የእለት ዜና

ስለ ቤት ውስጥ ሰላም!

Views: 396

የኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁንም አንድ አንድ ያለ የተጠቂዎቹን ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። ሁኔታውን ሳይከፋ መቆጣጠር ካልተቻለ ነገሮች ምን ያህል አስፈሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ ከወዲሁ አስጨናቂ ሆኗል። አውሮፓ እና አሜሪካ ቫይረሱን እያስተናገዱ ባሉበት መጠን ኢትዮጵያ ውስጥ ማስተናገድ የሚታሰብ አይሆንም።

ይህ ጭንቀትና ስጋታችን ወደ ጥንቃቄ የሚያመራ ከሆነ ግን ከወዲሁ መቆጣጠርና መቋቋም ይቻል ይሆናል። ይህም ጥንቃቄ ከመደጋገፍና መ,ከመረዳዳት እንዲሁም ከጸሎት ጋር ተዳምሮ፣ የምንናፍቀውን ሰላማዊ ጊዜ እንደሚያቀርብልም በተስፋ የምንጠብቀው ነው።

ታድያ የወረርሽኙን ስርጭት ለመቆጣጠር መንግሥት ጥቂት የማይባሉ እርምጃዎችን ወስዷል። ለተለያዩ ውሳኔዎቹ ማሠሪያ የሚሆነ የሚመስል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ታውጇል። ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ የተሰጠ ዝርዝር መመሪያ ባይኖረውም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለኢትዮጵያውያን ‹አዉ መጣልህ!› ዓይነት ለሕጻናት እንደሚቀርብ ማስፈራሪያ የሚቆጠር ነው።

ገና ሥሙ ሲጠራ የተኩስ ድምጽ፣ የብዙ ሰዎች መታሰር፣ የፍትህ መጓደል፣ ያለመናገር ያለማውራት ወዘተ የሚታየው ሰው ጥቂት አይደለም። ከወዲሁም የፈተና ውጤትን ለመስማት እንደጓጓ ተማሪ፣ ‹‹ዝርዝሩ ምንድን ነው?›› እያለ በተደጋጋሚና፣ ‹ዝርዝሩ ለምን ዘገየ?› እያለ በቁጣ የሚጠይቀው ጥቂት አይደለም።
ጥሩ! ይህ ጽሑፍ በወጣበት ጊዜ ምንአልባት የመመሪያው ተፈጻሚነት ላይ ይሆናል ክርክሩ። ብቻ በዛም አለ በዚህ ለወራት የሚቆይ የተባለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት ጊዜ ግን የሴቶች ጉዳይ እንዳይዘነጋ አደራ ማለት ያስፈልጋል። በተለይም በአዋጁ ከማይነኩ መብቶች ውስጥ የሴቶች መብት የለበትምና፣ እንደው በዚህ ላይ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ቢያንስ መብታቸው እንዳይጣስ አደራ ማለት ግድ ይላል።

በተለያዩ አገራት እየሰማን እንዳለነው የቤት ውስጥ ጥቃት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ዓለም ስትረጋጋ በርካታ በፍቺ የሚፈርሱ ትዳሮች እንደሚኖሩም የሚጠበቅ ነው። ልጆችም ይበተናሉ። ከዛም በላይ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት እየተሰማ እንዳለው በፖሊሶች ሳይቀር በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተሰምተዋል። እንግዲህ ቤቱ በእሳት ሲቃጠልና ሰው ለማጥፋት ሲሯሯጥ፣ ከቤት ውስጥ እቃ ለመስረቅ የሚሞክር አይጠፋምና ነው።

ይህንን መንግሥት እንዲሁም በሴቶች ጉዳይ ዙሪያ ዝም የማይሉ ተቋማት ሊከታተሉት የሚገባ ጉዳይ ነው። ከዚህም አንደኛው የስልክ ጥሪን ማስተካከል ነው ባይ ነኝ። ስለሴቶች ጉዳይ ከሚጨነቁ ማኅበራት መካከል ሴታዊት ‹አለኝታ› የተሰኘ ሴቶች ጥቃትና ጉዳታቸውን የሚያሳውቁበት የስልክ መስመር ይፋ አድርጋ ነበር። ነገር ግን በወቅታዊ ሁኔታዎች ምክንያት አገልግሎቱ ላልተወሰነ ጊዜ እንደማይኖር ማኅበሯ አስታውቃለች።

እንዲህ ያሉ አማራጭ መንገዶች ግን በመንግሥት በተለይም በሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴርና ቢሮዎች በኩል ሊሠራት ይችላል/ይገባልም። በአሁኑ ሰዓት የሕክምና ባለሞያዎች ሰዎችን ለማዳን እንደሚሯሯጡት፣ ለቤት ውስጥ ሰላምና ለሴቶች ደኅንነት ደግሞ ፖሊሶችን መመደብ ያስፈልጋል።

እርግጥ ነው ይህ በአንድ ማኅበር አቅም ብቻ የሚሆን አይሆንም፣ የፖሊስና የፍትህ ኣካላትን ትብብር ያስፈልጋል። እርግጥም በሰላሙ ዘመን ጥቃቶች ደርሰው ክስ መመሥረትና ጥቃት ፈጻሚን በሕግ ፊት ማቅረብ ለፍትህ ስርዓቱ ከነውር የተቆጠረ ይመስላል፤ ብዙ ሲደረግም አይስተዋልም።

እንዲህ ባለ ሰዓትም ከዛ የተለየና የተሻለ ነገር ባይጠበቅም፣ ጥቃቱ ግን ከቀደመው ይልቅ ሊበረታ ስለሚችል የመፍትሔ ሐሳብ ማፈላለግ ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
ሊድያ ተስፋዬ

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com