አዲስ ማለዳ ባለፈው እትሟ የጃኖ ባንክ አደራጆች ቢሮ በመዝገታቸው ምክንያት ባለ አክሲዮኖች ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ዘግባ ነበር። የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ቢሮ ቢለቅም ሥራውን እየሠራ መሆኑን በአካል ተገኝቶ ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።
የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ጃኖ ባንክን ለማቋቋም ከአንድ ዓመት በፊት የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩ እና ሽያጩንም በሁሉም ባንኮች ውስጥ በተከፈተ ዝግ አካውንት ሲያካሂድ መቆየቱን አደራጅ ኮሚቴው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው አዲስ መመሪያ፣ አዲስ ባንክ ለማቋቋም የሚያስችለውን ዝቅተኛ የመመሥረቻ ካፒታል ቀድሞ ከነበረበት 500 ሚሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረጉ አዲስ በሚቋቋሙት ባንኮች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ኮሚቴው ጠቁሟል።
በመቋቋም ላይ የነበረው ጃኖ ባንክ በበኩሉ፣ የባንክ ምሥረታ ሒደቱን ከመግታት ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው አማራጭ መሠረት ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ለመቀየር 2/3ኛውን የባለአክሲዮኖች ድጋፍ አግኝቶ እና ስምምነታቸውን በፊርማቸው አረጋግጦ ለብሔራዊ ባንክ ፊርማውን አስገብቷል ተብሏል። ብሔራዊ ባንክም የባለአክሲዮኖችን በዝግ አካውንት የሚገኝ ካፒታል ወደ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋሙ አካውንት ለማዛወር በሒደት ላይ ይገኛል።
ጃኖ ባንክ በምሥረታ ላይ ሲገለገልበት የቆየውን ቦሌ መድኃኒዓለም ሞል የሚገኘውን ቢሮ የቀየረ በመሆኑ ይህንኑ መረጃ ባለመገንዘብ “አደራጆች ቢሮ ዘግተው ጠፉ” በሚል የተዘገበው ትክክል እንዳልሆነ አደራጅ ኮሚቴው ገልጿል። የባለ አክሲዮኖች ካፒታል በዝግ አካውንት የተቀመጠ በመሆኑ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ውጭ፣ ማንም እንደፈለገ ሊያንቀሳቅሰው የማይችል ስለሆነ፣ ማንኛውም ባለአክሲዮን ካፒታሌ ይመለስልኝ የሚል ጥያቄ ካለው በሕጋዊ መንገድ ማቅረብ የሚችል መሆኑን አደራጅ ኮሚቴው አስታውቋል። ባንኩ ወደ ማይክሮ ፋይናንስ እንዲቀየር የፈረሙ ባለአክሲዮኖች ውሳኔው በጠቅላላ ጉባኤ እንዲወሰን በመባሉ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤ የሚያሳውቅ መሆኑን አደራጅ ኮሚቴው ጠቁሟል። አዲስ አድራሻቸውን በቀጣይ እናሳውቃለን ሲሉም ተናግረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014


