ማክሰኞ ሚያዚያ 18 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ኮምኒኬሽን ባለስልጣን ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሥራ ለመጀመር አስቀምጦለት የነበረውን ቀነ ገደብ ማራዘሙ ተገለፀ።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ ፍቃዱን የወሰደው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከመንግስት ጋር በገባው ውል መሠረት በዘጠኝ ወር ውስጥ ማለትም በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ አገልግሎት መስጠት መጀመር የነበረበት ቢሆንም በሥምምነቱ መሠረት አገልገሎት መስጠት አልጀመረም።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለካፒታል እንደተናገሩት፤ የአለም አቀፍ እና ወቅታዊ የአገሪቷ ሁኔታዎች ለመዘግየቱ እንደ ምክንያቶች ተወስደው የሳፋሪኮም ቀነ ገደብን እስከ ሀምሌ ወር ድረስ አራዝሞታል።
ሳፋሪኮም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የራሱን ኔትወርክ በመገንባት ማጠናቀቁን የገለፀ ቢሆንም፤ የካፒታል ምንጮች እንደገለፁት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የገባው ሥምምነት ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ወደ ሥራ ላይገባ እንደሚችል ገልፀዋል።
ዕረቡ ሚያዝያ 15 ቀን 20214 ኹለቱ ኩባንያዎች በመሰረተ ልማት መጋራት ላይ እና የደንበኞች ግንኙነቶች ላይ ሲያደርጉ የነበረው ድርድር ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልፀው እንደነበር የሚታወስ ነው።
ምንጮቹ ሥምምነት ሰነዶችን ማዘጋጀት ብዙ ሥራ እንደሚፈልግ ገልፀው፥ ኹለቱ አገልግሎት ሰጪዎች ምንም እንኳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥምምነቱን ቢፈራረሙም ወደ ትግበራ ለመግባት ግን ቢያንስ ከ3-4 ወር ሊወስድ ይችላል ብለዋል።
ለአስር ዓመት ይቆያል የተባለው ሥምምነት ቀደም ሲል በዋጋ እና በመክፈያ ምንዛሪ አለመስማማት ምክንያት አለመግባባት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን አሁን በተደረሰው ሥምምነት መሠረት ክፍያው በብር እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ይሆናል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ 2022 ማለቂያ በፊት ሥራ ለመጀመር ዝግጅቱን በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጿል። ለዚህም በመርህ ደረጃ የደረሰበት ሥምምነት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሶ ኹለቱም ኩባንያዎች በባለስልጣኑ ማዕቀፍ መሰረት እነዚህን ሥምምነቶች ለመጨረስ እየሰሩ መሆኑን መግለፁን ካፒታል ዘግቧል።
_
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




