ተመሳሳይ መንገድ አንሂድ!

0
968

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ዛሬ በአንድ መድረክ አንዲት እህቴ ያቀረበችው ጽሑፍ ነው መነሻዬ። እዛና እዚህ ብዬ አልጠቁምም፤ ግን በንግግሯ ‹ፌሚኒዝም› ለምን እንደሚጠላ ዕይታዎቿን ጠቅሳ፤ ወንዶችን ወቅሳለች፣ በብዙ መልኩ ተቃውማለች። ‹ፈጣሪ የለም› የሚሉ ወንዶችን ፈላስፋ ብለው፣ ሴቶች ግን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በሴቶች ‹ቨርዥን› ለምን አይጻፍም ስንል ይቃወሙናል የሚል ሐሳብ አነሳች። ነገሩ ወደ ሲቄ እንድመጣ ግድ አለኝ። ለምንድን ነው ተመሳሳይ መንገድ ለመሄድ የምንመርጠው ብዬ መጠየቅም ፈለግኩኝ።

በምድር ላይ ትንሹና ተፈጥሮአዊ የሆነው ልዩነት ሴትና ወንድ ሆኖ መፈጠር ብቻ ይመስለኛል። የተቀረው ሁሉ ሰው ሠራሽ የማኅበራዊ ኑሮ ውጤት ነው። መውለድ የመቻል ጸጋ ሴትን ሊያተልቅ እንጂ ሊያሳንሳት እንደማይችል እሙን ነው። እናቱን ፍጹም እያከበረ በሌሎች ሴቶች ላይ ጥቃት የሚያደርስ ወይም ሴቶችን የሚንቅ ሰውም፣ ደካማ የሆነ ማኅበራዊ ስርዓት ውጤት እንደሆነ ግልጽ ነው። እህቱን እየጠበቀ ሌላዋን የሚጎዳም ከዚህ የተለየ አይደለም።

ትግላችን ከወንዶች ጋር ነው ወይስ ከስርዓት ጋር? ‹ሙያ የሌላት ሴት እንዳታገባ! ቤት ውላ ልጆችህን ካልጠበቀች ምኑን ሚስት ናት!› ብለው የሚመክሩ እናቶች አሉ። እና እንዴት ነው ወንዶችን ብቻ መጠየቅ የሚቻለው? ‹የምን ሰው ፊት መውጣት ነው! ሴት ልጅ ሰብሰብ ስትል ነው!› የሚሉ አክስቶች ካሉ፣ ትግላችን ከማን ጋር ሊሆን ነው?

አዲስ መንገድ እንሂድ እንጂ! ማን እንዲለወጥ ነው የምንፈልገው? ምን እንዲለወጥ ነው የምንፈልገው? መድረክ ስናገኝና ብዙ ሰሚ ባለበት አደባባይ ላይ እንዴት ያለ ደወል ደውለን አድማጭን እናንቃ?

የሴቶች የእኩል መብት ጥያቄ የወንዶችን መብት መንጠቅ ወይም ከወንዶች እኩል መብት ማግኘት አይደለም። እንደ ሰው መብትን ማስከበር ነው። ጉዳዩ ለምን ለወንዶች ተፈቀደ ሳይሆን ለምን ለሴቶች ተከለከለ ነው። አለበለዚያ ትግላችን በአንድ ጎን ከስርዓት ጋር በሌላ በኩል ከወንዶች ጋር ይሆናል ማለት ነው። እንዲህ ውሉን ያልለየ ጥያቄ መልስም አያመጣ፣ ለውጥም አያስገኝ።

የእኩልነት ጥያቄን አጉልታችሁ የምታነሱ እህቶቼ! የልባችሁ የሚደርሰው በሴቶች ላይ የደረሰ በወንዶችም ላይ ሲደርስ ነው? ወንዶቹን ‹እሰይ! እናንተም ቅመሷት!› ማለት መቻልስ የትግሉ ፍጻሜ ነው? አይመስለኝም። የሴቶች ጥቃት የሚቀንሰው፣ እኩል መብት የሚከበረው፣ ሕገመንግሥቱን ወይም የሃይማኖቱን መጽሐፍ በሴቶች አንቀጽ ስንጽፍ አይደለም። ሁለቱንም በስርዓት የሚያከብር፣ በስርዓት የሚመራ ትውልድ ሲፈጠር ነው። ለዚያ ደግሞ ተመሳሳይ መንገድ ሄደን ጠያቂውን መቀየር ሳይሆን ጥያቄው መልስ አግኝቶ ዳግም እንዳይጠየቅ ማድረግን ግብ እናድርግ!
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here