የስቅለት በዓልና አከባበሩ

Views: 150

በክርስትና እምነት በድምቀት ከሚከበረው የትንሣኤ በዓል አስቀድሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ስርዓት መሠረት በአብያተ ክርስትያናት የሚደረጉ ስርዓቶችና ክዋኔዎች አሉ። ዘንድሮ ግን እንደወትሮ የሆነ አይመስልም። የሰዎች ስበስብ ለመባባሱ ምክንያት ለሆነው ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሲባል ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን በአብያተ ክርስትያናት ተሰብስቦ መከወን አልተቻለም። ሆኖም የቤተክርስትያኒቱ አባቶች ካህናትና ዲያቆናት አላስታጎሉም። ያንንም ተከትሎ ምዕመኑ ክዋኔዎቹን በትዕይንተ መስኮቶቹ በኩል እየተከታተለ የስርዓቱ ተካፋይ ሲሆን ታዝበናል።
ታድያ የትንሣኤ ዋዜማን ቀድሞ እለተ አርብ የስቅለት በዓል ይከበራል። ይህንንም በሚመለከት አዲስ ማለዳ ከመምህር ዲያቆን እሱባለው ደምሴ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች። በዓሉንና የአከባበር ስርዓቱን በሚመለከት ያገኘችውን መረጃም በተከታዩ መልክ አሰናድታዋለች።

በዓል ምንድን ነው?
በቤተክርስትያን በዓል የሚለው ቃል ከግዕዙ ‹አብዐለ› የወጣ ሲሆን ‹አከበረ፣ ከፍ ከፍ አደረገ› የሚል ትርጉም አለው። መንፈሳዊ ትርጉሙ ደግሞ ከዚህም ከፍ ያለ ነው። ይህን በዓል ስናከብር ከጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ፍጹም አንድነት ለመፍጠር እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል መሣሪያ ነው። ከፈጣሪ ጋር ያለንን ኅብረት የምናጠናክርበት ነው።

በዓል ሲባል የተከሰተን አንድ ኹነት ብቻ የምናስብበት የሚመስላቸው አሉ። ይህ ለመንፈሳዊ በዓል አይሆንም። ምድራዊ በዓልም ቢሆን ታሪካዊ ነገርን ማሰብ ብቻ ሳይሆን የተለየ አንድነትን መፍጠር ካልተቻለ ትርጉም ያጣል። ኦርቶዶክሳዊ በዓላት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር የተለየ ኅብረት እንድንፈጥር ያግዛሉ።
ወደ ስቅለት ስንመጣ ተመሳሳይ የሚያደርገው ያለፈውን የምናስብበት ብቻ ሳይሆን አሁን እንደሆነ አድርገን ክርስቶስ የዋለልንን ውለታና ያሳየንን ፍቅሩን የምናስብበት ነው። ታሪክነቱን ብቻ ግን አይደለም። አንዲህ ነው፤ በነገረ ሃይማኖት ወይም ቲዮሎጂ ትምህርት ጊዜ በኹለት ይከፈላል። አንደኛው እየቆጠርን ያለነው ዘመን ሲሆን አሁን በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 2012ኛው ላይ ያለነው። ይህ የሰውኛ አቆጣጠር ነው። በዚህ አቆጣጠር ከ2012 ላይ 33 ዓመትን ቀንሰን፣ ስቅለት ለዚህ ያህል ዓመት ነው ያከበርነው እንላለን።

አምላካዊ የጊዜ አቆጣጠር የሚባለው ሌላው ነው። ይህ ከፍጥረታት ዘመን ውጪ የሆነ ነው። ለእግዚአብሔር ትላንትና ወይም ነገ የሚባል የለም፣ አሁን ነው። እግዚአብሔር ከጊዜ ውጪ ስለሆነ ነው። እና በዚህ ጊዜ ስናስብ አሁን እንደተደረገ አድርገን ነው ቀኗን የምናስባት። በሕሊናችን ሄደን የተሰቀለበትን፣ የተቀበለውን መከራ፣ ግርፋትና ስቃይ፣ የሰውን ጭቃኔና የእግዚአብሔርን ፍቅር እናስባለን። ከዛች ቀን ጋር አንድ ስንሆን አሁን እየተደረገ እንዳለ እናስባለን።
እናም በዓል አስቦ ለመዋል ሳይሆን ከትላንት ጋር ራሳችን ለማዋሃደና በዛ ውስጥ ከሚገኘው መንፈሳዊ ትሩፋትና ዋጋ ተሳታፊ ለመሆን ነው።

የስቅለት አከባበር ስርዓት
የኦርቶዶክሳዊ በዓላት በሙሉ በዝግጅት ነው የሚከበሩት። አንደኛው ዝግጅት ጾም ነው። በጾም ወደ በዓሉ እንሄዳለን። ሁሉንም በዓላት ጾም ይቀድማቸዋል። ጾም ዝግጅት ነው። የክርስቶስ ስቅለትን፣ ሞትና ትንሣኤውንም የምናከብረው በዝግጅት ነው። በተለየ ሁኔታ የጾምና የጸሎት መርሃ ግብር አለ። እሱ እየተደረገ ቀን ከ6፡30 ጀምሮ እስከ 9 ሰዓት ድረስ ቅዳሴ አለ።

ምክንያቱም እንዳልኩት በዓሉ ያለፈውን የምናስብበት ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር በተለየ ለመገናኘት የምንዘጋጅበት ስለሆነ ነው። በበዓሉ መዳረሻ ሰሞነ ሕማማት አለ፤ ከሰኞ እስከ አርብ አምስቱ ቀናት። በእነዚህ ቀናት በተለየ ሁኔታ ምንባባት ይነበባሉ።

በብሉይ ኪዳን ስለክርስቶስና እርሱ ስለሚቀበላቸው መከራዎች ቀድሞ ተነግሯልና እነሱ እየተጠቀሱ ይነበባሉ። ለዚህም መጽሐፈ ስንክሳር ተብሎ የሚታወቅ መጽሐፍ አለ። ይህም ከብሉይና ከሐዲስ ኪዳናት፣ ከሊቃውንት የተውጣጣ ስብስብ ነው።

በዚህም ስለክርስቶስ ሞትና ሕማሙ፣ ትንሣኤው ይነገራል፣ በሰዓት የተከፋፈለ ሲሆን በዛ መሠረት ይቀርባል። እሱን ተከትሎ በዜማና በስግደትም ጭምር ይቀርባል። በሰባቱም የጸሎት ጊዜያት መጻሕፍትን በማንበብ፣ በመስገድ ከስቅለቱ፣ ከሕማሙና ከመከራው ጋር የሚገናኙ ምስጢር ያዘሉ በግጥም መልክ የተደረሱ ድርሰቶችን በዜማ ጭምር በማለት ይከበራሉ፣ በሰሞነ ሕማማት።

የስቅለት ቀን ደግሞ ከቤተመቅደስ ዝግጅት ይጀምራል። ካህናት በአምስቱ ቀናት ጥቁር ልብስ ነው የሚለብሱት። በሌላ ወቅት በቅዳሴ ጊዜ መልበስ የሚገባው ነጭ ነው፣ ሆኖም በሰሞነ ሕማማት ግን ሐዘናችንን ለማሳየትና ሕማሙን ለማሰብ ጥቁር ይለበሳል። ቀኑን የሚያሳስቡና የሚያስታውሱ ነገሮች ሁሉ ዝግጅት ይደረግላቸዋል። የቤተ መቅደስ መንበሩ ሁሉ ጥቁር ልብስ ይለብሳል። በቤተመቅደሱም እለተ አርብን የሚያስታወሱ ነገሮች ይኖራሉ።

እንደተለመደው እየተነበበ፣ እየተሰገደ፣ ጸሎት እየተደረገ የተቻላቸው ሕማሙንና ለሰው ልጅ ፍቅር ብሎ ያደረገውን እያሰቡ እንደ አቅማቸው በእንባ ጭምር፣ የክርስቶስን ሕማም እናስባለን። መጨረሻ ላይ በቤተክርስትያን ምንባባት ካለቁ በኋላ 11 ሰዓት ላይ ‹‹ንሴብኦ ለእግዚአብሔር፣ ስቡአ ዘተሰብአ› ይባላል፣ ይህም ‹‹እግዚአብሔርን እናመስግነው፣ ምስጉን ነው የተመሰገነ›› ማለት ነው።

ኦሪት ዘፀዓት ላይ እስራኤል ከግብጽ ባርነት ወጥተው ባህረ ኤርትራን ሲሻገሩ የሙሴ እህት ማርያም እንደዘመረችው ሁሉ፣ እኛም እውነተኛ ሙሴ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ፣ ግብጽ ከተባለው የዘለዓለም ባርነት ወደ ፍጹም ነጻነት ስለተሻገርን፣ ከዘለዓለማዊ ባርነት ወጥተናል የሚለውን በማሰብ ነው ያን የምንዘምረው። ከበሮ ይመታል፣ እልልታና ሽብሸባም ይሆናል።

ንባቡ ግን እስከ ቅዳሜ ይቀጥላል። የስቅለት እለት ስግደት ሲያበቃ ታድያ ምዕመኑ እየቀረበ ስግደት እንዲሰጠው ይጠይቃል። ቄሱም በወይራ ቅጠል እየጠበጠቡ ተጨማሪ ስግደት ይሰጣሉ።

በዋናነት ሲጠቃለል በዓሉ በንባብና በስግደት የሚከበር በዓል ነው። ንባባቱ ስለ ክርስቶስ ሕማም የሚያሳስቡ ናቸው። መስገዳችን ደግሞ ለእኛ ብሎ መውደቅ መነሳቱን፣ እርሱ ለእኛ ብሎ በሰውነት የደረሰበትን መከራ ለማሰብ ነው። መከራው ከሕሊና በላይ የሆነ ነውና።

ቅዳሜ – ‹ገብረ ሰላም›
ቅዳሜ ማለዳ ካህናት ከቤተ መቅደስ ተሰብስበው ከመጽሐፍ ቅዱስ ‹መኃልየ መኃልየ ዘሰሎሞን› ወይም ‹ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዲሁም መዝሙረ ዳዊት እየተደገመ፣ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ከስቅለቱ ጋር የተያያዘ ድርሰት እየተጸለየ ቅዳሜም ‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ› ‹በመስቀሉ ሰላምን አደረገ› እየተባለ፣ ዓለም ከእግዚአብሔር ተለይቶ የነበረ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ግን መታረቁ እየታሰበ ጸሎት ይደረጋል።

በዛም ቄጤማ ቀርቦ ከተባረከ በኋላ ቀሳውስቱ በቤተ መቅደሱ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ይሰጣሉ። ይህም የሰላም ምልክት ነው። ኖኅ መርከብ ውስጥ በነበረ ጊዜ የላካት ርግብ የሰላም ምልክት፣ የጥፋት ውሃ መጉደሉን፣ ምድርም ለሰው ልጅ ምቹ ሁኔታ ላይ መድረሷን ለማረጋገጥ ቅጠል ይዛ እንደመጣችው፣ ካህናቱ አሁን ኃጢአትና በደል፣ ጉስቁልና ሁሉ በክርስቶስ የማዳን ሥራ ከእኛ ርቆልናል፣ አሁን ሰላም ሆነ የሚለውን ለማብሰር ቄጠማ ይሰጣሉ፣ ያም ገብረ ሰላም ተብሎ ይጠራል።
ምሽት ከኹለት ሰዓት ጀምሮ ትንሣኤን ለማክበር ዝግጅት ይጀመራል። መንፈቀ ሌሊት ላይ ተጀምሮ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ቅዳሴ ያልቃል። ምንባባት ይነበባሉ፣ በዜማም ይባላሉ። በዓለ ስቅለት ጋር በተያያዘ ይህን ነው የሚመስለው።

የበዓሉ መከበር ትርጉም ምንድን ነው?
ትልቁ ሐሳብ እዚህ ጋር ነው ያለው። በዓል ማክበር አንድን ክስተት ማሰብ ብቻ አይደል። ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል ነው ይህን ያደረገው። ጌታችን የመጣበት ዋና ዓላማም ይህ ነው፣ ሰዎች ከእግዚአብሔር ርቀው ስለነበር ወደ ራሱ ያቀርበን ዘንድ ነው አምላክ ሰው የሆነው። እኛ እንድንቀርበው እራሱ ቀረበን፣ ሰው በመሆንና መከራን በመቀበል። በምድር ላይ በሠራቸው ሥራዎች ሁሉ እሱን እንድንመስል ነው። በሠራው ሥራዎችም አንደኛ ቤዛ እንዲሁም ምሳሌ ሊሆነን ነው።
ቤዛነት ማለት የሰውን ልጅ ለማዳነ ነው። በተጨማሪም ሆኖ በማሳየት ‹ሁኑ› ሲለን ነው። ጠላት ውደዱ ሲል እሱ ጠላቱን ወድዶ ነው።የሚያሳድዷችሁን መርቁ ሲል እሱም በመመረቅ ነው። ንድፈ ሐሳብ ብቻ አይደለም የሚያስተምረው።

በክርስትናም አንድ ሰው ክርስትያን ነኝ ሲል ክርስቶስን እከተላለሁ ማለቱ ነው። እናም እርሱ ያደረገውን ለማድረግ መጣር አለብን። እሱን አብነት አድርገን ለሰው ልጆች ፍቅርን ማሳየት አለብን። ይህ ፋሲካ የፍቅር በዓል ነው። ክርስቶስ ለሰው ልጆች ነው የሞተው። በእርሱ በደል ተገኝቶ አይደለም፣ ሐሰት ነገር ተገኝቶበት አይደለም። ከሳሾቹም በቂ ምክንያት አልነበራቸውም።

ይህን ያደረገው ለእኛ ነው። ይህን በዓል ስናከብር እሱን መውደዳችን የምናረጋግጠው እሱ እንደወደደን፣ ያለልዩነት፣ ሃይማኖትና ብሔር ወይም የፖለቲካ ልዩነት ሳናደርግ ስንዋደድ ነው።

አሁን ያለንበት የወረርሽኝ ጊዜ ሆነና ትኩረታችን ሁሉ በሽታው ሆነ እንጂ፣ አገራችን ቀድሞ የነበረችበትን ሁኔታ ስናስብ ሃይማኖተኛ በምትባል አገርና 90 በመቶ በላይ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ባለበት፣ አኗኗራችን ግን ከዛ የተቃረነ ነው።

ክርስትያኖች ክርስቶስ ያደረገውን እያሰብን መተሳሰብ ይኖርብናል። በዓሉን በእለት ተእለት ሕይወታችን በተግባር መግለጥ ይኖርብናል። ክርስቶስን መምሰል የሚቻለው ለሌላው በመኖር ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com