ሐሙስ ሚያዝያ 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የቀድሞ ትዳር አጋሩን የቀኝ እጅ በገጀራ በመቁረጥ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ግለሰብ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቱን የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቴፒ ምድብ ችሎት አስታወቋል።
ግለሰቡ ጥፋተኛ የተባለው በኢፌዴሪ ወንጀል ህግ ቁጥር 27(1) እና 539(1) (ሀ) ስር የተደነገገውን ህግ በመተላለፉ መሆኑ በችሎቱ ተገልጿል።
መስፍን ማሞ የተባለው ግለሰብ፤ ወንጀሉን የፈፀመው በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ሠላም ቀበሌ ልዩ ሥሙ ዳውሮ ሠፈር በሚባል አካባቢ ነው ተብሏል።
ግለሰቡ ወንጀሉን የፈፀመው የቀድሞ ትዳር አጋሩ የነበረችውን ገነት ኃይሌን የካቲት 03 ቀን 2014 ዕለተ ሐሙስ በግምት ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ የቤቱን በር በኃይል በርግዶ በመግባት በያዘው ገጀራ የቀኝ እጇን ሙሉ በሙሉ ቆርጦ በመጣል መሆኑን ከአቃቤ ህግ ምስክሮች ቃልና ተቆርጦ በተጣለው እጇ ፎቶ ግራፍ ለማረጋገጥ መቻሉን በችሎቱ ተገልጿል።
በተጨማሪም እጇ ከተቆረጠ በኋላ ህይወቷን ለማትረፍ ስትል በጓሮ በር ሩጣ ለማምለጥ ስትሞክር፤ ተከታትሎ በያዘው ገጀራ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿን በመቆራረጥ ከፍተኛ የአካል ጉዳት እንዳደረሰባት ከአቃቤ ህግ ምስክሮች ቃልና የሰነድ ማስረጃ ማረጋገጥ ተችሏል።
ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ ከቀድሞ የትዳር አጋሩ ገነት ኃይሌ አንድ ወንድ ልጅ እንደወለደና በ2009 በፍርድ ቤት በህጋዊ መንገድ ፍቺ ከፈፀሙ በኋላ በቤንች ሸኮ ዞን ሸኮ ወረዳ ግዝመሬት ቀበሌ ላይ ትዳር መስርቶ ይኖር እንደነበረ ተረጋግጧል።
በዚህ መሠረት የሸካ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቴፒ ምድብ ችሎት በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት መስፍን ማሞ የተባለው ግለሰብ በፈፀመው ከባድ የሆነ ሰው የመግደል ሙከራ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ጉዳት የደረሰባት ግለሰብ በወቅቱ እንደተናገረችው ፍርዱ ምንም እንኳን የጎደለውን ሰውነቴን ባይመልስልኝም ፍትህ በማግኘቴ ተደስቻለሁ ያለች ሲሆን፤ እንደዚህ አይነት ጭካኔ የተሞላውን ድርጊት ህብረተሰቡ እንዲያወግዝ በመጠየቅ ትክክለኛ ፍትህ እንዲያገኝ ላደረጉት የፍትህ ተቋማት ምስጋናዬን አቀርባለሁ ስትልም ተናግራለች።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n





