የዋጋ ግሽበቱ በመጋቢት ወርም መቀጠሉን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ

0
844

ማክሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በየወሩ በሚያወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ የመጋቢት ወር 2014 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ34 ነጥብ 7 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጿል፡፡

የምግብ ዋጋ ግሽበት የመጋቢት ወር 2014 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ43 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ከየካቲትወር 2014 ጋር ሲነጻጸር በ1 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷ፡፡

በያዝነውም ወር በአብዛኛው በእህሎች የዋጋ ጭማሪ የታየ ሲሆን፤ የአትክልት ዋጋም ላይ መጠነኛ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ሩዝ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ሽንቡራና ምሥር በአብዛኛው የዋጋ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን፤ በተጨማሪም ወተት፣ አይብና ዕንቁላል፣ ቅመማ ቅመም (በዋናነት ጨውና በርበሬ) ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ የምግብ ዘይትና ቅቤ ዋጋ በፍጥነት የጨመረ ሲሆን ቡናና ለስለሳ መጠጦች ተከታታይ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።

በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት የመጋቢት ወር 2014 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ23 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ካለፈው የካቲት ወር ጋር ሲነፃፀር 0 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ከምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ አነቃቂዎች (ጫት)፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጂ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መስሪያ እቃዎች (የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ኪዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማሰገጫዎች)፣ ነዳጅ፣ ህክምና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ በተከታታይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው ተብሏል፡፡

የመጋቢት ወር 2014 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው የካቲት ወር 2014 ጋር ሲነፃፀር በ4 ነጥብ 0 ከመቶ እና የምግብ የኢንደክሱ ክፍሎች በ4 ነጥብ 3 ከመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት የምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት በ3 ነጥብ 4 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here