“አንበሳ ፋርማሲ እና ኒዮን አዲስ እንዲፈርሱ ተወሰነ ተብሎ የሚናፈሰው መረጃ ፍጹም ከእውነታው የራቀ ነው”፦ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን

0
1273

ሐሙስ ሚያዝያ 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) አንበሳ ፋርማሲ እና ኒዮን አዲስ እንዲፈርሱ ተወሰነ ተብሎ የሚናፈሰው መረጃ ፍጹም ከእውነታው የራቀና መሰረተ ቢስ መረጃ ነው ሲል የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ የቅርስ ቤቶቹ ይዘታቸው እና ቅርጻቸው ሳይቀየር፤ ባሉበት ሳይነኩ አካባቢው እንዲለማ ተደረገ እንጂ፤ እንዲፈርሱ አልተወሰነም ብሏል።

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በትላንትናው ዕለት የቅርስ ቤቶቹን መፍረስ አስመልክቶ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ሲናፈስ ስለነበረው መረጃ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በማብራሪያውም አንበሳ ፋርማሲ እና ኒዮን አዲስ የተባሉ ድርጅቶች በኪራይ ሲገለገሉበት የነበሩበት እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ንብረት የሆኑ ቤቶች፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቅርስነት ይዘታቸው ሳይቀየር፣ ባሉበት ምንም ዓይነት የቅርጽና የይዘት ለውጥ ሳይደርግባቸው በአካባቢው ከሚገነባው አዲስ ግንባታ ጋር ለአልሚው ባለሀብት እንዲተላለፉ መደረጉን ገልጿል።

በዚህም በቅርሶቹ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይደርስባቸው በኮርፖሬሽኑ እና በከተማ አስተዳደሩ መካከል ሥምምነት ላይ መደረሱንም አስታውቋል፡፡

በተለይ ከቅርብ ዓመታት በፊት ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው በርካታ ቤቶቹ እና የቅርስ ቤቶች በልማት ምክንያት በከተማ አስተዳደሩ መፍረሳቸውን ተከትሎ፤ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታትና የቤቶችን ደህንነት በጋራ በመጠበቅ እንዲሁም ከተማዋን በጋራ ለማልማት ኹለቱ አካለት ሥምምነት ላይ በመድረሳቸው፤ ከአሁን በፊት በተለየ ሁኔታ ልዩ ትኩረት ለቅርስ ቤቶች ደህንነት እንደተሰጠም ገልጿል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ያሉንን ቅርሶች በመጠበቅ እና በመንከባከብ፤ ቅርስ ጥበቃ እና ልማት ሚዛኑን አስጠብቆ እንዲሔድ ማድረግ ሌላኛው ከድህነት መውጫ መንገድ ሊሆን እንደሚገባ ገልጿል፡፡

ሆኖም በእርጅና ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን እና ቤቶችን ደግሞ ለኹላችን ጥቅምና እድገት በሚያስገኝ መልኩ ማልማትም ተጊቢ ነው ብሎ እንደሚያምንም አስታውቋል፡፡

በዚህም ልማት እና ቅርስ ጥበቃ ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲሔዱ ማድረግ ተጊቢ እንደሆነ ህብረተሰቡ በውል እንዲረዳ ያሳሰበው ኮርፖሬሽኑ፤ ከዚህ አውድ ውጭ ሌላ ትርጉም ሰጥተው ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ እና በድሬደዋ ከተማ የሚገኙ የፌደራል መንግስት ቤቶችንና ይዞታዎችን የሚያስተዳድር እንዲሁም በቤት ልማት ዘርፍ የተሰማራ የመንግስት የልማት ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here