አበበች ጎበና የሕፃናት ክብካቤና ልማት ማኅበር በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

0
1736

አዲስ ማለዳ የፋሲካን በዓል ምክንያት አድርጋ ‹እንኳን አደረሳችሁ! እንዴት ናችሁ?› ስትል ከጎበኘቻቸው መካከል ከተመሠረተ ከአርባ ዓመታት በላይ የሆነው አበበች ጎበና የሕፃናት እንክብካቤና ልማት ማኅበር አንዱ ነው። በደጓ እናት አበበች ጎበና (ነፍስ ኄር) የተመሠረተው ይህ ድርጅት፣ አሁንም የእርሳቸውን ሕልም እውን ለማድረግ ጉዞውን በተስፋ ቀጥሏል። ትኩረቱን ሕፃናትና ሴቶች ላይ በማድረግም በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።

አዲስ ማለዳም በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ በሚገኘው የማዕከሉ ዋና ግቢ አቅንታለች። በግቢው ውስጥ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ጀምሮ 35 የሚሆኑ ሕጻናት ይገኛሉ። በተለያዩ መርሀ ግብሮችም በአዲስ አበባና ቡራዩ 6 ሺሕ 160 የሚደርሱ ሕጻናት ባሉበት ሆነው ድጋፍ ይደረግላቸዋል።

ከማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ይትባረክ ተካልኝ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል። ይትባረክ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ አበበች ጎበና የሕጻናት ክብካቤና ልማት ማኅበር አሁን ያለበት ሁኔታ ከባለፉት ዓመታት የተለየ አይደለም፤ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ሆኖም ግን ችግሮች የሉበትም ማለት አይደለም አሉ። ድርጅቱ መሠረቱን ሕጻናት እና ሴቶች ላይ በማድረግ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከ300 ሺሕ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

‹‹ሕጻናትን ከመንከባከብና ከመርዳት ባሻገርም፣ የሴቶችን ችግር በቀረፍን ቁጥር የሕጻናትንም ችግር እንቀርፋለን ብለን በማሰብ ሴቶች ላይም የተለያዩ ሥራዎችን እንሠራለን።›› ነው ያሉት። በዚህም አረብ አገር ሄደው ጥቃት ደርሶባቸው የተመለሱ ሴቶች፣ ለዝሙት አዳሪዎች፣ ልጅ ታቅፈው መንገድ ላይ ለሚለምኑ እናቶች የተለያዩ ሥልጠናዎች እንደሚሰጣቸው አንስተዋል።

ምግብ ዝግጅትና መስተንግዶ፣ ልጅ አያያዝ፣ የቤት ውስጥ ሥራ አሰራር የመሳሰሉ እስከ ስድስት ወር የሚፈጁ ሥልጠናዎችን ከትራንስፖርት አበል ጋር በነጻ እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል። ከሥልጠና በኋላም ሥራ እንዲያገኙ የግንኙነት ሥራዎችን እንሠራለን ሲሉ አክለዋል።

ይህም ብቻ አይደለም፣ ሴቶች በመንደራቸው ተደራጅተው እንዲቆጥቡ፣ ዕድሉ ያላቸው በከተማ ግብርና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ባላቸው ነገርም ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ መሥራት እንዲችሉ የጤና ትምህርት ይሰጣቸዋል በማለት በግቢው የሚሠሩ ተግባራትን ጨምረው ጠቅሰዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ድርጅቱ የምግብ ዕጥረት ያለባቸውን ሕጻናት ወደ ማዕከሉ አምጥቶ ለስድስት ወር እንደሚመግብ ተጠቅሷል። ከስድስት ወር በፊት የተጎዳ ሰውነታቸው ሲስተካከል ደግሞ ሌሎችን በመቀበል ምገባ የሚያካሂድ ሲሆን፣ በጤናና ሌሎች ምክንያቶች ሰውነታቸው መመለስ ያልቻሉት በቀጣዩ ዙር የምገባ መርሃ ግብርም እንደሚቀጥሉ ነው የተገለጸው።

ድርጅቱ በተጨማሪም በጤና፣ በቤተሰብ ዕቅድና ክትትል፣ በትምህርት፣ በውሃና ንጽህና እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ መረዳት ተችሏል። ቤታቸው ሊወድቅ የተቃረበው ቤተሰቦችን ቤት የመጠገን ሥራ፣ ልጆች ትምህርታቸውን ትተው ውሃ ፍለጋ እንዳይዞሩም ለቤተሰቦቻቸው ውሃ የማስገባት ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል።

የድርጅቱ የገቢ ምንጭ
ድርጅቱ 80 በመቶ ገደማ የሚሆነውን ገቢውን የሚያገኘው ከዓለም ዐቀፍ ለጋሾች ነው። ከ15 በመቶ እስከ 20 በመቶ የሚሆን ገቢውን ደግሞ የሚያገኘው በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ነው።
በዓለም ዐቀፍና በኢትዮጵያ የተከሰቱ ጦርነቶች ድርጅቱ በሚንከባከባቸው ሕጻናት ሕይወት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተለ እንደሚገኝ እና ምናልባትም ተፅዕኖው እስከ አሁን ያልታየ ነው ሲሉ የሕዝብ ግንኙነትና የኮምዩኒኬሽን ኃላፊው ይትባረክ ይገልጻሉ።

ሆኖም የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በመሥራት የራስን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅትም እንጀራ በመጋገር እንደ ሸራተን አዲስ ሆቴል፣ ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል፣ ግዮንና ዋቢ ሸበሌ ሆቴሎች ባልትና ጭምር እንደሚያስረክቡ አንስተዋል።

በተጨማሪም፣ ለማኅበረሰቡ በክፍያ አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል እና ካፊቴሪያ እንዲሁም ሹራብ እንደሚያመርቱም አመላክተዋል። ሆኖም ድርጅቱ ከሚሠራቸው ሥራዎችና ከሚያስፈልገው ገንዘብ አንጻር የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ከዚህ በላይ ማደግ እንደሚገባቸው ነው የገለጹት።

የድርጅቱ የገንዝብ አቅም ማደግ ከቻለም ከ10 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት ለመድረስ ሐሳብ መኖሩን ብሎም አስተማማኝ አቅም ከተፈጠረ በመላ አገሪቱ መሥራት እንደሚቻል ተናግረዋል።
‹‹እንደ ኬንያ እና ጋና ያሉ አገራት ለእንደዚህ ዓይነት ድርጅቶች በጀት ይመድባሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ የተለመደ አይደለም። በቂ ነው ባይባልም በመንግሥት በኩል መጥቶ ከመጎብኘት ጀምሮ አንዳንድ ደጋፍ ይደረጋል።›› ሲሉም ነው ያለውን ሁኔታ የሚያስረዱት።

አበበች ጎበና የሕጻናት ክብካቤና ልማት ማኅበር ዳይሬክተር (Executive Director) እሸቱ አረዶ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ላለፉት 43 ዓመታት በተለይ በሴቶችና ሕጻናት ላይ ትኩረቱን በማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ እንደኖረ አውስተዋል። በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት በቂ በጀት አለመኖሩን በአጽንዖት ገልጸዋል።

የውጭ እርዳታ ከቆመ ድርጅቱ ቆመ ማለት ነውና፣ ይህ እንዳይሆን ደግሞ የገቢ ምንጭ የመፍጠር ሥራዎችን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚበጅ ጠቁመዋል። በዚህም ድርጅቱ መደበኛ አባል፣ የክብር አባልና የዕድሜ ልክ አባል ከሚባሉ አባላቶቹም ገቢ እንደሚሰበስብ ጠቅሰው፣ በቀጣይም ጀርመን አገር ቅርንጫፍ በመክፈት ገቢ ለማግኘት ለመሥራት እቅድ መኖሩን አመላክተዋል።
አባል መሆን በገንዘብ ከማገዝም በላይ እንደሆነና፣ ሰዎች አባል ሲሆኑ ግዴታ ገንዘብ ለማዋጣት ብቻ ሳይሆን በሙያና በጉልበት ለመርዳትም አባል መሆን እንደሚችሉ ተጠቅሷል።

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተከሰተው ችግር ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸውም፤ አሁን ላይ አራት ልጆች ወደ ማዕከሉ መጥተዋል ብለዋል።

‹‹ኹለቱ እግራቸው ክፉኛ የተጎዳ በመሆኑ ቤት ተከራይተንላቸው አለርት ሆስፒታል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ነው። ኹለቱ ደግሞ ወላጆቻቸውን በማጣታቸው ማዕከሉ ውስጥ ገብተው ከሌሎች ሕጻናት ጋር እንክብካቤ እየተደረገላቸው እየኖሩ ነው።›› ሲሉም ተናግረዋል።

‹‹ድርጅቱ በበቂ ሁኔታ ስር የሰደደና በቦርድ የሚመራ፣ አባላትና ልምድ ያላቸው ሠራተኞች አሉት። ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ካረፉ በኋላ ይዳከማል የሚል ስጋት በሰዎች ዘንድ መኖሩም አግባብ አይደለም። እርሳቸው መሠረቱን ገንብተው ነው ያለፉት፣ የእርሳቸው አለመኖር የሚያመጣው ጫና የለም።›› ብለዋል ዳይሬክተሩ። አያይዘውም ‹‹የክብርት ዶክተር አበበች ጎበና ኹሉንም ነገር ያደረጉት ለሕዝብ ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የእናታችን በጎ ዓላማቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እገዛ ያድርግ።›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በዓል አከባበር
በአበበች ጎበና የሕጻናት ክብካቤና ልማት ማኅበር በዓላት በደማቅ ሁኔታ ይከበራሉ። ልጆች ቤተሰባዊ ስሜት እንዲሰማቸው ምግብና መጠጥ በበቂ ሁኔታ ባለበት እንደሚከበር ነው ይትባረክ ያስረዱት።

በእንደዚህ ዓይነት ተቋማት መንፈሳዊ ተግባራትን መፈጸም የማይቻል ቢሆንም፣ አዳጊዎችን ስለበዓላትና ኃይማኖት ሳያስተምሩ ማሳደግ ትርፉ ኪሳራ በመሆኑም በዓላት በመጡ ቁጥር በደመቀ ሁኔታ አብረን እናከብራለን ነው ያሉት።

የዘንድሮውም የፋሲካ በዓልም በተመሳሳይ መልኩ በድምቀት ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅቶች መኖራቸወን ጠቅሰው፣ ቢቻል በውጭ ከምንረዳቸው ሴቶችና ሕጻናት ጋር በአንድነት ልናከብርም እንችላለን ነው ያሉት።

በማዕከሉ ያሉት ሕጻናት በየዓመቱ ያለው ቁጥራቸው ተቀራራቢ ሲሆን፣ ለዚህም ብዙ ጊዜ የአደራ ቤተሰብ ሲገኝ ወደዚያ ለመሄድ የሚወጡ በመኖራቸው ነው ተብሏል። አንዳንድ ጊዜ በሄዱበት ቤተሰብ ሳይመች ሲቀርና ችግር ሲፈጠር ወደ ማዕከሉ ተመልሰው የሚመጡ እንዳሉም ነው ያስረዱት።

ልጆች በማዕከሉ ከሚያድጉ ይልቅ የአደራ ጊዜ ቤተሰብ ውስጥ ቢያድጉ በብዙ ረገድ በእጅጉ የተሻለ ቢሆንም፣ ከማዕከሉ ተቀብሎ የሚያሳድግ የአደራ ጊዜ ቤተሰብ ማግኘት ቀላል አይደለም ተብሏል።

ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ሕጻናት ችግረኛ መሆናቸውን አጽፈው ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚመጡ ከሆነ እንደሚረከብ ነው ድርጅቱ ያስገነዘበው። አሁን ላይ በማዕከሉ ያሉት ሕጻናት 35 ይሁኑ እንጂ፣ የሚመጡ ካሉ እስከ 120 የሚደርሱ ሕጻናትን መንከባከብ የሚያስችል አቅም አለም ተብሏል።

ማዕከሉ በውስጡ ላሉ ሕጻናት ያለማቋረጥ ድጋፍ የሚያድርገው እስከ 18 ዓመታቸው ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ የሚቋቋሙበት ገንዘብ በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉ ይደረጋል ነው የተባለው። ወደ ዩንቨርሲቲ ለሚገቡትም ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉና እንዲመረቁ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተነግሯል።

ማኅበሩ ብዙ ልደርስላቸው የሚገቡ ሕጻናት፣ ሴቶችና ወጣቶች በመኖራቸው የኹሉም ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ያስፈልገኛልም ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ምልከታ አበበች ጎበና የሕፃናት ክብካቤ ልማት ማኅበር ግቢ ውስጥ የልጆች መመገቢያ እና መጫወቻ ክፍሎች አሉ። ከመኝታ ክፍሎች በተጨማሪም ከትምህርት ቤት ሲመለሱ የሚጫወቱት ክፍልና ማጥኛ ክፍል አላቸው። ግቢው ለሠራተኞች የሚሆኑ የተለያዩ ቢሮዎችን ያካተተ ሲሆን፣ የክብርት ዶክተር አበበች ጎበና በተለያዩ ጊዜያት የተቀበሏቸው የአገር ውስጥና የውጭ በርካታ ሽልማቶችም በማዕከሉ ቢሮ ይገኛሉ። ግቢውም እንዲሁ ዛፎች የሚበዙበት ነው።

የክብርት ዶክተር አበበች ጎበና በ1972 ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ኃይማኖታዊ በዓል (ግሸን) ለማክበር በሄዱበት ወቅት ኹለት የተቸገሩ ልጆችን ይዘው በመምጣት የበጎ አድራጎት ሥራቸውን በመጀመር፣ በዓመቱ 21 ገደማ ልጆች ተቀብለው በመንከባከብና በመርዳት ድርጅቱ ዛሬ እንዲደርስ መሠረት ጥለዋል።

በርካቶች የክብርት ዶክተር አበበች ጎበናን የአፍሪካ ማዘር ትሬዛ (Mother Teresa of Africa) ሲሉ ይገልጿቸዋል። በአንጻሩ አበበች ጎበና ከማዘር ትሬዛ አንጻር ትዳራቸውን ከማጣት ጀምሮ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ መሆናቸውንና ራሳቸውን ችለው የዓለም ተምሳሌት መሆን እንደሚችሉ በማንሳት፣ የአፍሪካ እናት (Mother of Africa) ሲሉ ይጠሯቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here