የአፋር ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተዘዋዋሪ ችሎት የፍትሕ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

0
795

የአፋር ብሔራዊ ክልል ቂልበቲ ረሱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተዘዋዋሪ ችሎት የፍትሕ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የክልሉ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

መቀመጫው አብዓላ ከተማ የነበረው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕወሓት አካባቢውን መቆጣሩን ተከትሎ ወደ ሰመራ ከተማ እንዲዞር መወሰኑን እና በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አማካይነት ወረራ ከተፈጸመባቸው ኹለቱ ዞኖች አንዱ በሆነው ቂልበቲ ረሱን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የሚገመግም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት፣ እንዲሁም የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የተካተቱበት አብይ ኮሚቴ መቋቋሙ ነው የተገለጸው።

በዚህም መሠረት ከዞን ፖሊስ፣ ዐቃቤ ሕግ፣ ማረሚያ ቤትና ፍርድ ቤት እያንዳንዳቸው ሪፖርት እንዲያቀርቡ መደረግ መቻሉን በኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በኃላፊነት የሚሠሩና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሥራ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዞኑ ማዕከል የነበሩት ታራሚዎች በአውሲ ረሱ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ መደረጉንና፣ እነዚህም ታራሚዎች በዞኑ ከሚገኙት ወረዳዎች የመጡ፣ በጊዜ ቀጠሮ ላይ የነበሩ፣ ጉዳያቸውም በወረዳ ፍርድ ቤት ላይ ያለና የፍርድ ሒደታቸው የተቋረጠ እንደሚገኙበትም ገልጸዋል።

በወረዳው ፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ ሳለ በመስተጓጎሉ ምክንያት ሂደቱ የተቋረጠ በመሆኑ ፍትሕ እየተነፈግን ነው፣ ብሎም ፍርድ ቤት መቅረብ ስንችል አልቀረብንም የሚል ቅሬታ ታራሚዎች ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ ከሚመለከታቸው ከእያንዳንዱ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ጋር በመሆን የእያንዳንዱን ታራሚ ጉዳይ በማስታወስ ወደ ሥራ እንደተገባ ነው ያመላከቱት።

በሕወሓት ወረራ ምክንያት ታራሚዎች የክስ መዝገባቸው በነበሩበት የቀረ ሲሆን፣ ከማረሚያ ቤት አስተዳዳሪዎች ጋር በመሆን የግል ማኅደራቸውን በመጠየቅም መሟላት ያለባቸውን ዶሴዎች ለሟሟላት የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና በሥሩ የሚገኙት ዳኞች ታራሚዎችን በአካል በማየት የእያንዳንዳቸውን ጉዳይ ከነተጠረጠሩበት ምክንያት ማስረጃ ለማቅረብ መሞከሩም ተገልጿል።

በጥቅሉ 30 የሚደርሱ ክሳቸው በመስማት ሒደት ላይ ያሉና የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ሲጠባበቁ ለነበሩት ውሳኔ ተላልፏልም ነው የተባለው።
የጊዜ ቀጠሮ ያልነበራቸው ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ከማድረግ ጀምሮ፣ በክስ ሒደት ላይ ላሉት፣ እንዲሁም ዋስትና በማያስከለክሉ ወንጀሎች የተጠረጠሩት ላይ ደግሞ የዋስትና መብት እንዲያገኙ መደረጉ ተመላክቷል።

እንዲሁም የፍትሃ ብሔር ጉዳይ በተመለከተ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ አይከናወንም ተብሎ መታሰብ ስለሌለበት በሚል፣ የፍትሃ ብሔርም ሆነ የወንጀል ጉዳይ በኹኔታው ላይ በመመርኮዝ እንዲታይ ለማድረግ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተዘዋዋሪ ችሎት እየሠራ መሆኑ ነው የተገለጸው።

በዞኑ ሕወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ የክልሉ ቦታዎች ለሚገኙ ከ350 ሺሕ በላይ ዜጎቸም፣ በቀጣይ የተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ መታሰቡ ተመላክቷል።
በቂልበቲ ረሱ ዞን ካሉት ስምንት ወረዳዎች ስድስቱ እስካሁን ድረስ በአሸባሪነት በተፈረጀው ሕወሓት ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ እና ጦርነቱም እንደቀጠለ የሥራ ኃላፊው አመላክተዋል።

ሕወሓት በአፋርና በአማራ ክልል ለአምስት ወራት ከቆየ በኋላ፣ ዳግም አፋር ክልል ላይ ጦርነት ከፍቶ በወረራቸው አካባቢዎች የነበሩ የክልሉ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here