የኩፍኝ በሽታ በ79 በመቶ መጨመሩ ተገለጸ

0
716

የኩፍኝ በሽታ በ79 በመቶ መጨመሩን የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ። ድርጅቱ እንደገለጸው፣ የኩፍኝ በሽታ እንደ አዲስ ማገርሸቱን ገልጾ፣ የኮሮና ቫይረስ እና ግጭቶች ለበሽታው መስፋፋት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
በዚህም በዘንድሮው ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ ባሉት ኹለት ወራት ውስጥ ብቻ ከ19 ሺህ በላይ የኩፍኝ በሽታዎች ተከስተዋል ተብሏል። ይህም በኩፍኝ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ብዛት ከአምናው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ79 በመቶ መጨመሩን ነው ድርጅቱ ያስታወቀው።
በቀጣዩ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኩፍኝ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ብዛት 9 ሺህ 665 የነበረ ሲሆን፣ በተያዘው ዓመት ጥር እና የካቲት ወር ውስጥ 17 ሺህ 338 ሰዎች መጠቃታቸው ተገልጿል።
ሶማሊያ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ናይጀሪያ እና ኢትዮጵያ በኩፍኝ በሽታ የተጠቁ አገራት ሲሆኑ ግጭቶች ፣ የሰዎች መፈናቀል እና የጤና መሰረተ ልማት በጦርነት መውደማቸው ለበሽታው መከሰት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ 3 ሺህ 39 ሰዎች በኩፍኝ በሽታ የተጠቁ ሲሆን፣ 58 በመቶዎቹ ደግሞ የመጀመሪያ ዙር ክትባት ማግኘታቸው ተገልጿል።
በአብዛኛው ህጻናትን የሚያጠቃው የኩፍኝ በሽታ ተላላፊ በሽታ ሲሆን ተገቢው የሕክምና ክትትል ከተደረገ መዳን ይቻላል። ይሁንና በበሽታው ላለመጠቃት አስቀድሞ ክትባት መውሰድ ይመከራል።
የኩፍኝ በሽታ ተገቢውን የህክምና ክትትል ካላገኘ ከመግደል ጀምሮ ዘላቂ ለሆነ የአዕምሮ ጉዳት፣ ለሳንባ ምች፣ ያለጊዜው ጽንስ መውለድ፣ ለመስማት ችግር እና ለሌሎች ጉዳቶች የሚዳርግ በሽታ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
ከመጋቢት ወር ማብቂያ ጀምሮ በ43 የዓለም አገራት ያሉ 203 ሚሊዮን ህጻናትን የበሽታ መከላከያ ክትባቶችን የመስጠት እቅድ ቢኖርም እስካሁን ክትባቱ አለመጀመሩ ተገልጿል።
ክትባቱ ባለመሰጠቱ ምክንያትም 73 ሚሊዮን የዓለም ህጻናት የኩፍኝ ወረርሽኝ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስጠነቀቀው የዓለም ጤና ድርጅት፣ አገራት እና ዓለም አቀፍ የክትባት ኩባንያዎች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡም አሳስቧል።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here