ከሳዑዲ ዓረቢያ በስደት ላይ የነበሩትን ወደ አገር ውስጥ መልሶ ለማቋቋም ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከስደት ተመላሽ ወገኖችን ወደ ሥራ ለማሠማራት ኹሉም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያበርክት ጥሪ አቅርቧል።
የስደት ተመላሾች መልሶ የማቋቋም ኮሚቴ፣ በተለያዩ የአረብ አገራት ከ750 ሺሕ በላይ ዜጎች እንደሚኖሩ የጠቆመ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ወደ 450ሺሕ የሚጠጉት በሕገ ወጥ መንገድ የሔዱ መሆናቸውን አመላክቷል። አሁን ላይ ወደ 102 ሺሕ የሚጠጉትን ከ7 እስከ 12 ወር ውስጥ ለመመለስ እንደታቀደ ጠቁሟል።
ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልግውን ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ብር ለማሟላት መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል።
ከዚህ አኳያ ከፋይናንስ ተቋማት በተለይም ባንኮች ምቹ ኹኔታዎችን ለመፍጠር ታሳቢ መደረጋቸው ጠቃሚ መሆኑን ያነሱት ተወያዮቹ፣ የፋይናንስ እና የብድር ኹኔታዎችን መመቻቸት እንዳለባቸው ነው የተገለጸው።
ከስደት ተመላሾችን እና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን መልሶ ከማቋቋም አንጻር ባንኮች እና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ ሚና አላቸውም ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014


