አዲሱ የጎንደር ዩኒቨርስቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል፣ ከመደበኛ ዲፕሎማሲ ባለፈ፣ በማኅበረሰባዊ ዲፕሎማሲ አገርን ማስተዋወቅ፣ እንዲሁም መብትና ጥቅሞቿን ማስጠበቅ የሚችል አስተዋጽዖ ማበርከትን በማለም የተተቋቋመ መሆኑ ተመላክቷል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ሐቅ ለዓለም ለማስገንዘብ መደበኛው ዲፕሎማሲ በቂ ባለመሆኑ፣ በጥቂቶች ተጀምሮ ብዙኃን የተቀላቀሉት ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ዕውነት ሳይወድ እንዲቀበለው እንዳስገደደ አብራርተዋል ተብሏል።
በዚህም፣ ኢትዮጵያ ከዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ፍረጃ ፋታ እንድታገኝ ከማስቻሉም ባለፈ አያሌ ጥቅሞች መገኘታቸውን ተዘግቧል።
ይህን ለማጠናከር የጎንደር ዩኒቨርስቲ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ለብሔራዊ ጥቅም የሚሟገቱ፣ በእውቀት የታነጹ እንዲሁም ለሠላም እና አብሮነት የሚተጉ ተማሪዎችና መምህራንን ማብቃትን በማለም ማዕከሉን መመስረት እንዳስፈለገው ነው የተጠቆመው።
ኢትዮጵያ ሁሌም ፈተናዎችን የምትሻገረው ያገባኛል ብለው የድርሻቸውን በሚወጡ ትጉህ ዜጎቿ ነው ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዳንኤል ክብረት (ዲ/ን)፣ ‘‘የኢትዮጵያን ጉዳይ የኹላችንም ነው። ዲፕሎማሲው መደበኛ ባልሆነ የሕዝብ ዲፕሎማሲ መታገዙ ለአገር ወደ ፊት መራመድ የላቀ ሚና አለው” ማለታቸውም ተነግሯል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምበሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፤ “የትምህርት ተቋማት የዲፕሎማሲ ሥራን በተቋም ደረጃ መያዛቸው የሚበረታታ ነው። ማኅበረሰቡን በማቀናጀት ለአገር ገጽታ እና ልዕልና ልንሠራ ይገባል” ማለታቸውም ተዘግቧል።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014


