በትምህርት ሚኒስቴር በጦርነቱ ምክንያት ከትግራይ ክልል አራቱም ዩኒቨርስቲዎች ሠላም ወዳለባቸው የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተዛውረው የተቋረጠ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ የተደረጉ ተመራቂ ተማሪዎች፣ መመረቃቸውን የሚያሳይ ጊዜያዊ የምረቃ ወረቀት አይሠራላችሁም መባላቸውን ተከትሎ ቅሬታ እንደተሠማቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካካል ዳንኤል በቀለ የተባሉት ተመራቂ፣ የተቋረጠ ትምህርታቸውን ሌላ ዩኒቨርስቲ ተዛውረው ቢያጠናቅቁም፣ ትምህርት ሚኒስቴር ጊዜያዊ የምረቃ ወረቀት አልሰጥም እንዳላቸው ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
እንደ ዳንኤል ገለጻ ከሆነ፣ ይሰጣችኋል የተባሉት ትምህርት ካቋረጡበት ጊዜ ወዲህ ያለውን ውጤት እንጂ፣ ለሥራ ቅጥር የሚያገለግል ጊዜያዊ የምረቃ ወረቀት እንዳልሆነ ነው ያብራሩት።
በሌላ በኩል፣ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ነው የምትመረቁት ተብለን በኋላ የገቡ ተማሪዎችን እየጠበቅን ነው ያሉት የሕግ ተማሪው፣ ይህም ጊዜያቸውን እንዲያባክኑ ከመዳረጉም በላይ የሥነ ልቦና ጉዳት እንዳስከተለባቸው ነው የተናገሩት።
ጉዳዩ መፍትሔ ካላገኘ ትምህርታቸውን ቢጨርሱም ያለ ምስክር ወረቀት ሥራ መወዳዳር ስለማይታሰብ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
ሌላኛዋ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩትና በምደባው መሠረት በጎንደር ዩኒቨርስቲ የማኔጅመንት ዘርፍ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ተማሪ ሜላት አብርሃም፣ ትምህርት ሚኒስቴር የምረቃ ምስክር ወረቀት እንደማይሠራላቸው መናገሩን ጠቁመዋል።
“ከዕድሜያችን በላይ ብዙ ነገሮችን አይተናል” ያሉት ተማሪዋ፣ ትምህርት ሚኒስቴር እስካሁን ያሳለፍናቸውን ውጣ ውረዶች ተመልክቶ በጉዳዩ ላይ መፍትሔ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
የጎንደር ዩኒቨርስቲ በበኩሉ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ለተወሰነ ጊዜ አስተምሩ ብሎ አደራ ከመስጠት ውጭ ስለ ምረቃ ወረቀት ያስተላለፈላቸው መልክት እንደሌለ ምላሽ መስጠቱን ሜላት አብራርተዋል።
‹‹ተምረን ምንም ዓይነት ነገር የለንም፤ የሦስት ዓመት ልፋታችን ከንቱ ነው የሆነብን›› የሚሉት ሜላት፣ መቀሌ ዩነቨርስቲም ‹‹ የግሬድ ስሊፕ›› እንጅ የውጤት ሪፖርት አይሰጠንም ነበር ሲሉ አክለዋል።
ወልቂጤ፣ ዲላና ሐሮሚያን ጨምሮ ወደ ስድስት የሚጠጉ ዩኒቨርስቲዎች በጊዜያዊነት የተመደቡ ተማሪዎችን እንዳስመረቁና በማስመረቅ ሒደት ላይ እንደሆኑም ሜላት ጠቁመዋል።
ሌላኛው ሚካኤሌ የማነ የተባሉት ተመራቂ ተማሪ የአንድ ሴሚስተር ውጤት ይዘን መስፈርቱን ሳናሟላ የትኛው መሥሪያ ቤት ነው በቅጥር የሚያስተናግደን ሲሉ ጠይቀዋል። አክለውም፤ “ትምህርት ሚኒስቴር እየቀለደብን ነው። እንደ ሕጻን ልጅ እያታለለን ነው። ማባበያው ይቅርብን፤ ሕጻን ልጅ አይደለነም። በአስቸኳይ መፍትሔ ይስጠን” ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ጉዳያችንን ሊፈታው አልቻለም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ስለሆነም መንግሥት መፍትሔ ይስጥበት ነው ያሉት።
ይህ ካልሆነ የተለያዩ ሰልፎችን እንናካሂዳለን፤ ለሥራ ቅጥር ማፈላለጊያ የሚሆን የምስክር ወረቀት ሊሰጠን ይገባል ሲሉ ሚካኤሌ ተናግረዋል።
በጦርነቱ ምክንያት ተማሪዎቹ ከነበሩበት ዩኒቨርስቲ ያለ ውጤታቸውን ማምጣት ስላልተቻለ፣ ለጊዜው በዚህ ሥራ ያፈላልጉ የሚል ጽሑፍ በምስክር ወረቀታቸው ላይ እንዲጨመርላቸው ነው የጠየቁት።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሐረጓ ማሞ ጋር ብትደውልም ስልክ ለማንሳት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ ማካተት አልተቻለም።
በትግራይ ክልል ሲማሩ የነበሩ 10 ሺሕ 164 ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንት ትምህርታቸውን አቋርጠው ክልሉን ከለቀቁ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎቹን ወደ ተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በጊዜያዊነት መድቦ እንዲማሩ ማድረጉ ሲገልጽ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014


