በዓለማችን ካሉ ተላላፊ በሽታዎች ቀዳሚ ሆኖ ብዙዎችን በመግደል የሚታወቀው ሳንባ ነቀርሳ ነው። እስከዛሬ ብዙዎችን ከገደሉ ዝነኛ ከሆኑ ተላላፊ በሽታዎች ይልቅ ቲቢ (ቱበር ክሎሲስ) በመባል የሚታወቀው ይህ የሳንባ ነቀርሳ በሽታ በዓለም ዙሪያ ብዙዎችን እየገደለ ያለ አሳሳቢ በሽታ መሆኑ ይነገርለታል።
ብዙዎችን ከመግደል ባሻገር አገራትን ብዙ ወጪ በማስወጣትም የሚታወቀው ይህ በቀላሉ ሊተላለፍ የሚችል በሽታ፣ እስካሁን ከታወቀ ብዙ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ግንባር ቀደም ገዳይነቱን መቀነስ ግን ሳይቻል ተኑሯል። ከመተንፈሻ አካል ጋር በተገናኘ ያጠቃውን ሰው በቀላሉ ለሞት ሊዳርግ የሚችለውን ይህን በሽታ ለመከላከልም ሆነ ለማከም ብዙ ተመራማሪዎች ለበርካታ ዓመታት ጥረት ቢያደርጉም፣ እስካሁን ውጤታማ መሆን ባለመቻላቸው አሁንም ገዳይነቱ እንደቀጠለ ነው።
መንግሥታትም ሆኑ ግብረ-ሰናይ ተቋማት በሽታውን ለመከላከልም ሆነ ገዳይነቱን ለመቀነስ እንዲሁም ሥርጭቱን ለመግታት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም፣ መጠነኛ መሻሻል ከማሳየታቸው በስተቀር ሙሉ በሙሉ መፍትሔ ማግኘት ሳይቻላቸው ቆይተዋል። በሽታው ላይ የሚደረግ ጥናትና ምርምር ከፍተኛ ቢሆንም፣ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ማነቆዎችና ሌሎች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በዘርፉ ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት እንደሆኑ ይነገራል።
በሳንባ ነቀርሳ ዙሪያ የሚከሰት ጉዳትንም ሆነ ሞትን ለመቀነስ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት ከሚያደናቅፉ ምክንያች መካከል የኮሮና ቫይረስ አንዱ ነበር። የሕክምና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና ድጎማ የሚያደርጉ መንግሥታዊም ሆኑ ገለልተኛ ግብረ-ሰናይ ተቋማት ሙሉ ትኩረታቸውን በወረርሽኙ ላይ እንዲያደርጉ ማድረጉ ይታወሳል። ይህም በመሆኑ የሳንባ ነቀርሳ ታማሚዎች ሊያገኙ የሚገባቸውን ትኩረት በአግባቡ እንዳያገኙ፣ እንዲሁም ኹሉ ነገር ወደኮሮና ቫይረስ ሕክምና እንዲዞር ተደርጎ ስለነበር የበሽታው ሥርጭትና ጉዳት መጨመሩን የሚናገሩ አሉ።
በተቃራኒው፣ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ተብለው የተወሰዱ ዕርምጃዎች ቲቢን የመሳሰሉ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎች ሥርጭትን ለመቀነስ አግዘዋል ብለው የሚከራከሩም አሉ። ወረርሽኙ እጅን በአግባቡ እንዲታጠቡ ማድረግ በመቻሉ በመጠኑም ቢሆን ከንፅህና ጋር የተያያዙ በሽታዎችን መቀነስ መቻሉም ይታመናል። በተመሳሳይ የአፍንጫና አፍ መሸፈኛ በመዘውተሩ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎችን ሥርጭት ለመቀነስ መቻሉም ይነገራል። ይህ ግምት ግን በሳይንሳዊ መንገድ ያልተረጋገጠና በጥናት ያልተደገፈ በመሆኑ ራሱን የቻለ ምርምርና ምልከታ እንደሚፈልግ ባለሙያዎቹ ይስማማሉ። ያም ተባለ ይህ ግን፣ የአንድ ነገር ክስተት ለሌላው ኹኔታ መለወጥ መንስዔ ወይም ሰበብ ሊሆን እንደሚችል ነው።
ከሳንባ ነቀርሳ በሽታ ጋር በተገናኘ ለሕክምናው እንቅፋት ሁነዋል ከሚባሉ ምክንያች መካከል ጦርነት ዋነኛው ነው። በኢትዮጵያ፣ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታንና የመን፣ እንዲሁም በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተከሰተው ጦርነት ለብዙዎች ሞት ምክንያት የሆነ ነው። በቀጥታ በውጊያ ከሚሞቱት በተጨማሪ፣ ከጦርነቱ ጋር ምንም ግንኙነት ሳይኖራቸው ሕክምና በማጣትም የሚሞቱት ቁጥርም ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ይነገራል።
ከጦርነት ጋር በተገናኘ የሚከሰተው ችግር ዘርፈ ብዙ ቢሆንም የሕክምና ዕጦት በግንባር ቀደም ከሚጠቀሱት መካከል ይመደባል። የተዋጊዎች መቁሰል እንዲሁም ንጽኃን ላይ የሚደርሰው የመቁሰል አደጋም ከፍተኛ ስለሚሆን የሕክምና ባለሙያዎች ሙሉ ትኩረታቸውን እንዲሰጡዋቸው ይደረጋል። በዚህም ሳቢያ ሳንባ ነቀርሳን ለመሳሰሉ ተላላፊ ገዳይ በሽታዎች የሚሰጥ ትኩረት እንዲቀንስ ያደርጋል።
በጦርነት ወቅት ትክክለኛ መረጃ ለመያዝም ሆነ ከቆመ በኋላ ጥናት ለማድረግ ኹኔታዎች ስለማይፈቅዱ፣ ልክ እንደጦርነቱ ሰለባዎች ቁጥር በሕክምና ዕጦት የሚሞቱትን ቁጥር ማወቅ ባይቻልም ከፍተኛ መሆኑን መገመት ይቻላል። በተለይ ጦርነቱ ከተጀመረ ረጅም ጊዜን በሚያስቆጥርበት ወቅት ኹኔታዎችን ወደነበሩበት መመለስ ስለሚያስቸግር ችግሮች እየተባባሱ እንደሚሔዱ ይታወቃል። ለምሳሌ ያህል አንድ ወር እያስቆጠረ ያለው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከጀመረ አጭር ጊዜ ነው ሊባል ቢችልም፣ ከአድማሱ ስፋትና ከተካሄደበት ወቅትና አካባቢ አኳያ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተገምቷል። ጦርነቱ በዚህ በአጭር ጊዜ ለበርካታ መፍትሔዎች መሰናክል እንዲሁም ለጥፋቶች መንስዔ መሆኑ ተነግሯል። ሕክምናና መድኃኒትን መቋቋም የሚችል የሳንባ ነቀርሳ ዝርያን ለመዋጋት የሚካሄደውን የተቀናጀ ዕርምጃንም ጦርነቱ ወደኋላ እንደሚጎትተው ተመራማሪዎች መናገራቸውን ‹ፈርስት ፖስት› ዘግቧል።
በጦርነት ወቅት የሕክምና ተቋማት ስለሚወድሙና የጤና ተቋማት አሠራራቸው ስለሚስተጓጎል ቀላል ሊባሉ በሚችሉ በሽታዎች በርካቶች ይሞታሉ። በተለይ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠር በየአገራቱ የተዘረጉ አሠራሮች ስለሚቋረጡ፣ ቲቢን ለመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች መስፋፋት በር ይከፍታል። በሕምና ዕጦት ብዙዎች እንዲሞቱ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ሥርጭቱን ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን ማስገደድ ስለሚያስቸግርም ወደ ወረርሽኝ ደረጃ በቀላሉ ሊያድጉ የሚችሉበት አጋጣሚም ሠፊ ነው።
በጦርነት ወቅት ከአደጋ ለማምለጥ ሕብረተሰቡ ተጠጋግቶ የሚኖርበት ወይም በጊዜያዊነት የሚጠለልበት ኹኔታ፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚፈናቀልበትና የሚሰደድበት አጋጣሚ ስለሚጨምር፣ በሳልና በትንፋሽ ሊተላለፉ የሚችሉ ሳንባ ነቀርሳን ለመሳሰሉ በሽታዎች ምቹ ኹኔታን ይፈጥራል። ቲቢ በሕክምና ሊድን የሚችል በሽታ ቢሆንም፣ አንድ በበሽታው የተጠቃ ሰው ከሕመሙ ለማገገም ሳምንታትን ስለሚወስድበት የጦርነት መኖር ታክሞ በቀላሉ እንዳይድን ያደርገዋል።
በሕክምና ለመዳን አስቸጋሪ የሆኑ መድኃኒትን የመቋቋም ብቃታቸው ከፍተኛ የሆነ የሳንባ ነቀርሳ ዓይነቶችን ለማከም በሠላሙም ጊዜ አስቸጋሪ እንደመሆኑ፣ ጦርነት ሲኖር ደግሞ የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል። በእነዚህ ሕክምናውን መቋቋም በሚችሉ ዝርያዎች የሚጠቃው የዓለማችን ሰው ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን፣ ቢያንስ በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊየን ሰዎች በላይ ይያዛሉ። እንዚህን ሰዎች አክሞ ጤነኛ ለማድረግ የተለያዩ መድኃኒቶች በማቀናጀት ለረጅም ጊዜ መንከባከብ ስለሚያስፈልግ የጤና ተቋማት መውደምም ሆነ የመድኃኒት ዕጦት በዘርፉ ለሚደረገው አዎንታዊ እንቅስቃሴ መሰናክል ይሆናል። ሕክምናው እስከ ኹለት ዓመት ሊወስድ ስለሚችል፣ እንዲሁም የሚወሰዱት መድኃኒቶች የተለያዩ እንደመሆናቸው ያልተገመቱ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትሉ በመቻላቸው ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ጦርነት በሚኖርበት ወቅት ከባለሙያ ዕጥረት አንስቶ አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላት፣ እንዲሁም አገልግሎቱን እንደአስፈላጊነቱ መስጠት አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የሳንባ ነቀርሳ ወረርሽኝ ከተከሰተባቸው የዓለማችን ክፍሎች መካከል የምሥራቅ አውሮፓና የቀድሞ የሶቭየት ሪፐብሊክ ግዛቶች ውስጥ የተከሰተው በዋናነት የሚጠቀስ ነው። የሶቭየት ሕብረት መፈራረስን ተከትሎ በአባል አገራቱ ውስጥ የነበረው የጤና አገልግሎት እንደኢኮኖሚው በመሽመድመዱ ብዙዎችን ለዕልቂት የዳረገው የሳንባ ነቀርሳ ወረርሽኝ እንዲከሰት ምክንያት ሆኖ ነበር። የሕክምና መሠረት ልማቶች መፈራረሳቸውና የመድኃኒት አቅርቦቱ መቋረጡ በሽታውን ለመከላከል ይደረግ የነበረን እንቅስቃሴ ስለሚያቋርጠው በርካቶችን ለበሽታ ያጋልጣል።
ለአንድ ወር የዘለቀው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትም ከዚህ ቀደም ወረርሽኝ የተከሰተበት አካባቢ እንደመካሄዱ አሁንም በበሽታው በርካቶች ሊጠቁ ይችላሉ የሚል ሥጋትን አሳድሯል። ሳንባ ነቀርሳ ከኤች አይ ቪ ጋር ባለው ቁርኝት ሳቢያ ጦርነቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የቫይረሱ ተጠቂ ቁጥር እጅግ ጨምሮ የነበረ በመሆኑ፣ ለቲቢ የሚጋለጡና ለሞት የሚዳረጉትም ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል። ጦርነቱ የሚካሄድባት ዩክሬን በሳንባ ነቀርሳ ተጠቂዎች ቁጥር ከአውሮፓ ቀዳሚዋ እንደመሆኗ፣ ምንም በዘርፉ እመርታ እያሳየች የነበረ ቢሆንም፣ ውጊያው በቀጠለ ቁጥር በበሽታው የሚጠቁባት ዜጎቿ ቁጥር እንደሚያሻቅብ ተጠቁሟል። አገሪቱ በቲቢ ከተያዙ ዜጎቿ ሲሶ የሚሆኑት መድኃኒትን መቋቋም በሚችለው ዓይነት ዝርያ የተያዙ እንደመሆናቸው ሊደርስ የሚችለው ሰብዓዊ ቀውስ ከፍተኛ እንደሚሆን ተገምቷል።
ጦርነት ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች እንዲዛመቱ በማድረግ ትልቅ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ውጊያው ለሚካሄድባቸው አገራት ብቻ ሳይሆን፣ በአቅራቢያ ለሚገኙ አገራትም ሆነ ለመላው ዓለም ሥጋት መሆኑ አይቀሬ ነው። በተደጋጋሚ እንደታየው ጦርነት ባለበት አገር ያልታሰበ ወረርሽኝ ድንገት ይከሰታል። ለዓመታት በዘለቀው የየመን ጦርነት የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቶ በርካቶችን ለሞት ዳርጓል። በሶሪያ የተከሰተው የፖሊዮ በሽታም ሌላው ምሳሌ ሲሆን፣ በአፍጋኒስታንም የኩፍኝ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር ተመዝግቧል። የመጀመሪያውና የኹለተኛው ዓለም ጦርነቶች በተካሄዱበት ወቅት በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ሳቢያ የሞቱት ቁጥር ወደር የማይገኝለት እንደነበረም ይነገራል።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014



