ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ ቋት ማዕከል እየተገነባ ነው

0
643

የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመረጃ ቋት ማዕከል እየገነባ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተካሄደው የህልውና ዘመቻ ምክንያት በተለይ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሲማሩ የነበሩ ተማሪዎችና ሲያስተምሩ የነበሩ መምህራን፣ እንዲሁም ከዚህ በፊት ከዩኒቨርሲቲዎቹ የተመረቁ ተማሪዎች አሁን ላይ የትምህርትና የሥራ ማስረጃዎቻቸውን ማግኘት ባለመቻላቸው መቸገራቸውን ተከትሎ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል የተባለ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መረጃዎች ማግኘት የሚያስችልን የመረጃ ቋት መገንባት መጀመሩን የትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል።

መረጃቸው የጠፋ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች አሁን ላይ ትምህርታቸውን ለማሻሻል እንዲሁም የደረጃ እድገት ለማሠራት የትምህርትና የሥራ ልምድ ማስረጃዎቻቸውን ማግኘት ባለመቻላቸው ተቸግረው የነበረውን አሠራር የሚቀርፍ መሆኑ ተነግሯል።

ትምህርት ሚኒስቴር የተማሪዎችና የመምህራንን መረጃ ማግኘት የሚችልበት ስርዓት ባለመዘርጋቱ ተፈጥሮ የነበረን ቅሬታ ይፈታል የተባለው ግንባታ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ መረጃ የሚያዝበት እንደሆነ ተጠቁሟል።

ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መረጃ ቋቱ ያላቸውን የተማሪዎች፣ የመምህራን እና የምርምር ውጤቶች የያዙ መረጃዎቻቸውን ማስገባት ጀምረዋል የተባለ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ሲማሩ ለነበሩና አሁን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ለሚገኙ ተመራቂ ተማሪዎች የመመረቂያ የምስክረ ወረቀት እየተዘጋጀ እንደሆነም ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here