ማክሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ መግቢያ በር ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ሩሲያን ወግነው ዩክሬንን ለመውጋት ለመመዝገብ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው የሚል ምስል በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ በመሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያዊያኑ ሰልፍ ዛሬ ማለዳም የቀጠለ ሲሆን፤ በኤምባሲው በር ላይ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ተሰልፈው ወደ ውስጥ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ለመታዘብ ችላለች።
ጉዳዩን በሚመለከት አዲስ አበባ የሚገኘውን የሩሲያ ኤምባሲ የጠየቀው አል ዐይን አማርኛ፤ ሩሲያ ኢትዮጵያውያን ወዶ ዘማቾችን እየመለመለች ነው መባሉን የሩሲያ ኤምባሲ አስተባብሏል ሲል ዘግቧል።
የኤምባሲው ፕረስ አታቼ ማሪያ ቸርኑኪና “ሩሲያ ለዩክሬን ጦርነት ኢትዮጵያዊያንን ለመቅጠር ማስታወቂያ አላወጣችም፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው መረጃም ሀሰተኛ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቢሆንም ግን ኢትዮጵያውን ወደ ኢምባሲው መሄዳቸው እውነት መሆኑን የገለፁት የኤምባሲው ፕረስ አታቼ፤ ወደ ሩሲያ ኢምባሲ የሄዱት ለምልመላ ሳይሆን ለሩሲያ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት “በርካታ ኢትዮጵያዊያን በኢሜይል እና በአካል ከሩሲያ ጎን መሆናቸውን እያሳወቁን ነው ለዚህ እናመሰግናለን” ሲሉም ማሪያ ቸርኑኪና አክለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ይሄንን እያደረጉ ያለው ረጅም እና ታሪካዊ በሆነው የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ወዳጅነት ላይ ስለሚተማመኑ እንደሆነም ኤምባሲው ተገልጿል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ እና ዩክሬን ይፋዊ ጦርነት ከጀመሩ 54ኛ ቀኑን መያዙ ይታወቃል።
በጦርነቱም እስካሁን አምስት ሚሊየን ገደማ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት አገራት ሲሰደዱ በርካቶች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።
_____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n





