የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጅንሲ የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች የደንብ ልብስ ይፋ ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ አሳወቀ።
የደንብ ልብሱ፣ የቁጥጥር ባለሙያዎቹ በግንዛቤ የተደገፈ ጥብቅ የትራፊክ ቁጥጥር በማድረግ በትራፊክ ግጭት አደጋ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ እና ለማስቀረት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ኤጅንሲው ለአዲስ ማለዳ ከላከው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ኤጀንሲው ይፋ ያደረገው የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች የደንብ ልብስ የቁጥጥር ስራውን የበለጠ ለማጠናከር የሚያግዝ ግብዓት እንደሆነ ተመላክቷል።
ባለፉት ኹለት ዓመታት በኮቪድ19 ወረርሽኝ ምክንያት በከተማዋ ጠጥቶ ማሽከርከርን ለመከላከል የሚደረገው ቁጥጥር ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ድርጅቱ ቁጥጥሩን ለመጀመር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ አሳውቋል።
ባለሙያዎቹ እስከ አሁን የደንብ ልብስ ስላልነበራቸው አንፀባራቂ ብቻ ለብሰው ሲሰሩ በመቆየታቸው፤ ከሌሎች ተቋማት ሰራተኞች ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ በተለይ አሽከርካሪዎች ሲያቀርቡት የነበረውን ቅሬታ ይፈታልም ነው የተባለው።፡
በተጨማሪም፣ የደንብ ልብሱ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ አንፀባራቂ በመልበስ አሽከርካሪን አስቁሞ ተሽከርካሪውን ይዞ እስከ መሰወር የደረሰ የዘረፋ እና የሌብነት ተግባርን ለመቅረፍ እንደሚረዳም ከተቋሙ በተላከው መረጃ ተጠቅሷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014


