በስምንት ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የሥጋና ወተት ምርት ከ3.9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

0
1161

ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 60 በመቶ አድጓል

በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት ውስጥ ለውጭ ገበያ ከቀረበ የሥጋና ወተት ምርት ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በዚህም ከ16 ሺሕ 65 በላይ ቶን ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ 78 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር (3.9 ቢሊዮን ብር በላይ) ገቢ ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ ገቢው ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቀት ጋር ሲነጻጸር ከ29 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ እንዳለው ነው የተመላከተው።
የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ደበሌ ለማ ይህ የገቢ ልዩነት ሊመጣ የቻለው በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑን ገልጸው፣ በግምት ያስቀመጥናቸው ምክንያቶችም ስላሉ እየተጠኑ ነው ብለዋል።

በዋናነት ግን በድንበሮች አካባቢ ያለው ግጭት የኮንትሮባንድ ንግድን እንደ ከዚህ በፊቱ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎታል ያሉ ሲሆን፣ አብዛኛው የዕርድ እንስሳት የሚመጡት ከቆላማ አካባቢዎች ማለትም ከሱማሌ፣ ቦረናና ባሌ አካባቢዎች መሆኑ እና በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ የተነሳ አርሶ አደሩ ያሉትን እንስሳት ወደ ገበያ ለመሸጥ እንዲያወጣ በመገደዱ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳይኖር ማድረጉን አንስተዋል።

ከፍተኛው ገቢው ከ11 ሺሕ 716 ቶን በላይ የበግና ፍየል ሥጋ በመላክ የተገኘው 66 ነጥብ 78 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የበግና ፍየል ሥጋ ዋነኛ መዳረሻዎች ዱባይና ሳዑዲ አረቢያ መሆናቸው ተመላክቷል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ 95 በመቶ የበግና ፍየል ሥጋ ወደ ኹለቱ አገራት ነው የሚላከው።

በተያዘው ዓመት የካቲት ወር ብቻ 9.25 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል። በሚቀጥለው ወርም ከረመዳን ጾም ጋር ተያይዞ ልዩ ትዕዛዞች ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ደበሌ ለማ፣ ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከመጋቢት እስከ ሚያዚያ ወር መጨረሻ ባለው አንድ ወር ውስጥ ሊገኝ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ሆኖም አርሶ አደሩ ያለውን አብዛኛውን እንስሳት ወደ ገበያ ስላወጣ ቄራዎች በግብዓት አቅርቦት ሊቸገሩ ይችላሉ ሲሉ ሥጋታቸውንም አስቀምጠዋል።

ከ513 ሺሕ ሊትር በላይ ወተት በመላክም 150 ሺሕ ዶላር ገደማ የተገኘ ሲሆን፣ አንድ ጊዜ 168 ቶን የአህያ ሥጋ በመላክ 190 ሺሕ ዶላር ቢገኝም፣ የቄራ ድርጅቱ ባለበት የውስጥ የፋይናንስ ችግር ምክንያት መላክ አቁሞ እንደነበርና አሁን ግን ለመላክ እየተዘጋጀ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ ጨምረው የገለጹት።

ማር እንዲሁ በዋናነት ወደ አውሮፓና አሜሪካ በመላክ 220 ሺሕ ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ በባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 30 ሺሕ ዶላር ሲነጻጸር፣ 190 ሺሕ ዶላር የሚደርስ ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ነው የተገለጸው።
በ2014 ስምንት ወራት በአጠቃላይ 78 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የበግና ፍየል ሥጋ፣ የአህያ ሥጋ፣ ወተት፣ የዳልጋ ከብት ሥጋ፣ የዕርድ ተረፈ ምርት፣ ሰም፣ የዓሳ እና ዶሮ ምርት በመላክ የተገኘ መሆኑ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here