የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጀኔቫ ባካሄደው ጉባኤ ለአፍሪካ ቀንድ ድርቅ መቋቋሚያ የሚውል 1 ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል መግባቱ ተሰምቷል።
በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ ከለጋሽ አካላት የተሰበሰበው ይህ ገንዘብ በድርቅ ለተጎዱት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ የሚውል ነው ብሏል።
በተለይም በሶማሊያ ስድስት ክልሎች ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ያሰታወቀው ጽህፈት ቤቱ፣ ዝናብ በወቅቱ የማይጥል ከሆነ እና የሰብዓዊ እርዳታ ሂደቱ ካልተጠናከረ በሀገሪቱ አሰከፊ ረሀብ ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቋል።
የአፍሪካ ቀንድ ለአራት ተከታታይ ጊዜ አነስተኛ የዝናብ መጠን እያገኘ መሆኑን እና በዚህም ምክንያት አንድ ሚሊዮን የቀጠናው ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን እንዲሁም ሶስት ሚለየን የሚሆኑ የቤት እንስሳት ውሃ እና ግጦሽ በማጣት መሞታቸውን ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቱ በመግለጫው አትቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀውም፣ በሶማሊያ ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በምግብ እጦት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በኬንያ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች እንዲሁም በኢትዮጵያ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች እንዲሁ ለምግብ እጥረት መዳረጋቸውን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014


