የዘንድሮ ዋጋ የጨመሩ ትምህርት ቤቶች በሚቀጥለው ዓመት መጨመር አይችሉም ተባለ

0
509

በ2014 የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሪ ያደረጉ የግል ትምህርት ቤቶች በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ የአዲስ አበባ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ተናገረ።
የ2015 የትምህርት ዘመንን የክፍያ ጭማሪ አስመልክቶ ከትምህርት ቤቶቹ ጋር ምክክር ያደረገው ባለሥልጣኑ እንዳሳወቀው፣ በ2014 ጭማሪ ያደረጉ ትምህርት ቤቶች በ2015 የትምህርት ዘመን ምንም ዓይነት ጭማሪ ማድረግ እንደማይችሉ ነው። በምክክር መድረኩ ላይ ውሳኔውን ያሳወቁት የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሕይወት ጉግሳ እንዳሉት፣ ላለፉት ኹለት እና ሦስት ዓመታት ጭማሪ ሳያደርጉ የቆዩ ትምህርት ቤቶች ግን በሚያቀርቡት ፕሮፖዛል እና ከወላጅ ጋር በሚያደርጉት መግባባት መሠረት ጭማሪ ማድረግ እንደሚችሉ ነው።
ከመደበኛ የአገልግሎት ክፍያ ውጭ በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ትምህርት ቤቶች ክፍያ መጠየቅ አይችሉም ያለው ባለሥልጣኑ፣ ከዚህ ቀደም ያለ አግባብ ጭማሪ ያደረጉ ትምህርት ቤቶች እርምት እንዲወስዱ መደረጉንም የባለሥልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ፍቅርተ አበራ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፎቻቸውን ጨምሮ ኹለት ሺሕ ገደማ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ የተባለ ሲሆን፣ እነዚህ ትምህርት ቤቶች 400 ሺሕ የሚጠጉ ተማሪዎችን በማስተናገድ ከአጠቃላይ የአዲስ አበባ የተማሪ ሽፋን 43 በመቶውን እንደሚይዙ በባለሥልጣኑ ተጠቅሷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here