‹‹ሰው እያየ ከሚደረገው፣ ተደብቆ የሚደረገው መልካም ነገር ይበልጣል››

Views: 177

1441ኛው የረመዳን ጾም ተጀምሯል። በእስልምና ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣው አጽዋማት መካከል ቀዳሚው ነው። ታድያ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተንሰራፋበት በዚህ ጊዜ ጾሙን በተመለደ ስርዓት ማከናወን ከባድ ነው። ሕዝበ ሙስሊሙም ከወዲሁ ወደ መስጊድ ከመሄድ ታቅቦ በየቤቱ ሆኖ ጸሎቱንና ስግደቱን በማድረስ ላይ ነው። የአባቶቹን ምክር ሰምቶም ሰሞነ ጾሙን በተመሳሳይ ጥንቃቄ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
የቫይረሱ ስርጭት ሊበረታ ይችላል ተብሎ ከተሰጋባቸው ከተሞች መካከል ቀዳሚዋ አዲስ አበባም የሁሉን ጥንቃቄ በአደራ መልክ ስትጠይቅ ቆየታለች። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትም እነዚህን አደራዎች ወደ ምዕመኑ በማድረስ ጥንቃቄ እንዳይለየው ከማስተማርና ከማሳሰብ አልቦዘነም። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጾሙን እንዲሁም ከቫይረሱ ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ ያሉ ጉዳዮችን በማንሳት ከምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼሕ አሊ መሐመድ ሺፋ ጋር ተከታዩን ቆየታ አድርጋለች።

እንኳን አደረሰዎ
እንኳን አብሮ አደረሰን
የረመዳን ጾም በእስልምና ታላቅ የሚባል ጾም እንደሆነ ይታወቃል። የጾሙ ዓላማና በመጾምስ ይገኛል ተብሎ የሚታመነው ትሩፋት ምንድን ነው?
የረመዳን ትሩፋት ብዙ ነው። አላህ እንዲህ ብሏል፤ ‹አማኞች ሆይ! እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የረመዳን ጾም ግዴታ ተደርጓል። ከእናንተ በፊት በነበሩ ሰዎች ላይ ግዴታ እንደተደረገ ሁሉ፣ በእናንተም ላይ ግዴታ አድርገናል።›

ከእኛ በፊት የነበሩ እነማን ናቸው ስንል፣ እነ ሙሴ እንደሚባለው እነ ነብዩ ኢሳና ሌሎች ብዙ ነብያቶች አሉ። በእነርሱ ሁሉ ላይ ግዴታ ተደርጓል። አጿጿሙ ግን ይለያያል። የአንዳንዱ 62 ወር ነው፣ የአንዳንዱ ሃምሳ ቀን ነው፣ የአንዳንዱ አርባ ቀንም አለ። የእኛ 30 ቀን ወይም 29 ቀን ነው። ይህ ማለት የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ኡመቶች የታዘዙት 29 ወይም 30 ቀን ነው። ይህም በጨረቃ አቆጣጠር ነው።

ስለዚህ የረመዳን ትሩፋት ብዙ ነው። ድሆች የሚጠየቁበት፣ የድሆች ቤት የሚሞላበት ወር ነው። በተለይ ያላቸው ሰዎች እጅግ በጣም ብዙ ትርፍ የሚያተርፉበት ወር ነው። ትርፍ ስንል ከሞት በኋላ የሚገኝ ትርፍ ነው። እዚህም በዓለም ላይ የሰው ልጅ በሕይወት እያለ አላህ ጥሩ ነገር ይሰጠዋል፤ ጥሩ ነገር ያገኛል ማለት ነው።
ረመዳን ዛሬ (ሚያዝያ 15/2012) ማታ ጨረቃዋ ስትወለድ፣ የጀነት በሮች ይከፈታሉ። ጀነት ማለት ገነት ማለት ነው። 8 ገነቶች አሉ እነዛ ክፍት ናቸው። በአንጻሩ ገሃነም የሚባሉት ሰባቱ ማታ ይዘጋሉ። ይህ ትሩፋት በረመዳን ምክንያት ነው። ከዛም አልፎ አባታችንን እናታችንን፣ አዳምን እና ሔዋንን ያሳሳተው ዲያቢሎስ ማታ ጨረቃው ሲወለድ ይታሰራል። ወሩም የሚታሰርበት ወር ነው። እሱ ታሰረ ማለት ደግሞ አጠቃላይ የእርሱ ቡድኖችና አጫፋሪዎች አብረው ወደ እስር ቤት ይገባሉ። ታስረውም የሚገቡበት እስር ቤታቸው ባህር ውስጥ ነው ይላል። ይህም ረመዳን እስከሚያልቅ ድረስ ነው።

ለዚህም ነው፣ አይደለም በእስልምና እምነት ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ሌላውም እምነት ተከታይ በዚህ ወር ጥሩ መንፈስ ነው የሚታይበት።ይህ ማለት ሰይጣናት ሲታሰሩ ሁሉም ባለበት ስርዓቱን ይዞ ይጓዛል። ብዙ የሚፈታተነው ነገር የለም።

ረመዳን ላይ ተፈታታኝ የሚሆነው ነፍስያ ናት። ነፍስያ ማለት የሰውን ልጅ የምታሳስት፣ የምታሰርቀው፣ ዝሙት የምታሠራው፣ መጠጥ የምታስጠጣው፣ ሌላም ለስሜቱ የምትገፋፋ ናት። እርሷ ግን አትታሰርም። እርሷ ልትታሰር የምትችለው ፈጣሪን በመፍራት ብቻ ነው።

እና አስቀድሞም እንዳልኩት የረመዳን ትሩፋት እጅግ በጣም ብዙ ነው። ሌላም ነብያችን የመጀመሪያዋ የረመዳን ጾም ዐስሩ ቀናት፣ አላህ ለፈጠራቸው ፍጡራን የሚያዝንበት ቀናት ናቸው። በልዩ ሁኔታ ያዝንላቸዋል። ከዛም በመቀጠል መካከለኛዋ ዐስሯ ጌታ የሚምርበት ነው። የመጨረሻዋ ዐስር ቀናት ደግሞ ከእሳት ነጻ የሚያወጣበት ነው። እናም በዚህ ወር ያለው ትሩፋት የጎላና ሰፊ ነው የሚባለው ለዚህም ነው። እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅም አይደል።

ዘንድሮ የዓለም ስጋት የሆነ ኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብዙ ክዋኔዎችን አስታጉሏል። በረመዳን የጾም ወር ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ያሳድራል?
ዘንድሮ ለየት የሚያደርገው እንደተባለው በአገራችን የተከሰተው ኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ነው። ኅብረተሰቡን ወደ መስጊድ እንዳይገባ ከመስጊድ አስወጥቶታል። የሙስሊሙ ባህልና የነበረው ልማድ በጣም ከባድ ነበር። በተለይ በረመዳን ላይ ብዙ ነገሮች በመስጊድ ውስጥ ይሠራሉ። ሰዎች ተሰባስበው ጸሎት ያደርጋሉ፣ እስከ ምሽቱ ሦስት ተኩል እንዲሁም አራት ሰዓት ድረስ በመስጊድ ተሰባስበው አብረው ሥራም ይሠሩ ነበር።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ግን የጀምአ ሶላት ቀርቷል። ስለዚህ በቤታቸው እየሰገዱ ነው። ስለዚህ አሁን ከእስከዛሬው ለየት የሚያደርገው፣ ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ አቅመ ደካሞችና የሚረዳቸው እንዲሁም የሚንከባከባቸው የሌላቸው ሰዎች፣ እንዲሁ በሜዳ ላይ ቀርተዋል። አሁን ያለው ሰው ከሀብቱ ለእነዚህ ወገኖች መድረስ መቻል አለበት። እጥፍ ትርፍም ነው የሚያገኘው። እስከ ዛሬ ከሚያገኘው የበለጠ ትርፍ ያገኛል።

ይህ ማለት አንድ ሰው ጌታ ግዴታ ያላደረገበትን ትርፍ ሥራ ሲሠራ፣ ግዴታውን እንደተወጣ ያህል ነው የሚቆጠርለት። አንድ ሰደቃ ቢሰጥ ዘካ እንደሰጠ ይቆጠርለታል። ዘካ ከእስልምና ውስጥ አንደኛው ማዕዘን ነው። ትርፍ ሰደቃ ለአንድ ወገን፣ ለአንድ እናት ወይም ወንድም ቢሰጥ፣ ዘካ እንዳወጣ ይቆጠርለታል፤ በዚህ በረመዳን ምክንያት ማለት ነው። የረመዳን ትሩፋቱ ብዙ ነው።

ስለዚህ ማኅበረሰባችን፣ የከተማችን ሕዝበ ሙስሊም ለእነዚህ ወገኖች እጁን መዘርጋት አስፈላጊው ነገር ነው።

በወረርሽኙ ምክንያት የአካል ንክኪ አይኖርም፣ ርቀትም መጠበቅ ይኖርበታል። ታድያ በምን መልክ ይህን የተለመደውን እርስ በእርስ መደጋገፍ አሁንም አጠናክሮ ማስቀጠል ይቻላል?
ይህ የሚደረገው ለምሳሌ አንድ ሰው በቤቱ እርድ ሊያከናውን ይችላል። እርድ በሚፈጽምበት ጊዜ ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገዋል። ከዛ ውጪ አርዶ፣ ምግቡን ሠርቶ፣ እስከዛሬ በነበረው ባህል የተሠራውን ምግብ በአንድ ላይ መብላት መጠጣት ነበር። ያንን አሁን ተከልክለናል። ይህን የከለከለው መንግሥት አይደለም፣ ፈጣሪ ጌታችን ነው።

ስለዚህ በሚገባው መልኩና በጥንቃቄ ሠርቶ ሲፈለግ በፌስታል፤ ወይም መጠቅለያ አድርጎ መስጠት ይችላል። ጥሬ ብር ከሆነ አያስቸግርም። በተለይ ለድሆች ጥሬ ብር ቢሰጥ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል። ስለዚህ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ፣ የጤና ባለሞያዎች የሚሰጡትን ትምህርት ተከትሎና ያንን በመተግበር ማካሄድ ይችላል፤ የሚያስቸግር ነገር የለም።

ለምሳሌም ዱቄት ሊሰጥ ይችላል። እስከ አሁንም የከተማችን ሕዝበ ሙስሊም እንዲሁም ክርስትያንም ሁሉም እየረዳ ነው። ያንን ሲያደርግ ግን ምንም የሚያስፈራ ነገር የለውም። ችግሩና በሽታው የሚተላለፍበት መንገድ በመሰባሰብ እና በንክኪ ነው። ርቀትን ጠብቆና ንክኪን አስወግዶ ድጋፉን መስጠት ይችላል። ልብ ከቀና ምንም የሚያስቸግር ነገር የለም።

በሃይማኖት ውስጥ ፍጹም እምነት ትልቅ ዋጋ አለው። ሰዎችም አሁን ላይ ቫይረሱን ለመከላከል ጥንቃቄ አድርጉ፣ ወደ ቤተ አምልኮ አትምጡ ወይም አትሂዱ ሲባል፣ ምዕመናንና ምዕመናቱ እምነት እንደማጣት ይቆጥሩታል። ይህ እንዴት ይታያል?
እምነት ሲባል የእምነትን ባለቤት ሊጎዳ አይደለም የመጣው፣ ሊጠቅም ነው። እምነቶች በባህሪያቸው ጎጂ አይደሉም፣ ጠቃሚዎች ናቸው።
ወረርሽ ሁልጊዜ ይከሰታል። አንድ ጊዜ ሶርያ ላይ ተከስቶ ነበር። ይህም ብዙ ሰው ያለቀበት ነበር። በተለይም የነብዩ ተከታዮች 30 ሺሕ በጣም ታዋቂ ታዋቂ የሆኑትም አልቀዋል። በዚህ ምክንያት ሲያልቁ የነበሩት መሪ ከመዲና የሄዱት አብደላ ሙጀራ ይባሉ ነበር። አብደላ ሙጀራ ይህን በሽታ መቋቋም አልቻሉም። ስላልቻሉም በሽታው በጣም ብዙ ሰው ፈጅቶባቸዋል፣ ጨርሶባቸዋል። እርሳቸውም በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ሞቱ።

እርሳቸው ሲሞቱ ሞአዝ ሙጀበል የሚባሉ ተተኩ። እርሳቸውም በዛው ወረርሽኝ ምክንያት ሞቱ፣ መሪ ናቸው። ሦስተኛ የተተካው መሪ አምል ሙልአስ የሚባሉ መሪ ናቸው። እርሳቸው ሲተኩ ግን ያደረጉት፣ ሁኔታውንና ማኅበረሰቡን ተመለከቱ። ማኅበረሰቡ በአንድ ላይ ነው የሚሰግደው፣ በአንድ ላይ ነው የሚሄደው፣ ርቀቱን አይጠብቅም፣ ይነካካል። ብዙ ነገሮችን ሲመለከቱ ከቆዩ በኋላ ውሳኔ አስተላለፉ።

በዛም ‹ይህ በሽታ እሳት ነው፤ ማገዶው ማን ነው?› አሉ። እሳት በባህሪው ደግሞ ጨርቅም ይሁን እንጨት ወይም ላስቲክ፣ ያገኘውን ነገር የመብላት እድል ስላለው ይህን እሳት በምንድን ነው ማጥፋት የምችለው ብለው አሰቡት። እሳት ሊጠፋ የሚችለው በውሃ ነው። ስለዚህ እርሳቸው የወሰዱት አማራጭ፣ ማገዶው የሰው ልጅ ነው ብለው በመነሳትና እሳቱ ወረርሽኙ ነው በማለት፣ የሰው ልጆች መቀራረብ የለባቸውም፣ መገናኘት የለባቸውም፣ በአንድ ላይ መሄድ የለባቸውም፣ መራራቅ አለባቸው የሚል ውሳኔ ወሰኑ።

ከዛም ሰዎችን ሰብስበው ተናገሩ። በንግግራቸውን ከዛን ቀን በኋላ ሁሉም ሰው ተራራ ላይ ርቀቱን ጠብቆ እንዲቀመጥ አዘዙ። ቤት ውስጥ አይደለም፣ ተራራ ላይ ነው ያሉት። ተራራ ላይ መውጣት ብዙ ነገር አለው። አየር ያገኛሉ፣ እርስ በእርስ አያገናኝም። ስለዚህ ሁሉም ሰው በተራራው ላይ እንዲቀመጥ አዘዙ።

ከዛም በኋላ ታድያ ወዲያውኑ በሽታውን ተቆጣጠሩት። በዚህ ጊዜ መስጊድ ተዘግቶ ነበር። ማንም የገባ ሰው አልነበረም። ያኔ የነበሩት አጠቃላይ የመካና የመዲና መሪ፣ አሕመድ ሙሐጥአብ የነብዩ ባልደረባ የሆኑት፣ የነብዩ ኹለተኛ ምትካቸው፣ ይህን ሲሰሙ በጣም ደስ ተሰኙ፣ ተደሰቱ። ስለዚህ ከመስጊድ አለመምጣትና በመስጊድ አለመሰባሰብ በሃይማኖቱ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ የለም።

እንደውም አንዳንዴ ሰው እያየ ከሚደረገው ነገር ተደብቆ የሚደረገው ይበልጣል። መስጊድ ስገባ ሰው አይቶ ‹ሼሕ አሊ ጥሩ ሰው ነው› እንዲለኝ አይደለም የምፈልገው። ፈጣሪ ጥሩ ነው ሲለኝ ነው። ስለዚህ በቤት ውስጥ የሚደረገው ጌታን ማምለክ በጣም በላጭና ተወዳጅ፣ ጥሩም ናቸው። ስለዚህ ማኅበረሰቡ በቤቱ ውስጥ ጠንካራ ሆኖ እምነቱን ማካሄድ፣ ሶላቱን መስገድ፣ ጌታን ማውሳትና ማንሳት ይችላል ማለት ነው። ምንም የሚያመጣው ተጽእኖ ወይም የሚያስፈራ ነገር፣ ከነበረውም የሚጎድልበት የለም።

ይህ ግንዛቤ ግን ምን ያህል ወደ ምዕመኑ ደርሷል?
ለማኅበረሰቡ እያስተማርን ነው። ማታ ማታም ትምህርት አለ። በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያም ላይ ትምህርት እየተሰጠ ነው። አሁንም በዛ እንቀጥላለን፣ እናስተምራለን። የመስጊድ ኢማሞች አሉ፣ ይህ የሚመለከታቸው አካላትም አሉ። በእነርሱ አማካኝነት ትምህርቱ እየተሰጠ ነው። ያም ብቻ አይደለም፣ ሰው ቅን ልቦና ካለው በስልክ ሊማር ይችላል። የከበደውን ነገር መጠየቅ ይችላል፣ ማንም አይከለክለውም።

የእምነት አባቶች በየቦታው አሉ። ስልክ አትደዋወሉ፣ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን አትጠቀሙ አልተባለም። ስለዚህ የከበደው ነገር ካለ ምን ላድርግ ብሎ መጠየቅ ይችላል። ያ የጠየቀ አካል ምንአልባት አልመልስለት ካለ፣ እርሱ ደግሞ ከእርሱ ወደተሻለ ሰው ይደውልና ይጠይቃል። ይህን ያህል አስገዳጅ የሆነ ነገር ግን የለም።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። በተለይ የሃይማኖት ተቋማትና ቤተ እምነቶች በፖሊስ ሳይቀር ዙሪያቸውን ይጠበቃሉ። በአንጻሩ በንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ግን ቸልታ አለ። ይህን ታዝባችሁ ከሆነ ምን ዓይነት አስተያየት አላችሁ?
መስጊዶች ላይ ጠንካራ ሥራ ሠርተናል። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጣም ጥሩ የሚያስብል ነገር ነው የሠራው። ሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ከመዝጋታቸው በፊት ነው ሁሉን ነገር ተግብሮ የሠራው። ያም ማኅበረሰቡን ለመጠበቅ ነው። አሁንም ቢሆን ምንአልባት መስጊድ በር ላይ ከውጪ የሚሰግዱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለእነርሱም የሚከለክል ሰው አቁመናል፣ አብረው እንዳይሰግዱ። ሁሉም በየቤቱ እንዲሰግድም ሥራ ሠርተናል።

እያየነው ያለነውና እኔም እየታዘብኩት ያለሁት ሱቆችና ንግድ ቤቶች አካባቢ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች ሰዉ እንደነበረ ነው፣ አንዳንድ አካባቢ ላይ ግንዛቤ የሌላቸው አሉ። እሱን የጤና ባለሞያዎች በሚሰጡት አቅጣጫ ማቆም ወይም መግታት አስፈላጊ ነገር ነው። አሁን መኪናዎች በታርጋ ተለይተው ሥራ እየተሠራ ነው፣ ተግባር ላይም ውሏል። አሁንም ቢሆን ይህን በተመለከተ ሥራ መሠራት ያለበት የንግዱ ማኅበረሰብ ርቀቱን እንዲጠብቅ በማስታወስ ነው።

አትግዛ፣ አትሽጥ አልተባለም። አዋጁ ያንን አላካተተም። እንደዛ ከሆነ ደግሞ ርቀቱን መጠበቅ መቻል አለበት፣ ሲገበያይ። አንዳንድ አካባቢ ላይ ጥሩ ተሞክሮዎችን መታዘብ ችያለሁ። በቅርቡ መድኃኒት ፈልጌ ወደ አንድ መድኃኒት ቤት ስገባ፣ ‹አባ ተራዎትን ይጠብቁ› አለችኝ። እኔ ቀጥታ ነበር የገባሁት። ይህም ሰው በተራ እየገባ የሚፈልገውን ገዝቶ ይመለሳል ማለት ነው። ያ የሚበረታታ ነው። አሁንም የንግዱ ማኅበረሰብ ላይ መደረግ ያለበት ርቀት ጠብቀው መሥራት አለባቸው የሚለውን ማስታወስ ነው።

ከዚህ ወረርሽኝ መከሰት በፊት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሰላም ማጣት ውስጥ ነበረች። የነበሩ የብሔር ግጭቶችም የሃይማኖት መልክ ወደመያዝ እየተሻገሩ ነበር። አሁን ደግሞ የተለያዩ ሃይማኖት አባቶችና ተቋማት አብረን ወደ ፈጣሪ እንጩኽ በማለት በጥምረት እየሠሩና እየተባበሩ ይታያሉ። ይህ እንዴት ያዩታል? ከወረርሽኙ መጥፋት በኋላ እንዲቀጥልስ ምን መደረግ አለበት?
ወረርሽኙንስ ያመጣው ማን ነው? ወረርሽኙ የመጣውኮ በሰው ልጆች ኃጢአት ነው፤ በእንስሳት አይደለም። በከብት፣ በበግ፣ በፍየል ኃጢአት አይደለም ይህ ወረርሽኝ የተከሰተው። ወረርሽኝኮ ብዙ ጊዜ ተከስቷል፣ ግን እንዲህ ዓለምን ያዳረሰ ወረርሽኝ በታሪክ እንዲህ ያለፈ የለም። ይህንን ያየን ሰዎች መለያየት እንደማይጠቅም፣ መነታረክ እንደማይጠቅም ተረድተናል። የትም እንደማንደርስም ተረድተናል። የሃይማኖት አባቶች አሁን ብቻ ሳይሆን ከአሁንም በፊት ነው። ኢትዮጵያንም ለየት የሚያደርጋት አንዱ ይህ ነው።

አብሮ የመረዳዳትና የመተዳበር፣ የመተጋገዝ፣ አንዱ ሌላውን የመደገፍ ባህላችን የበረታና የጎላ፣ የቆየም ነው።

ይህ ወረርሽ ብሔር አይመርጥም። ጥቁር ነው ቀይ፣ ረጅም ነው አጭር፣ ወንድ ነው ሴት ብሎ የሚለየው ነገር የለም። ሁሉንም አዳራሽ ነው። ሃይማኖትም አይለይም። ለምሳሌ ሙስሊሙ አይነካም ክርስትያኑ ይነካል ወይም በአንጻሩ ሙስሊሙነ ይነካ ክርስትያኑን አይነካም ተብሎ የታወጀ አዋጅ ከፈጣሪ የለም። ለሁሉም ነው የመጣው። ይህን ያየ ሰው እንዴት ነው ወደ ቀደመ ተግባሩ የሚመለሰው፣ እብደት ነው እንጂ።

የሚያጋጩትና የሚያጣሉት እነማን እንደሆኑ ይታቀዋሉ። ጥቅምና ሥልጣን ፈላጊዎች፣ ይህቺን አገር ብትንትን ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። እንደነ ሶርያ እና ሊብያ እንድትሆን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። ይህቺ አገር ደግሞ የጸሎት አገር ናት። ያስቡታል እንጂ ማንም አይነካትም። በነገራችን ላይ አገር ትፈርሳለች ሲባልኮ ምድሩ አይጠፋም፣ የምንጠፋው እኛ የሰው ልጆች ነን።

ስለዚህ ይህን አብሮነታችንን፣ አብሮ መሥራቱን፣ መተባበሩን መቀጠል ያስፈልጋል። እንጂ ከዚህም ሌላ የከፋ ሊገጥመን ይችላል። በትብብር ግን ማሸነፍ እንችላለን። ይህ ነገር ባይመጣኮ ግብጽ ደብድባን ሊሆን ይችል ነበር። አብሮነታችንን ግን ማንም ሊነካ አይችልም። ይህ ሲባል ለፖለቲካ አይደለም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የከተማችን አስተዳደር እንዲወዱን አይደለም። እውነተኛውን ነገር ነው ያስቀመጥነው።

ስለዚህ ከዚህ በኋላማ ሁሉም ሰው እጅ ለእጅ ተጨባብጦ ይህ በሽታ ሲወገድልን፣ አብሮ ልማቱን ማስቀጠል ነው ያለበት። ወደ ኋላ መመለስ አያስፈልግም።
የረመዳን ፆምን በሚመለከት እንዲሁም ከወቅታዊ የወረርሽኙ ሁኔታ ጋር አያይዘው ሊያስተላልፉ የሚፈልጉት መልእክት ካለ ልቀበል?
ይህን በሽታ አላህ ያንሳልን፣ ዱአችን ነው። ሕዝበ ሙስሊሙ በጭንቀት ነው ያለው። ያው ያልነበረ ስለሆነ ይህ ከመስጊድ መራቅ፣ አብሮ መብላት መጠጣት መቅረቱ እንደ ከባድ ነው። ሙስሊሙ ሲበላና ሲጠጣምኮ ብቻውን አይደለም። የረመዳን መምጣትን የሚጠብቁ ስንት ክርስትያን እህቶችና ወንድሞች አሉ። የሆነው ነገር እንኳን አይደለም ሙስሊሙን እነርሱንም አስጨንቋል።

እናም ይህ በሽታ ተነስቶልን እንድንተቃቀፍ፣ አብረን እንድንበላና እንድንጠጣ አላህን እንለምናለን። ማኅበረሰባችን ግን ጥንቃቄውን መያዝና ማሟላት አለበት። ያም ራስን ለመጠበቅ ነው። አንድ ሰው ጥንቃቄ ሲኖረው ለሚስቱ፣ ለልጆቹ፣ ለእናት ለአባቱ ብሎም ለአገሩ ነው የተጠነቀቀው። ለራሱ ብቻ አይደለም። እናም ሁሉም ጥንቃቄ ያድርግ፣ ርቀቱን ይጠብቅ። እስከ ዛሬ የነበረውን ባህላችንን ይህ በሽታ እስኪወገድ ድረስ እንቀንሰው እንላለን።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com