር ነው። በኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች የምግብ ዘይት ተደብቆ እንደሚገኝ ፖሊስን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ሲያጋልጡ ይሠማል።

ለአብነትም ባሳለፍነው የካቲት 28 እና 29/2014 በአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ሲዳሞ ተራ በተደረገ ፍተሻ ከኹለት ሺሕ 600 ካርቶን በላይ የምግብ ዘይት በስምንት ነጋዴዎች አማካኝነት ተደብቆ መገኘቱ የሚታውስ ነው።
በተያያዘም፣ በአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ሸራ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 12 ሺህሕ 944 ሊትር ዘይት ተደብቆ መገኘቱና በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነግሮ ነበር።

በተመሳሳይ፣ በዚሁ በያዝነው ዓመት የካቲት 30 በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 በአንድ ነጋዴ መጋዘን ብቻ ኹለት ሺሕ 380 ሊትር ዘይት በግብረ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገልጿል።

በ2014 ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት የምግብ ዘይት ተደብቆ የተገኘ ሲሆን፣ ድርጊቱ የተፈጸመው በዚህ ዓመት ብቻ ሳይሆን ባለፉት ዓመታትም ጭምር ነው። ለምሳሌም፣ የካቲት 6/2013 በአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ንፋስ ስልክ ጀሞ ሚካኤል አንበሳ ጋራዥ አካባቢ፣ ከኹለት ሚሊዮን ጀሪካን በላይ ፓልም ዘይት በቁጥጥር ሥር ውሏል ተብሎ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ጉዳዩን ሲዘግቡ መቆየታቸው አይዘነጋም።

ነጋዴዎች ዘይትንም ሆነ ሌላ ሸቀጥን ከውጭ ሲያስገቡ በብዛት ነው። ይህንንም በመጋዘን አከማችተው እያወጡ እንደሚያከፋፍሉና እንደሚቸረችሩ ይታወቃል። ታዲያ ይህን የተለመደ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የመጣውን ምርት ብዛትም ሆነ ዓይነት በምስጢር መያዝ የንግዳቸው መሠረታዊ አሠራር መሆኑን ሲናገሩ ይደመጣል። ይህን እንዳያከናውኑ ሠሞኑን እንደተደረገው መጋዘናቸው እየተገባ መቼ እንዳመጡትና እንዴት እየሸጡት እንደሆነ ሳይጣራ ዕቃዎቻቸውን መወረሱ፣ ሕጋዊዎቹ ላይም ሥጋት ስለሚፈጥር ለወደፊቱ ማን አምኖ ዘይት በብዛት አስመጥቶ መጋዘኑ ያስገባል ሲሉ ለዕጥረቱ መንስዔ የመሰላቸውን ምክንያት የሚናገሩም አሉ።

በተቃራኒው እንደ ቅሬታ አቅራቢዎች ገለጻ ከሆነ፣ ተደበቀ የተባለው ዘይት በቁጥጥር ሥር የሚውልበት አጋጣሚ ቢኖርም፣ በመደበቁ ምክንያት ማኅበረሰቡ በሚፈልግበት ወቅት ገበያ ላይ ከመጥፋቱም በተጨማሪ፣ ለዋጋ ንረቱም ምክንያት እንደሆነ ነው። በሌላ በኩል የሚደበቀውና በተለያዩ ጊዜያት በቁጥጥር ሥር የሚውለው የምግብ ዘይትስ ለማኅበረሰቡ ጥቅም እየዋለ ነው ወይ የሚለው ጉዳይ ሌላኛው ጥያቄ ሆኖ ተስተውሏል።

አዲስ ማለዳም ቅሬታውን በማንሳት ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አበባ ታመነ ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ እሳቸው የሚገልጹትም ተደብቆ የሚገኘው ዘይት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እየሆነ መሆኑን ነው።
አከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለተስተዋለው የዋጋ ንረትና የአቅርቦት እጥረት መፍትሄ ለማምጣት እየተሠራ ነው የሚሉት አበባ፣ ከውጭ ዘይት እንዲገባ መታዘዙን እና በቅርቡም ምርቱ ወደ አገር ቤት እንደሚገባ ለአዲስ ማለዳ አሳውቀዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በሌላ በኩል፣ ሠሞኑን ዘይት ጠፍቶ ከቆየ በኋላ በመንግሥት ሥር ባሉ ተቋማት ውስጥ ላሉ ሰዎች እየተከፋፈለ መሆኑ እና ሌላውን የማኅበረሰብ ክፍል ተደራሽ አለማድረጉ በብዙዎች በኩል ቅሬታ ማሳደሩን አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው አስተያየት ሰጪዎች መረዳት ችላለች።
ከአራት ሺሕ ወርሃዊ ደሞዜ ኹለት ሺሕ ብር የቤት ኪራይ ከፍየ፣ ቀሪውን ለሌሎች አስቤዛዎችና ለትራንስፖርት አውጥቼ፣ ከዚህም አልፎ አንድ ሺሕ ብር ዘይት ገዝቼ ሦስት ልጆቼን እንዴት ላስተዳዳር እችላለሁ ሲሉ የጠየቁት ዋጋየ አያሌው የተባሉት እናት ናቸው።

ቅሬታ አቅራቢዋ ሠሞኑን ዘይት እየተከፋፈለ መሆኑን አስታውሰው፣ ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎችስ መካፈል አልነበረባቸውም? በመንግሥት ተቋም ሥር ያሉ አካላት በጥቅማጥቅም ማግኘት ሲችሉ፣ ጭቁኑና አነስተኛ ደሞዝ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ወዴት ይውደቅ ተባለ? ሲሉ ጠይቀዋል።

በ2013 በቡሬ ከተማ የተመረቀው ባለቤትነቱ የበላይነህ ክንዴ የሆነው ፊቤላ የዘይት ፋብሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዘይት ፍላጎት 60 በመቶ እንደሚሸፍን በወቅቱ ሲወሳ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ እንደሚያመለሰክተው፣ የ2014 የዘይት ፍላጎት በወር 75 ሺሕ 543፣ በዓመት ደግሞ 906 ሺሕ 525 ቶን ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚቀርብ የዘይት መጠን ደግሞ በወር 69 ሺሕ 950፣ በዓመት 839 ሺሕ 405 ቶን ነው። በዚህም በዓመት ውስጥ 67 ሺሕ 119 ሊትር ወይም ሰባት ነጥብ አራት በመቶ የአቅርቦትና የፍላጎት ክፍተት እንዳለው መረጃው ያሳያል።

ከመረጃው መረዳት የሚቻለው በ2015 ያለው የፍላጎት መጠን ቢጨምር እንጂ የአቅርቦት መጠኑ እንደማይጨምር ነው። ይህንንም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ቀድሞ ባወጣው ጥናት አመላክቷል። በ2015 የዘይት ፍላጎት በወር ከ77 ሺሕ ቶን በላይ ሲሆን፣ በዓመት ውስጥ ደግሞ 924 ሺሕ 656 ቶን መሆኑን በጥናቱ ተጠቁሟል። በዚህም በአገር ውስጥ የሚቀርብ የዘይት መጠን ከ2014 ጋር ሲነጻጸር ተመሳሳይ ማለትም በወር 69 ሺሕ 950፣ በዓመት 839 ሺሕ 405 ቶን ነው። በ2014 ያለው የአቅርቦትና የፍላጎት መጠን ክፍተት ሰባት ነጥብ አራት በመቶ ሲሆን፣ የ2014 ደግሞ 85 ሺሕ 250 ቶን ወይም ዘጠኝ ነጥብ 22 በመቶ ነው። ይህም የሚያሳየው በ2014 ካለው የምግብ ፍላጎት ይልቅ በ2015 የሚኖረው የምግብ ፍላጎት ቢጨምርም አቅርቦቱ ግን ከ2014ቱ የተለየ እንደማይሆን ነው።

ይህ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለው ክፍተትም በአገር ውጥ ባሉ አነስተኛና መካከለኛ የዘይት አምራቾች፣ ብሎም በነጻ ገበያ ከውጭ በሚገባ ዘይት የሚሸፈን እንደሚሆን በንግድና ኢንዱትሪ ሚኒስቴር የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2014 ያወጣው መረጃ ይጠቁሟል።

ታዲያ ይህ ክፍተት የሚሸፈነው በነጻ ከሚገባና በአገር ውስጥ ከሚገኙ አምራች ፋብሪካዎች ከሆነ፣ ዘይት ለማምረት የሚያስፈልጉ የቅባት እህሎች በአገሪቱ ውስጥ ለማምረት በሚያስችል ደረጃ እየተመረቱ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ ሌላኛው የሚነሳ ጥያቄ ነው።
የምግብ ዘይትን ለማምረት የሚረዱ የቅባት እህሎች በኢትዮጵያ በስፋት መመረት አለመቻላቸው ለተከሰተው ችግር ምክንያት እንደሆነና መፍትሔውም ሙሉ አቅምን ተጠቅሞ የቅባት እህሎችን ማምረት ስለመሆኑ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ይናገራሉ።
የቅባት እህሎችን በተግባር ማምረት ነው እንጂ ይህን ያህል ቶን ዘይት በማስገባትና በማምረት ችግሩ ይቀረፋል ማለት ፐሮፓጋንዳ ነው የሚሉት የኢኮኖሚስት ባለሙያው ዳዊት ካሳ ናቸው።

እንደ ዳዊት ገለጻ ከሆነ፣ ለችግሩ መከሠት ምክንያት የቅባት እህሎችን አለማምረትም ነው። የምግብ፣ መጠጥና ፋርማስዩቲካል ኢንስቲትዩት ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ “ከ2007 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት አጠቃላይ በአገር ውስጥ የእህል ምርት ለማምረት ከለማው መሬት የቅባት እህል ለማልማት የዋለው የእርሻ መሬት የሚሸፍነው በአማካይ 6.61 ከመቶውን ብቻ ነው።”

- ይከተሉን -Social Media

በተያያዘም በዚህ የእርሻ መሬት ላይ የሚመረተው የቅባት እህል በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚመረተው የእህል ምርት በአማካይ 2.71 ከመቶ ብቻ የሚሸፍን መሆኑን መረጃው ጠቁሟል።
በመሆኑም፣ የቅባት እህሎችን የማምረት አቅም ማሳደግ ይበልጥ ችግሩን ለመፍታት እንደሚያስችል ነው ከመረጃውና ከዳዊት ገለጻ መረዳት የተቻለው።

ዳዊት ለተከሰተው የዘይት ችግር የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ሌላኛው ምክንያት መሆኑን አንስተው፣ እንደዚህ ዓይነት ግጭት ሲፈጠር በሰው እጅ ያለን ነገር ማግኘት አቀበት ስለሚሆን በምርት ራስን መቻሉ ተመራጭ መሆኑን አንስተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች