ሐሙስ መጋቢት 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነውን የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች ፍላጎቷን በአገር ውስጥ አምራቾች እንደምትሸፍን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
“ንግድዎን በመቅረዝ ላይ ያኑሩ” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው የፊንቴክስ 3ኛ ዙር የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች አገልግሎቶች እና ቴክኖሎጂዎች ዓለም ዓቀፍ አውደ ርዕይና ኮንፍረንስ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል በይፋ ተከፍቷል፡፡
በአውደ ርዕይና ኮንፍረንሱ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በአሁኑ ወቅት 70 በመቶ የሚሆነው የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች በአገር ውስጥ አምራቾች የሚመረቱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ቢሆንም ግን አሁንም አገሪቷ 30 በመቶ የሚሆነውን ምርት እና ጥሬ እቃዎች ከተለያዩ አገራት እንደምታስገባና፤ በዚህም በዓመት ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆነ ወጪን እንደመወታወጣ የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ባለፉት 5 ዓመታትም 78 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶችን ከውጪ አገራት ማስገባቷን ተናግረዋል።
እነዚህንም ከውጭ የሚገቡ የፈርኒቸር ምርቶች በማስቀረትና በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት መንግስት የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ እቅድ እንዳለውም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች ዘርፍ በአገራችን ሰፊ የማደግ እድል ያለው ዘርፍ ነው ያሉት መላኩ፤ ነገር ግን የሰው ሃይል ሥልጠና ማነስ፣ የግብዓት አቅርቦት ችግሮች፣ የኬሚካል እና የመለዋወጫ እጥረት፣ የገበያ ትስስር ችግር እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች አለመደረግ በዘርፉ ላይ እንደተግዳሮት የሚጠቀሱ ጉዳዮች መሆናቸው ተናግረዋል።
እነዚህንም ተግዳሮቶች ለመፍታት መንግስት የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ እቅድ እናዳለው የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በተጨማሪም የአገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት ኤክስፖርትን መቀነስ እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራን መርሃ ግብር በማሳደግ ለዘርፉ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ፕራና ኤቨንትስ እና አፍሪካን ትሬድ ፖርትነርንስ በጋራ በመሆን ባዘጋጁትና በዛሬው ዕለት በተከፈተው የፊንቴክስ 3ኛ ዙር የፈርኒቸር፣ የቤተ ውበትና የግንባታ አጨራረስ ምርቶች ዓለም ዓቀፍ አውደ ርዕይና ኮንፍረንስ ላይም ከ40 በላይ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ፣ ከኬኒያ፣ ከፖላንድ፣ ከጣሊያን፣ ከቱርክ፣ ከጀርመን እና ከቻይና የሚሳተፉ ሲሆን፣ ከ400 በላይ ገዥዎችና ከ4 ሺህ በላይ የንግድ ማኅበረሰብ አባላትና ጎብኚዎች እንደሚስተናገዱበት ይጠበቃል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






