“የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሻሻል የሚረዳ ፖሊሲ የለንም”

0
1498

ለማወርቅ ደክሲሶ ትውልድና ዕድገታቸው አርሲ ነው። በትምህርት ዝግጅታቸው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን በማኅበረሰብ አገልግሎት ከኢንድራ ጋንዲ ናሽናል ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።
ለማወርቅ ላለፉት 12 ዓመታት በመንግሥት ተቋማት እና በተለያዩ አገር በቀልና ዓለም ዐቀፍ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት በተለያዩ የሥራ መደቦች አገልግለዋል። አሁኑ ላይ በተለይ በሥራ ፈጠራ ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ በሚሠራው ‹ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት› ከፍተኛ የፕሮጀክት አስተባባሪ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ ዘርፍና ሥራ አጥነት ጉዳይ ላይ አትኩረው ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት፣ ኢንተርፕርነር ዘርፍ ላይ እንደመሠማራቱ ምን እየሠራ ነው?
ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት እንደማንኛውም አማካሪ ደርጅት የማማከር ሥራዎችን ይሠራል። አጠቃላይ ፕሮጀክቶችን ከማዘጋጀት ጋር የተገናኙ ሥራዎችን እንሠራለን። እንደ ተሠማራንበት ዘርፍ ትኩረት ከምናደርግባቸው ጉዳይች አንዱ ኢንተርፕርነርሽፕ ሥልጠና፣ ቢዝነስ ዴቨሎፕመንትና የማይንድ ሴት ሥልጠናዎችን እንሠጣለን።

እነዚህ ዘርፎች በደንብ ልምድ ወስድን በትኩረት የምንሠራባቸው ጉዳዮች ናቸው። ስለዚህ ብሩህ ማይንድስ በዘርፉ ላይ እንደሚሠራ ተቋም ልዩ ምልከታ የሚለውን ውይይት የጀመርነው ለዚህ ነው። ይመለከተናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ኢንተርፕርነርሽፕ ብዙ ተለፍቷል፤ ብዙ ተወርቷል። መንግሥት በበኩሉ ብዙ ጥረት ጥሯል፤ የግል ተቋማትም ይሞክራሉ ግን በሚፈለገው ደረጃ ሥራ መፍጠር አልተቻለም። በሚፈለገው ደረጃ ወጣቶቻችን ወደ ሥራ እየተሠማሩ አይደለም። ይሄ በአግባቡ ካልተፈታ ደግሞ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ችግርም ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህ እንደ አንድ ኢንተርፕርነርሽፕ ላይ እንደሚሠራ ተቋም ብሩህ ማይንድስ ኮንሰልት በየወሩ የሚካሄድ ልዩ ምልከታ የተሠኘ የምክክር መድረክ ጀምሯል።

“ልዩ ምልከታ” የተሠኘው ወርኃዊ የውይይት መድረክ ዓላማው ምንድን ነው?
ዓላማው ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ፈጠራ ዘርፉን ማበረታታት ነው። ሥራ ፈጠራ ላይ በርካታ የአሰራር፣ የአተገባበር ክፍተቶች አሉ። እነዚያን ክፍተቶች በማረቅ፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው መነጋገር። የሥራ ፈጠራ በተፈለገው ደረጃ እንዳያድግ ተግዳሮት የሆኑ ችግሮችን መቅረፍና የቢዝነስ ኢኮ ሲስተሙን ማሻሻል ነው።

የሥራ ፈጠራ ‹ኢኮ-ሲስተም›ን ማሻሻል የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ አይደለም፤ የግሉ ዘርፍ መሰማራት አለበት። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም እዚህ ላይ በጣም ውጤት ሊመጣ በሚችል ልክ መሰማራት አለባቸው። ፖሊሲ ላይ ክፍተቶች ካሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማደረግ ያስፈልጋል። አሠራር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ባለድርሻ አካላት በአንድ መድረክ ተገናኝተው፣ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች፣ ሥራ ፈጠራ ላይ የሚሠሩ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጀምሮ በተዋረድ ያሉ የመንግሥት ተቋማት፣ የፖሊሲና የምርምር ተቋማት በየደረጃው ችግሩን በጋራ ለመፍታት እየተነጋገርን ብንሔድ ይሻላል።

እንደ አገር ሥራ ፈጠራ ላይ የሚባክነው ሀብት ቀላል አይደለም። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትልቅ በጀት ይዘው ይመጣሉ። ምን ያክል ውጤታማ ሆኗል የሚለው በደንብ መታየት አለበት። መንግሥት ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሁን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አቋቁሟል፤ ጥረት አድርጓል ማለት ነው። ይሄ ነገር ግን የሥራ አጥ ችግሩን እንዲፈታ የአሠራር ክፍተቶች ካሉ እየተነጋገሩ ፣ የአሠራር ክፍተቶቹ እየተቀረፉ መሔድ አለባቸው።

በየዓመቱ ከኹለት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ገበያውን ይቀላቀላሉ። ባለፉት ሦስት ዓመታት የቀረቡ ሪፖርቶች አሉ። በመጀመሪያው ዓመት የቀረበ የሥራ ዕድል ሪፖርት አለ፣ በእውነት እነዚያ የቀረቡ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል ወይ የሚለው መታየት አለበት። በእነዚህ ኹለት ዓመታት ደግሞ እየተንገዳገደ ባለው ኢኮኖሚያችን ላይ የሥራ አጥነትና ሌሎች ጫናዎች ተጨምረው፣ አሁን የዋጋ ግሽበት ተጨምሮበት ብዙ ነገሮች ከፍተኛ ጥረት የሚፈልጉበት ሠዓት ነው። ስለዚህ ያለችንን ሀብት በደንብ ተጠቅመን የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ብንሠራ በሚል ነው የተነሳነው።

እስካሁን ባደረጋችኋቸው የሥራ ፈጠራ የውይይት መድረኮች ላይ ምን ምን ነጥቦችን አነሳችሁ?
በመጀመሪያ ዙር የተነሳው የሥራ ፈጠራ ባህል በኢትዮጵያ ምን ይመስላል የሚል ነው። የሥራ ዕድል በኢትዮጵያ የተጀመረው ምናልባት መካከለኛው ዘመን በሚባለው ከአጼ ዘርዓያዕቆብ ጀምሮ ነው። የጌታና የሎሌ ሥራ ቀርቶ በደመወዝ ሰው በሠራበት እንዲከፈለው የሚያደርጉ ነገሮች ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ ተሻሻሉ፤ በአጼ ምኒልክ ደግሞ 11 ሚኒስቴር ያለው ካቢኔ ሲቋቋም የመንግሥትን መዋቅር ለሥራ ምቹ እያደረጉ እንደመጡ እናያለን።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቋቋመችው በ1957 ነው። ከዚያ በኋላ ሚኒስቴሩ የሥራ ፈጠራ ጉዳይን በዋናነት የሚሠራ፣ ለመንግሥት ተቋማት ሰው ኃይል የሚመድብ ነው።

ከኢሕአዴግ መምጣት በኋላ የግሉ ዘርፍ መስፋፋት ሲጀምር፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ፖሊሲ ሲዘጋጅ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ትንሽ የሥራ ፈጠራን አስፍተውታል። ይሄ በ1997 የወጣው ዐዋጅ ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ዕድልን ማስፋፋት ችሏል። ከዚያ በኋላ ደግሞ እነዚያ ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች በሚፈለገው ደረጃ ወደ መካከለኛና ከፍተኛ እያደጉ፤ ከሥር ደግሞ ለሌሎች ወጣቶች እንዲተኩ ፖሊሲው በፈለገው ደረጃ የተሳካ አይደለም።

በ2010 የሥራ ፈጠራ ኮሚሽን አቋቁማለች። አሁን ላይ ደግሞ ተሸሽሎ በሚኒስቴር ደረጃ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሆኗል። እነዚህ ኹሉ ተቋማት ግን በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ አምጥተዋል ወይ የሚለው በመጀመሪያ አይተናል።

በኹለተኛው የውይይት መድረክ ላይ የተነሳው ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርፕርነርሽፕ ፖሊሲ አለን ወይ የሚል ነው። ኢትዮጵያ ውሰጥ በግልጽ የተቀመጠ የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚያትት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሻሻል የሚረዳ ፖሊሲ የለንም። ሌሎች አገራትን ስንመለከት፣ እንደው በቅርብ ኬኒያን እንኳን ብንመለከት የሥራ ዕድል ፈጠራ ፖሊሲ አላት። የሥራ ዕድል ፈጠራ ፖሊሲዋ ከኢንደስትሪ ፖሊሲ፣ ከመሬት ፖሊሲ፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ፖሊሲ፣ ከወጣት ልማት ፖሊሲ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ ነው።

የሥራ ዕድል ፈጠራ ፖሊሲ አለመኖሩ ብዙ ጉዳቶች አሉት። ፖሊሲ ማነው ሥራ ፈጣሪ? ለሥራ ፈጣሪዎች የሚገቡዋቸው ማበረታቻዎች፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ አሠራሮች፣ ሥራ ፈጣሪ ምን ይጠበቅበታል? የሚለውን በግልጽ ማስቀመጥ አለበት። ፖሊሲ ቢኖረን ከውጭ የሚመጡ የፓተንት መብታችንን እናስከብር ነበር። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሠራን ነገር በውጭ አገር ሠርተው እያመጡልን ነው። ፖሊሲ ቢኖረን ግን ይሄንን መካላከል እንችል ነበር። የኛ ምርቶች በውጭ አገር ከደረጃ በታች እየተመረቱ ለገበያ እየቀረቡ ነው።

ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ የማምረቻ ቦታ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም። እነዚህ ነገሮችን በደንብ ማየት ካልቻልን ያስችግረናል። የሥራ ፈጠራ ፖሊሲ ስናዘጋጅ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲያችንን ማየት፣ የኢንቨስትመንት ፖሊሲያችንን ማየት፣ የንግድ ፖሊሲያችንን ማየት ይፈልጋል።
የሥራ ዕድል ኮሚሽን ፈጥሪያለው የሚላቸው ሥራዎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚፈጠሩት እየተቆጠሩ ነው። የበለጠ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሥራ ዕድል ምኅዳሩን ማስፋት አለብን። ኢትዮጵያ ውስጥ ሠፊ የሆነ የውኃ ሀብት፣ የሰው ኃይልና መሬት አለ። እነዚህን አጣጥሞ መሔድና ግብርና ላይ መሥራት ይገባል። ምክንያቱም የኢኮኖሚ ዕድገታችን የምናረጋግጠው ግብርና ላይ በርተተን ስንሠራ ነው። የግብርና ምርታችን የተትረፈረፈ ካልሆነ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ማቅረብ አንችልም።

እኛ ከ110 ሚሊዮን በላይ የሰው ኃይል አለን፣ ሠፊ ያልታረሰ መሬት አለን፣ የውኃ ሀብት አለን፣ እነዚያን አልተጠቀምንም። ስለዚህ ወጣቶቻችን ሥራ ፈላጊዎች አንጂ ሥራ ፈጣሪዎች አልሆኑም ብለን ለመውቀስ የሥራ ፈጠራ ምኅዳሩ ምቹ ነው ወይ? በየከተማው የሚፈጠሩ ትንንሽ ሥራዎችን እያሳደድን መኖር እንችላለን ወይ ይሄ ካልሆነ?
ኢንዱስትሪ ፓርክ እየገነባን ነው። የገነባናቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግብዓት ከውጭ የሚያስመጡ ናቸው። የግብርና ምርትን ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ማቅረብ ካልቻልን የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጥ ከባድ ነው የሚሆነው።

በኢትዮጵያ በሥራ ፈጠራ ዘርፍ ላይ ያለው መሠረታዊ ችግር ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ ያለውን መሠረታዊ የሥራ ፈጠራ ችግር አንድና ኹለት ብለን የምንገልጸው አይደለም። ዘርፉ በውስብስብ ችግሮች የተያዘ ነው። ዋና ዋና ችግሮችን ብናይ፣ አንደኛ የሥራ ፈጠራ ፖሊሲያችን መታየት አለበት፣ ኹለተኛ የሥራ ፈጠራ ግንዛቤያችን ምንድን ነው? እንደ አገር ምንድን ነው ያለን አቅም? የትኛው ላይ ነው ሥራ መፍጠር ያለብን? የሚለውን ማየት አልቻልንም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግብርናን ከሚገባው በታች ነው እየተጠቀምነው ያለነው። ስለዚህ ግብርና ላይ በደንብ መሥራት አለብን።

የሥራ ፈጠራ ባህላችንን ስንመለከት፣ ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ባህል አልነበረንም። ለሦስት ሺሕ ዓመት እንደኖረች ኢትዮጵያ፣ ከሦስት ሺሕ ዓመት በፊት ቀጥቅጠን በምንጠቀመው ማረሻ ነው ዛሬም እያረስን ያለነው። ብረት ቀጥቅጠው ማረሻና ሌሎች መገልገያዎችን የሚሠሩልንን አላከበርናቸውም። ፈትለው ሸምነው (ይሄን የመሰለ) ባህላዊ ልብስ የሚያለብሱን ወገኖቻችንን አላከበርናቸውም። ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ፈጠራ ባህላችን በጣም የቀጨጨ እንዲሆን አድርጎታል።

ዛሬም ላይ ስንመጣ የትምህርት ፖሊሲያችን ይሄን ነገር ለማዘመን አላገዘንም። የትምህርት ፖሊሲያችን ሥራ ፈጣሪ እንድንሆን ሳይሆን ሥራ ተቀጣሪ መሆን እንድንችል ነው እያደረገን ያለው። የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አሉ። እዚያ ላይ በርካታ ጥረቶች ይደረጋሉ፣ ግን በሚገባ ቁጥጥር ስላልተደረገበት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆቻችን ሀብት የሚያባክኑ ናቸው እንጂ ሥራ የሚፈጥሩ ተቋማት እየሆኑ አይደለም።

የግሉ ዘርፍ ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በደንብ መቆጣጠር ይጠይቃል። ባለሀብቶቻችን ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ከመሠማራት ይልቅ ሰርቪስ ዘርፍ ላይ ነው ትኩረታቸው። ሕንጻ ገንብተው ማከራየት፤ ሪል እስቴት መሥራት። ላኪዎች በሚያገኙት ዶላር መኪናና ኮስሞቲክስ እንጂ ማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ማሽነሪ አምጥተው ማስፋፋት ላይ ከባለሀብቶች በኩል አይታይም።

ወጣቶቻችንም፣ በጣም ቀላል አገልገሎቶችን ነው የሚፈልጉት። ከዚያ ያለፈ እንደ አገር ግብርና ላይ የሚሠሩ ሥራ ፈጣሪዎች የሉም። ሥራ ፈጠራችንን ለማሻሻል የሁላችንንም ርብርብ ይፈልጋል። ወጣቱና ባለሀብቱ ማንፋክቸሪንግ ላይ መሥራት፣ መንግሥት ማንፋክቸሪንግና ግብርናን ማበረታታት አለበት። እያበረታታ አይደለም እያልኩ አይደለም፣ ግን በጣም መሥራት አለበት። እንደ አገር ሸማች ማኅበረሰብ ነው ያለን፤ ስንዴ፣ ዘይት፣ በርበሬ ሸምተን ነው የምንኖረው። ስለዚህ እንደ አገር ከሸማችነት ወደ አምራችነት መሸጋገር አለብን።

በየዓመቱ ከዩኒቨርስቲ የሚወጡ ምሩቃንን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ አጥ እየሆኑ ነው። አንደ አገር ለምን ሥራ መፍጠር አልተቻለም? ምንስ ጉዳት ያስከትላል?
ለምን ሥራ መፍጠር አልተቻለም ለሚለው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ዋነኛው የሥራ ፈጠራ ምኅዳራችን በጣም ጠባብ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ውሰጥ ያሉት ኢንዱስትሪዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ከ50 በመቶ በታች ነው እየሠሩ ያሉት። ለምናስመርቃቸው ምሩቃን ምቹ የሥራ ፈጠራ ምኅዳር ከፈጠርን ወጣቱ ሥራ መፍጠር ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ በሥራ ፈጠራ አሠራሮች ላይ ከላይ እስከ ታች የሚታዩ የአሠራር ክፍተቶች አሉ። እንደ መንግሥት፣ እንደ ግል ድርጅት የሥራ ፈጠራ አሠራሮቹ ሥራ ለመፍጠር ምቹ አይደሉም።

የሥራ አጥነት ምን ያስከትላል ላልከው፣ መልሱ ይታወቃል። አንደኛ አምራች ዜጎቻችንን በአግባቡ አለመጠቀማችን፣ አምራች ዜጎቻችንን እያባከንን ነው። ስለዚህ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አዳጋች ይሆንብናል፤ ልማታችንን ዘገምተኛ ያደርገዋል።

ኹለተኛ እነዚህን ወጣቶች በአግባቡ አለመጠቀማችን፣ እነዚህ ወጣቶች ሳይፈልጉ በግድ ወደ አጉል መንገድ እየመራናቸው ነው። ወደ ወጣት ሱሰኝነት ብሎም እስከ ማኅበረሰብና አገር ድረስ አደጋ እስከመሆን ይደርሳል። ይሄ በደንብ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ያለንን የሰው ኃይል ተጠቅሞ ወደሚፈለገው ልማት መግባት ሲገባ፣ በሚገባ ባለመጠቀም ወደ ጥፋት እንዲሔዱ እየገፋናቸው ነው። ይሄ ደግሞ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አደጋ ያስከትላል ማለት ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሠተው የሥራ አጥ መበራከት ተጠያቂው ማነው?
ተጠያቂው በየደረጃችን ኹላችንም ነን። ከወጣቶቹ ብንጀምር እውነት ሥራ ለመፍጠር ተፍጨርጭረን የወጣነው ስንቶቻችን ነን? ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር ተነሳሽነቱ አለን ወይ? ከአራት ዓመት በፊት መንግሥት 10 ቢሊዮን ብር ለሥራ ፈጠራ መድቦ ነበር። ምን ያክል ወጣት ያንን ገንዘብ በአግባቡ ተጠቅሞ ተለወጠበት? ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ክህሎታችንን ማሳደግ አለብን።

እንደ ማኅበረሰብ ሥራ ፈጣሪን አለማክበራችን፣ ሥራ ፈጣሪን እንደ ጀግና አለመቁጠራችን ሌላ ችግራችን ነው። የግሉን ዘርፍ ስንመለከት ሥራ ፈጣሪነትን ለማስፋፋት የበኩሉን ያደርጋል ወይ? ቅድም እንዳልኩት ባለሀብቱ ሕንጻ ገንብቶ ኪራይ መሰብሰብና ቁጭ ብሎ የሚሸመጠጥ ገቢ ላይ ነው ትኩረቱ። ለበርካታ ወጣቶች ሥራ መፍጠር በሚችለው ማንፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ባለሀብቶቻችን ደፍረው ይገባሉ ወይ የሚለው ሌላው ጉዳይ ነው።

ወደ መንግሥት ስንመጣ ያለው ችግር አንድና ኹለት ብለን የምንጨርሰው አይደለም። የፖሊሲ ክፍተት አለ፤ የአፈጻጸም ከፍተት አለ፤ የአሠራር ክፍትት አለ። አንድ ባለሀብት ግብርና ላይ ለመሠማራት መሬት ቢጠይቅ መሬት ያገኛል ወይ? ኦሮሚያ ክልል ብትሔድ፣ ቤኒሻንጉል ብትሔድ መንግሥት እንደ ውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስለሚቆጥረው ለውጭ ባለሀብት ነው የሚፈቅዱት። ስለዚህ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታታ የመንግሥት አሠራር አለ ወይ? መንግሥት ለባለሀብቶች በተዋረድ የደኅንነት (ሴኩሪቲ) ዋስትና ይሰጣል ወይ? የሚለውን ስናይ ችግር አለ።

የአፈጻጸም ጉዳይን ስንመለከት፣ በየደረጃው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች ይታያሉ። የአገልግሎት ሠጭ ሠራተኞችን ብቃትና ፍላጎት በደንብ መታየት አለበት። ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት የኹላችንንም ርብርብ ይጠይቃል።

እንደ አገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ወይም ወጣቱን ወደ ሥራ ለማስገባት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
እንደ አገር የሚጠበቅብን ተቀናጅቶ፣ ተናብቦ መሥራት ነው። መንግሥት ከልማት ድርጅቶች ጋር፣ ከግል ድርጅቶች ጋር ተናብቦ መሥራት አለበት። ያለመናበብ ችግሮች ይስተዋላሉ፣ መንግሥት የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ ብሎ ብዙ ሀብት ያፈሳል። ብዙ ሀብት የሚፈሰው ወርክሾፕና ስብሰባ ላይ ነው። አያስፈልጉም እያልኩ አይደለም፤ ስብሰባዎቹ ከልብ ወደ ተግባር ተቀይረው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት በሚችሉበት ኹኔታ ተግባራዊ ይደረጉ ነው።

መንግሥት የሥራ ዕድል ፈጠራን ላስፋ ብሎ ትልቅ ወርክሾፕ ያዘጋጃል፤ በተመሳሳይ ሌላ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ደግሞ ሌላ ተመሳሳይ ወርክሾፕ ያዘጋጃል። ለምን አስፈለገ? መንግሥት ባደረገው ወርክሾፕ በተነሱ ሐሳቦች ላይ ወደ ተግባር መግባት ይቻላል። ስለዚህ ተቀናጅቶና ተናቦ መሥራት አንደኛው ነገር ነው።

መንግሥት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ቅድሚያ መሥጠት አለበት ብዬ አስባለሁ። አሁንም የሥራ ዕድል መፍጠር ካልቻልን በየዓመቱ የሚፈጠረውን ኹለት ሚሊዮን ሥራ ፈላጊ ወጣት ማሰብ አለብን ማለት ነው። ስለዚህ ከፖሊሲ ማዕቀፍ ጀምሮ፣ ከአፈጻጸም ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ሠራተኞች ኃላፊነት ተሰምቷቸው ከልብ የሚሠሩ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል።

ሦስተኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምኅዳራችንን ለማስፋት ግብርናን በደንብ ማስተዋል አለብን። መንግሥት የጀመረው በጣም ጥሩ ነው። በዚህ ዓመት 16 ሚሊዮን ኩንታል በበጋ መስኖ ስንዴ ይመረታል ተብሏል። ግን ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማማረት ያላት አቅም 16 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ አይደለም። ይሄን በደንብ ማስፋት ነው።

በኢትዮጵያ የሥራ አጥ ጉዳይ ሲነሳ ከመንግሥት ጀምሮ “ወጣቱ ተምሮ ሥራ መጠበቅ የለበትም፤ እራሱ ሥራ ፈጣሪ መሆን አለበት” ይባላል። እውን በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ የሚፈጥሩበት ምቹ ኹኔታ አለ ማለት ይቻላል?
የለም! ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችሉ ምቹ ኹኔታዎች የሉም። ምቹ ኹኔታዎች የሌሉት በዋናነት ደሀ ስለሆንን፣ ምንም ሀብት ስለሌለን አይደለም። ጥቃቅን ችግሮቻችንን መፍታት ስላልቻልን ነው። የሥራ ዕድል ፈጠራ ፖሊሲ ቢኖረን፣ ወጣቶች በምን ዘርፍ ሲሠማሩ ምን ሲደርጉ ሥራ ፈጣሪ ይሆናሉ? በምን ይበረታታሉ? የሚለውን ማስቀመጥ ቢቻል ወጣቶችን ለሥራ ፈጠራ ማነሳሳት ይቻላል።

ከትምህርት ሥርዓታችን ስንነሳ፣ የትምህርት ዝግጅታችን ሥራ ፈጣሪ እንድንሆን የሚያስችል ነው ወይ? ብለን ስናስብ ከፍተት አለ። ስለዚህ የትምህርት አሰጣጣችንን ማስተካከል አለብን። መንግሥት ቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ለማስፋፋት በጣም ብዙ ኢንቨስት እየደረገ ነው። ግን ቴክኒክና ሙያ ላይ ያሉ አስፈጻሚ አካላትን ስንመለከታቸው ለሥራ ፈጠራ ጀርባቸውን የሰጡ ናቸው።

ሌላው የወጣቶች የሥራ ቦታ አፈላላግ ነው። በየዓመቱ ለሥራ ፍለጋ ከሚወጣው ኹለት ሚሊዮን ወጣት አንድ ሚሊዮን የሚሆነው አዲስ አበባ ነው የሚፈልገው። እዚህ አዲስ አበባ የሥራ ቦታ ማሰብም አስቸጋሪ ደረጃ ላይ የደረሰበት ኹኔታ ነው ያለው። ስለዚህ የሥራ ቦታ አንዱ ሌላ ችግር ነው።

ሦስተኛ የፋይናነስ ተደራሽነት አላቸው ወይ? የፋይናንስ ተደራሽነቱን ከኹለቱም አቅጣጫ ማየት አለብን፤ መንግሥት ካለው ሀብት ላይ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማበረታታት ካደረጋቸው ተግባራት መካከል የ10 ቢሊየኑን ማንሳት ይቻላል፤ የአፈጻጸም ክፍተት ቢኖራቸውም። በአማራ፣ በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባዎች ተዘዋዋሪ በጀት (ሪቮልቪንግ ፈንድ) ለማቅረብ በተለያየ ጊዜ ተሞክሯል።

እነዚያ ነገሮች በአግባቡ ጥቅም ላይ ውለው አልተመለሱም። ያ ደግሞ መንግሥትን ተነሳሽነት እንዳይኖረው አድርጎታል። ይሄ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ዓለም ዐቀፍ ግብረ ሰናይ ተቋማትን ጭምር ያሳስባል። ሪቮልቪንግ ሪከርዳችን ጥሩ ቢሆን፣ ሪቪልቪንግ ፈንድ የሚሰጡ ፕሮጀክቶች ይዘው ይመጣሉ። ግን ሪከርዳችን ጥሩ ስላልሆነ እንደዚህ ዓይነት ፈንዶችን አያመጡም። ወጣቶች ገንዘቡን በአግባቡ ተጠቅመው ቢመልሱ፣ መንግሥት ደግሞ ተገቢ ለሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች ብቻ ቢያቀርብ የፋይናንስ ተደራሽነት ችግርን መቅረፍ ይቻላል።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here