በአማራ ብሔራዊ ክልል በአራት ወረዳዎች የኩፍኝ በሽታ መከሠቱን የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ጃቢ ጠህናን፣ ማቻከል፣ ባሶ ሊበን እና ምንጃር ሸንኮራ በተባሉ አራት የክልሉ ወረዳዎች የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ መከሠቱን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፍቅረማርያም ዮሴፍ በሌሎች አካባቢዎችም ሥጋቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ በሽታው ከተጠቀሱት ወረዳዎች ውጭ በሌሎች ቦታዎችም ሊገኝ እንደሚችል ገልጸዋል። የኩፍኝ በሽታ በሰሜን ሸዋ ዞን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ቀደም ብሎ ከየካቲት 05/2014 ጀምሮ ራራቲ፣ ጨርቻ ዮሐንስ፣ አረርቲ ቀበሌ 02፣ ክርስቶስ ሳምራ እና መምሃር አገር በሚባሉ አምስት ቀበሌዎች እንደተከሠተ እና ቀጥሎም በሌሎች ሦስት ወረዳዎች እንደተገኘ ነው በኃላፊው የተገለጸው።
እስካባለፈው ሳምንት ድረስ በተደረገ ምርመራ 28 ያህል ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ኃላፊው ገልጸው፣ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ነው ያመላከቱት። እስካሁን በበሽታው ተይዞ የሞተ ሰው እንደሌለም አስረድተዋል። በተለይ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በሽታው ለመዛመት በምክንያትነት የተነሱት የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የቦታ ምቹ አለመሆን እና የጤና ተቋማት መራቅ ናቸው።
ትኩሳት እና ሽፍታ የበሽታው ዋና ምልክቶች ሲሆኑ፣ የዓይን ሕመም (መቅላት)ና የንፍጥ መዝረብረብ፣ እንዲሁ በሽታው የተያዘ ሰው የሚያሳያቸው ሌሎች ምልክቶች መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመው፣ በሽታው ለሞት የሚዳርግ በመሆኑ እነዚህ ምልክቶች የታየበት ማንኛውም ሰው ወደ ሕክምና ተቋም ሊወሰድ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
በሽታው ወደ ሌሎች አካባቢዎችና ወረዳዎች እንዳይዛመትም የቤት ለቤት ሕክምና፣ ቅኝት ወይም የአሰሳ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በበሽታው የተያዙትን ሰዎች ለይቶ ማከምን እና ቫይታሚን ‹ኤ› ቤት ለቤት መስጠትን የመሳሰሉ የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑ ነው የተነገረው።
በሽታው ለተገኘባቸው ታማሚዎችም የተቻለውን ያህል ሕክምና እየተሠጠ እንደሚገኝ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጨምረው ጠቁመዋል።
እንደ ክልል የበሽታው ሥርጭት መጠን ባፉት ኹለት እና ሦስት ዓመታት በከፍተኛ ኹኔታ እየተስፋፋ ነው ሲል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ አመላክቷል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኩፍኝ በቫይረስ የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን፣ ከሰው ወደ ሰው በከፍተኛ ኹኔታ በመተላለፍም የሚታወቅ ነው። በሽታው በወቅቱ ሕክምና ካለገኘም የዓይን ብርሃንን እስከማሳጣት ሊያደርስ እንደሚችልና ለሳንባ ምች፣ ለአንጎል ዕብጠት ብሎም ለኢንፌክሽን እንደሚያጋልጥ ተጠቁሟል።
አሁን ላይ በተለይ በድሃ አገራት የኩፍኝ በሽታ የክትባት አቅርቦት በበቂ ኹኔታ አለመኖር እንደትልቅ ችግር ይወሰዳል። ክትባቱን ማግኘት እየቻሉ ልጆቻቸው እንዳይከተቡ የሚያደርጉ ወላጆችም በሽታው በሚፈለገው ልክ እንዳይቀንስ ምክንያት እንደሆኑ ይነሳል። ሕጻናት የበሽታው ይበልጥ ተጋላጮች እንደሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በየዓመቱ በኩፍኝ በሽታ ምክንያት በመላው ዓለም 110 ሺሕ ገደማ ሰዎች ሕይወታቸው ያልፋል። ባለሙያዎች እንደሚገለጹትም፣ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚጨምረው፣ ሰዎች ለክትባቱ ባላቸው የተሳሳተ መረጃ፣ እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት ሥርዓቶች በመውደቃቸው ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014



