የበዓል ወቅት ጤናማ አመጋገብ

0
1372

በበዓላት ወቀት ከወትሮው የተለዩ የምግብና መጠጥ ዓይነቶችን መመገብ የተለመደ ቢሆንም፣ አንዳንዶች በበዓላት ወቀት በአመጋገብ ሳቢያ ጤናቸውን ያጣሉ። በበዓላት ወቅት አመጋገብ በተለያየ ሁኔታ ጤና የሚነሳ ወይም ላልተጠበቀ አደጋና ሕይወት ማለፍ ሊዳርግ እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በአብዛኛው የበዓላት ሰሞን አመጋገብ ብዙዎችን ለተለያዩ ችግሮች ሲጥል ይስተዋላል። ለዚህ ምክንያቶቹ ደግሞ ከመጠን በላይ መመገብ፣ ስጋና የእንስሳት ተዋጽዖን ማዘውተር እና ብዛት ያላቸው የአልኮል መጠጦች መውሰድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ታዲያ በዓልን በሰላም ለማክበር ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች የበዓላት ሰሞን አመጋገብ አንዱና ዋነኛው ሲሆን፣ ጤናማ የበዓል አመጋገብን በመከተል ጤናን መጠበቅ ያስፈልጋል።

አጿማትን ተከትለው በሚመጡ በዓላት አመጋገብን ማስተካከል እንደሚገባ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች ይመክራሉ። የትንሣኤ በዓል በመጣ ቁጥር አንዳንድ ሰዎች ቅባት የበዛበት ምግብ ተመግበው ለሕመም የሚጋለጡበት ሁኔታ ይከሰታል። የትንሣኤ በዓል ከረጅም ጊዜ ጾም በኋላ የሚመጣ በዓል በመሆኑ ቅባት የበዛበት ምግብ እና አልኮል መጠቀም ተገቢ አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የሥነ ምግብ ባለሙያዎች በበዓል ወቅት አመጋገቦች ጤናማ መሆን እንዳለባቸው ይመክራሉ። ባለሙያዎች እንደሚሉት የአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን የበዓል አመጋገብ ተመሳሳይ ነው። ጾም ሲፈታ የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ማለትም ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ቅቤ እና መሰል ምግቦችን መመገብ የተለመደ ነው። ይህ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ከቅባት ርቆ የቆየው ጨጓራ በአንድ ጊዜ ለመቀበል ይቸገርና ለሕመም ይዳርጋል ይላሉ። ለበዓል ቅባት የበዛበት ምግብ ማዘጋጀት የተለመደ ቢሆንም፣ መጥኖ መሥራት ተገቢ መሆኑን የሚመክሩት የዘርፉ ባለሙያዎች ጤናን ለመጠበቅ ሠውነትን ቀስ በቀስ አለማምዶ መመገብን ይመክራሉ።

የሥነ ምግብ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት በበዓል ወቅት ማኅበረሰቡ የሚመገባቸው የእንስሳት ተዋጽዖዎች በተፈጥሯቸው ከፍተኛ ቅባት አላቸው። በጾም ወቅት የሚዘወተሩ ምግቦች ቅባት ያልበዛባቸው በመሆናቸው ጨጓራ ለሥርዓተ ልመት ይጠቀምባቸው የነበሩ ንጥረ ነገሮች (ኢንዛይሞች) መጠናቸው እንደሚቀንስም ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በዚህም ጨጓራ ከለመደው ሥርዓት የወጣ አመጋገብ ማለትም ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ስንጀምር ሆድ መንፋት፣ ማቃጠል፣ ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና መሰል ሕመሞች ያስከትላል።

በበዓላት ወቅት ስጋና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን መመገብ የተለመደ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ከበዓል አመጋገብ ጋር በተያየዘ ከሚከሰቱ የተለመዱ ሕመሞች በተጨማሪ በተለይ ከስጋ አመጋገብ ጋር በተያየዘ በድንገት ለሞት የሚያጋልጡ አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። ከእነዚህም መካከል በስጋ ውስጥ የሚገኙ አጥንቶች ለድንገተኛ ሞትና አደጋ ሊዳርጉ ይችላሉ። የዘርፉ ባለሙያዎች ሰዎች ስጋ ሲመገቡ በጥንቃቄ እንዲመገቡ ይመክራሉ።

ስጋ በተፈጥሮው በቫይታሚን ኤ፣ ቢ እና ዲ የበለጸገ ሲሆን፣ በእነዚህ ቫይታሚኖች የበለጸገ መሆኑ ደግሞ ለዐይን መስተካከል፣ ለጥርስ ጥንካሬና ለአዕምሮ ጤንነት ትልቅ አስተጽዖ አለው። በዚህ ወቅት ቀይ ስጋና ጮማን አዘውትሮ መመገብ አይመከርም። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቀይ ስጋን አዘውትሮ መመገብ ለልብ ሕመምና ለስኳር ሕመም መንስኤ ሊሆን ይችላል።

እንቁላል በበዓል ወቅት በብዛት ለምግብነት የሚውል ምግብ ሲሆን፣ በከፍተኛ ፕሮቲን የበለጸገ መሆኑንና አነስተኛ የካሎሪን ይዘት በውስጡ መኖሩ ለሰዎች ጤንነት ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ከዚህ በተጨማሪም ሰውነትን “ኮሊን” የተባለ ንጥረ ነገር እንዲያመርት ያግዛል። እነዚህን ጥቅሞች ለማግኘት ደግሞ እንቁላልን ቀቅሎ መመገቡ ይመከራል።

በበዓል ወቅት ሰዎች አልኮልን በብዛት ይጠቀማሉ። ምክንያታቸው ደግሞ የምግብ መፍጨትን ያፈጥናል በሚልና በበዓል ወቅት እንደ መዝናኛ ስለሚቆጠር ነው። ነገር ግን፣ አልኮል አብዝቶ መውሰድ ጉበት በመጉዳት ቅድሚያውን ቦታ ይወስዳል። በበዓል ሰሞን ስጋን እና አልኮልን በአንድ ላይ መውሰድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም ጥናቶች ያሳያሉ።

የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል በበዓላት ወቅት ሰዎች ከአመጋገብ ጋር በተገናኘ የተለያየ የጤና እክል እንደሚገጥማቸው ይገልጻል። ማዕከሉ የበዓላት ወቅት ጤናማ አመጋገቦችን እንደ ምክር ያስቀምጣል። ማዕከሉ የበዓላት ወቅት ለጤናማ አመጋገብ ያግዛል ብሎ ካስቀመጣቸው መካከል የበዓል ቀን አመጋገብ እቅድን ማዘጋጀት ነው።

ሰዎች በበዓል ወቅት አመጋገባቸውን በእቅድ ካላስተካከሉና በዘፈቀደ የሚመገቡ ከሆነ የጤና እክል እንደሚገጥማቸው የሚገልጸው ማዕከሉ፣ ሰዎች በበዓል ወቅት የሚመገቡትን ምግብ መቆጣጠር ካልቻሉ እና ሌሎች ሰዎች አጓጊ ምግቦችን ሲመገቡ ተመልክተው ከተመገቡ ከእቅድ ውጭ የሆነ አመጋገብ መሆኑን ያብራራል።

አክሎም እንዲህ የሚል ምክር ይሰጣል፤ ‹‹የደም ስኳርዎ እንዲረጋጋ ለማድረግ በተለመዱት የመመገቢያ ሰዓቶች ይብሉ። ምግብዎ ከመደበኛው ዘግይቶ የሚቀርብ ከሆነ፣ በተለመደው የምግብ ሰዓትዎ ትንሽ መክሰስ ይብሉ እና ራት ሲቀርብ ትንሽ ትንሽ ይብሉ።››

ማዕከሉ የሚመክረው ኹለተኛው ጤናማ የበዓል አመጋገብ፣ በበዓላት ወቅት የሚቀርቡ ምግቦችን መምረጥ ሲሆን፣ ጣፋጭ የበዓል ምግቦች ሲቀርቡ ጤናማ ምርጫዎችን መለየት ይገባል ይላሉ። ሰዎች በጣም ከሚወዷቸው ምግቦች ውስጥ ትንሽ ምግብ ከያዙ በኋላ ምግብ ከሚቀመጥበት ጠረጴዛው መራቅን ይመክራል።

ሰዎች ከጤናማ የምግብ ምርጫቸው በኋላ በቀስታ ወይም በተረጋጋ ሁኔታ መመገብን የሚመክረው ማዕከሉ፣ ለዚህም ቢያንስ 20 ደቂቃዎችን መውሰድን ይመክራል። ከምግብ በኋላ አልኮል አለመጠቀም ወይም መመጠን እንደሚገባ የሚመክረው ማዕከሉ፣ አልኮል በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በመቀነስ ከስኳር በሽታ መድኃኒቶች ጋር መስተጋብር እንደሚፈጥር ይገልጻል።

እንዲሁም ሰዎች በበዓላት ወቅት ያለባቸውን የጤና ችግርና የሚወስዱትን መድኃኒት ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸውም ይመክራል። ምናልባትም የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች መድኃኒት ከወሰዱ፣ መጠኑን ማስተካከል ይጠበቅባቸው እንደሆነ ሐኪም ማማከር አለባቸው።

ሌላኛው ተስማሚ ምግቦችን አስቀድሞ መለየት እና ተስማሚ ያልሆኑ ምግቦችን አለማቅረብ ሲሆን፣ ሰዎች ቀድመው በትክክል የሚወስዷቸውን ምግቦች ከመረጡ ከእነዚያ ምግቦች ውስጥ ለጤና ተስማሚ አይደሉም ብለው እንዳይሰጉ እንደሚረዳ ማዕከሉ ይመክራል።

ከአመጋገብ በተጨማሪ ማዕከሉ የሚመከረው አካላዊ እንቅስቃሴን ሲሆን፣ ሰዎች ጣፋጭ ምግቦችን በበዓላት ወቅት ካዘወተሩ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ በበዓል ወቅት ከሚከሰት የጤና መታወክ ራሳቸውን መከላከል እንደሚችሉ ያብራራል። ይህም ከወትሮው በላይ መብላትን ለማካካስ እና ጭንቀትን ለመቀነስ ይረዳል። ከጓደኞች እና ቤተሰብ ጋር አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ በተለይ ከበዓል ምግብ በኋላ በእግር መሄድ ይመከራል።

በበዓላት ወቅት ሰዎች የእንቅልፍ ጊዜያቸውን የመቀነስ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል የሚገልጸው ማዕከሉ፣ እንቅልፍ ማጣት በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ያደርገዋል ይላል። ሰዎች እንቅልፍ ሲያጡ ብዙ መብላትን እንደሚመርጡ እና ከፍተኛ ቅባት ያለው እና ከፍተኛ የስኳር መጠን ያለው ምግብ እንደሚመገቡ ይገልጻል።

በመሆኑም፣ ሰዎች በበዓላት ወቅት መደበኛ የእንቅልፍ ጊዜያቸውን ማስቀጠልና ወቅቱ ምን እንደሆነ እያስታወሱ ማክበር እና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ተገናኝተው መዝናናት ላይ የበለጠ በማተኮር፣ በምግብ ላይ ያላቸው ትኩረት መቀነስ እንዳለባቸው ማዕከሉ ይመክራል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚመክሩት በ24 ሰዓታት ውስጥ ከሁሉም የምግብ ክፍሎች ማለትም ከጥራጥሬ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ከእንስሳት ተዋጽኦ የተሰባጠረ ጤናማ አመጋገብን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በባሕላዊ መንገድ የሚዘጋጁ እንደተልባና ሱፍ ምግቦችን ቀድሞ በመመገብ ከአፍ ጀምሮ እስከ ጨጓራ ያለውን የሥርዓተ ልመት አካሎች ወደ መደበኛው ሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ሌላኛው ተገቢ መፍትሔ ነው። የምግብ መጠንን በመቀነስና የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ ባለመጠቀም በበዓል ወቅት የሚከሰቱ ሕመሞችን ማስወገድ እንደሚቻልም ይመክራሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here