ፍትሕ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የጥብቅና ድርጅት ፈቃድ ሰጠ

0
393

የፍትሕ ሚኒስቴር የመጀመሪያውን የጥብቅና ድርጅት ፈቃድ በዚህ ሳምንት ለ‹ሐበሻ ሌጋል አድቮኬትስ ኤልፒ› መስጠቱ ተገልጿል።
ፈቃዱ የተሰጠው በፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር ዐዋጅ ቁጥር 1249/2013 መሠረት መሆኑም ነው የተጠቆመው።
ፍትሕ ሚኒስቴር ከአዲሱ የኢትዮጵያ የፌዴራል ጠበቆች ማኅበር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዐዋጁን በተሟላ ኹኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ዝርዝር የአሠራር መመሪያዎችና ውስጠ ደንብ መቅረጽን ጨምሮ፣ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና መነሻ የሚሆን የሰው ኃይል እና ግብዓት በመመደብ ወደ ሥራ መግቧቱን አውስቷል።
በአዲሱ የጠበቆች ዐዋጅ አንቀጽ 37 መሠረትም፣ የፀና የጥብቅና ፈቃድ ያላቸው ቢያንስ ኹለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ጠበቆች አንድ ላይ በመሆን የጥብቅና ድርጅት ማቋቋም እንደሚችሉ በመደንገጉ በዐዋጁ መሠረት የመጀመሪያ የሆነው የጥብቅና ፈቃድ መሥጠቱን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥብቅና አገልግሎት በድርጅት መስጠት የሚያስችል ሕግ መውጣቱና ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ፣ ለዜጎች የተሻለና ጥራት ያለው የሕግ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውና በደንበኞችና ጠበቆች መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን የሚያጎለብት ከመሆኑም ባሻገር፣ የተሻለ ዋስትና የሚሠጥ ነው ተብሏል።
ፍትሕ ሚኒስቴር የዐዋጁን ዝርዝር ተመልክተው መስፈርቱን የሚያሟሉ ከሆነ ለሌሎች አመልካቾችም የጥብቅና ፈቃድ እንደሚሰጥ አመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here