“በጎንደር ከተማ በትላንትናው ዕለት፤ በተፈጠረው ግጭት እና በጠፋው የሰው ህይወት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን፣ ድርጊቱንም እናወግዛለን”፦ ኢዜማ
ዕረቡ ሚያዚያ 19 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጎንደር ከተማ በትላንትናው ዕለት፤ ሚያዝያ 18 ቀን 2014 በተፈጠረው ግጭት እና በጠፋው የሰው ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ፣ ድርጊቱንም እንደሚያወግዝ አስታወቀ።
በትናንትናው ዕለት በጎንደር ከተማ በሸይኽ ከማል ለጋስ ሥርዓተ ቀብር ላይ በተፈጠረው ችግር ምክንያት፤ በከተማዋ የሰው ህይወት መጥፋቱንና ጉዳት መደረሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም “አገር የኹላችን ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ከልካይ ምክንያት በኹሉም የአገሪቱ አካባቢዎች መብታቸው ተከብሮ ሊኖሩ ይገባል፡፡” ያለ ሲሆን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁንም ክቡሩ የሰው ህይወት እንደዘበት የሚቀጠፍባት አገር እንደሆነች ቀጥላለች ብሏል።
በተቀናጀ ሁኔታ የአገርን እና ህዝቧን ደህንነት ለማስጠበቅ መስራት አስቸኳይ እና አንገብጋቢ አጀንዳው እንዲሆን አሁንም መንግስትን እናሳስባለን ያለው ኢዜማ፤ መንግስት ጉዳዩን በፍጥነት አጣርቶ አጥፊዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ እንዲሁም ችግሩ እንዳይስፋፋ እና የበለጠ ጥፋት እንዳያመጣ እንዲቆጣጠር ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮ የመኖር እሴቱን ከሚሸረሽሩ ተግባራት እራሱን እንዲጠብቅ በመጠየቅም፤ የሀይማኖት መሪዎች እና የአገር ሽማግሌዎች ህዝብን የማረጋጋት ሥራ እንዲሰሩ ጥሪውን አቅርቧል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



