“የሰው ልጅ ሰላም ምንጩ ፈጣሪውን መፍራት መቻሉ ነው።”፦ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ

0
1487

ማክሰኞ ሚያዝያ 4 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የሰው ልጅ ሰላም ምንጩ ፈጣሪውን መፍራት መቻሉ ነው፤ ፈጣሪውን መፍራት የቻለ ሰው ደግሞ የራሱን ሰላምና መብት አክብሮ የሌሎችን ሰዎችንም መብትና ሰላም ያስከብራል። ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ተናገሩ።

እስካሁን የጠፋው ጥፋት ይብቃ ከአሁን በኋላ ፊትን ወደ ሰላም ማዞር ችግሮቻችንን በምክክርና በውይይት እንፍታ። ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲው አገርን ለማስቀጠል የአገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ አገርን ለማስቀጠል የአገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመው፤ ምክክሩ እኩልነት በሰፈነበት፣ በእውነትና በአንድነት መንገድ የሚከወን ከሆነ ለአገራችን አወንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

መመካከርና መወያየት የቆየ የኢትዮጵያውያን ትውፊት እንደሆነ ያወሱት ሃጂ ዑመር፤ በመመካከርና በመወያየት ችግራችንን ልንፈታ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲው አገራዊ ምክክሩ ወደታች ወርዶ ተፈፃሚ እንዲሆን እንዲሁም አገር ወደ ሰላማዊ ሁኔታዋ እንድትመለስ ከመንግሥትና ከኅብረተሰቡ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

ሕዝቡ ጥፋተኛን ለይቶ በማውጣትና የጥፋት መንገዶችን በመዝጋት የአገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። ኮሚሽኑም ከኢትዮጵያውያን ጋር በመማከር በጋራ ችግሮች የሚስተካከሉበትንና ወደ ሰላም የሚገቡበትን ዕድል መፍጠር እንደሚገባው ጠቁመዋል።

አገራዊ ምክክሩን ተግባራዊ ለማድረግ ጠበቅ ያለ መመሪያና ሕግ ሊኖር እንደሚገባ የጠቆሙት ሃጂ ዑመር፤ አገራዊ ምክክሩ በአገሪቱ የጠፋውን ሰላም ለመመለስና በዘላቂነት አብሮ ለመኖር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

እንደ ተቀዳሚ ሙፍቲው ገለፃ፤ ከዚህ ቀደም በጦርነትና በሌሎችም ምክንያቶች የጠፋው ጥፋት ጠፍቷል፣ በደረሰው ውድመት የወደመው ወድሟል፣ የተፈናቀለው ተፈናቅሏል፣ አሁን ግን የጠፋው ጥፋት ይበቃል በማለት እርስ በእርስ መቋሰልን ትቶ ፊትን ወደ ሰላም ማዞር ይገባል።

“እንደ ሃይማኖት አባትነቴ ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም መጋደልና መጫረስ እንዲበቃ እማጸናለሁ” ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲው፤ አገራዊ ችግሮችን በንግግር በውይይት መፍታት እንደሚያሻም ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንቱ አክለውም፤ “የሰው ልጅ ሰላም ምንጩ ፈጣሪውን መፍራት መቻሉ ነው፤ ፈጣሪውን መፍራት የቻለ ሰው ደግሞ የራሱን ሰላምና መብት አክብሮ የሌሎችን ሰዎችንም መብትና ሰላም ያስከብራል።” ብለዋል።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here