የውጭ ግብዓት አቅርቦት ውሎች እየተሠረዙ ነው
የኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት ለኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ከውጭ የሚገቡ የምርት ግብዓቶችን በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት የተነሳ ማቅረብ አልቻልኩም ሲል ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ድርጅቱ ለተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ግብዓቶችን ሲያቀርብ እንደቆየ ገልጾ፣ አሁን ላይ ግን በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት የተነሳ በርካታ ግብዓቶችን ማቅረብ ካቆምኩኝ ሦስት ዓመት ሊሆነኝ ነው ብሏል።
በተለይም ለጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተዳመጠ ጥጥ፣ ብትን ጨርቅና የስፌት ክሮችን የሚያቀርብ መሆኑን የገለጸው ድርጅቱ፣ አሁን ላይ የጥጥ ዕጥረት ቢኖርም ምንዛሬ ባለመኖሩ ማቅረብ እንዳልተቻለ አስታውቋል።
እንዲሁም ሌሎች አገር ውስጥ የሌሉ እና ከውጭ መግባት ያለባቸው በርካታ ግብዓቶች እንዲገቡ ቢፈለግም፣ ነገር ግን የምዛሬ ዕጥረት የተነሳ ችግሩን በቀላሉ መቅረፍ እንዳልተቻለ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ግዥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደሻው ለገሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ለብረታ ብረት፣ ቆርኪና ጣሳ የሚሆኑ ግብዓቶች ይፈለጋሉ። የግብርና ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችም የምግብ ማበልጸጊያ ንጥረ ነገሮችን ይፈልጋሉ ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም፣ የቆዳ ፋብሪካዎችም የኢንዱስትሪ ኬሚካሎችን የሚፈልጉ ሲሆን፣ ጫማና ቦርሳ የሚሰፉ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን (Accessories) ይፈልጋሉ ነው ያሉት።
ዳይሬክተሩ በግብዓት ዕጦት የተነሳ ሥራ እስከማቆም የደረሱ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በተደጋጋሚ ውል ቢገባም የምንዛሪ ዕጥረቱ ስለማይቀረፍ ውሉ ይሰረዛል ብለዋል። በዚህም ድርጅታችንን ጥቁር መዝገብ (Blacklist) ውስጥ አስገብተዉታል፤ አገራችንንም እነሱ አይከፍሉም በማለት ባንኮቻችንን ኹሉ ለማመን ይቸገራሉ ሲሉ አስረድተዋል።
ለአብነትም ለአልሚ ምግብ ግብዓቶች ውል ገብተን በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት የተነሳ ውሉ ተሠርዟል የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ የተነሳ አገልግሎታችን በዕቅዳችን መሠረት እየሄደ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ማንኛውም አምራች ኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ይፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሆኖም ፋብሪካዎች ግብዓት ፈልገው እኛ ጋር ቢመጡ ግብዓቱ እስካልመጣ ድረስ አናግዛቸውም ሲሉ አስገንዝበዋል። እጃችን ላይ የብዙ ፋብሪካዎች በርካታ ጥያቄዎች አሉ፤ እኛም ምንዛሪ እያገኘን ስላልሆነ የምንረዳቸው ነገር አይኖርም በማለት ገልጸዋል።
ድርጅቱ እንደ ቡናና ሰሊጥ ያሉ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በመላክ በሚገኘው ምንዛሪ ግብዓት ለማስገባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹በርትተን ለውጭ ገበያ በመላክ የሚገኝ ምንዛሬ ካለ፣ በመንግሥት ፖሊሲ መሠረት ቅድሚያ የሚሠጣቸውን እየለየን የምንደግፋቸው ይሆናል።›› ሲሉ ጠቁመዋል።
ኹሉም ፋብሪካ የግብዓት ዕጥረት አለበት የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ችግሩን ለመፍታትም መፍትሔው የጋራ ነው፤ ይህም የአገሪቱን የውጭ ንግድ አቅም ማሳደግ ነው ሲሉ አመላክተዋል።
የውጭ ምንዛሬ እንዴት ነው የሚገኘው የሚለው ላይ መሥራት እንደሚገባ አንስተውም፣ ለውጭ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት እና ኹሉንም ምርቶች ከውጭ ከማስገባት በአገር ውስጥ ለመተካት መሥራት አስገፈላጊ ነው። በዚህም ሊተኩ በማይችሉት ምርቶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መሥራት ከተቻለ ችግሩ ይቀረፋል ሲሉ አስረድተዋል።
በብዙ ኢንዱስትሪዎች የተከሠተው የጨው ዕጥረት በነዳጅ ዋጋ መጨመር የተነሳ በትራንስፖርት ዕጥረትና አፋር ክልል ባለው የጸጥታ ኹኔታ የተፈጠረ መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ላይ ከጨው አምራቾች ማኅበር፣ እንዲሁም ከአፋር ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን ዕጥረቱን ለመቅረፍ እየሠራን ነው ብለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 178 መጋቢት 24 2014


