የ2014 ረመዳን ወር ጾምና ድባቡኢትዮጵያ ልዩነታቸው አንድነታቸውን የማይነጥለው አንድነታቸው ልዩነታቸውን የማይጠቀልለው በርካታ የዕምነት ተከታይ ዜጎችን እቅፍ ድግፍ አድርጋ የያዘች አገር መሆኗ የአደባባይ ሀቅ ነው።
ታዲያ ይህ ወቅትም የእስልምና ዕምነት ተከታዮች የረመዳንን ጾም የቁርዓን ሥርዓት በሚፈቅደው መልኩ እየጾሙ ይገኛሉ። ከቀናት በኋላም 1443ኛው የኢድ አልፈጥርን በዓል ያከብራሉ። ታድያ የእምነቱ ተከታዮቹ ጾሙን ከመጾማቸው ባሻገር የተለያዩ መልካም ሥራዎችን እያከናወኑ ተስተውለዋል።
በእስልምና እምነት ኢፍጣር የሚባል ሥርዓት በብዛት ሲከናወን የሚስተዋል ሲሆን፤ በይበልጥ መልካም ሥራዎችን የሚያከናውኑትም በዚህ ወቅት ነው። በጎ አድራጎቱ የሚከናወነው በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በማኅበርም ጭምር ነው።
ለአብነትም ኢማን ኢስላማዊ ማኅበር በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ የ1443ኛው የረመዳን ወር ኢፍጣር በአካባቢው ለሚገኙ በችግር ላይ ላሉ አቅመ ደካማ እናቶች፤ ባላቸው ለሞቱባቸው ሴቶች እንዲሁም ለሌሎች ወገኖችን የረመዳን ፓኬጅ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን በድረ ገጹ አመላክቷል።
ማኅበሩ ከዚህም በተጨማሪ ባሳለፍነው ሚያዚያ 8/2014 በአፋር ክልል በተለያዩ ወረዳዎች በጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች በአሳይታ ከተማ የኢፍጣር ድጋፍ አድርጓል።
ከዒድ እስከ ዒድ መርሃ ግብር ምን ላይ ደረሰ?
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ‹ታላቁ የኢድ ስግደት በኢትዮጵያ› እንደሚደረግ ጥሪ ማቅረባቸውና መርሃ ግብሩ መጋቢት 16/2014 ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ይህን መነሻ በማድረግም ከዒድ እሰከ ዒድ ወደ አገር ቤት በሚል ጥሪ ከረመዳን ጾም፤ ኢድ አልፈጥር ጀምሮ እሰከ ኢድ አል አደሃ በዓል ዝግጅት መዘጋጀቱን የተለያዩ ሚዲያ ተቋማቶች ሲዘግቡ ቆይተዋል።
ታዲያ ይህ ዝግጅት ኢትዮጵያ ያላትን ጥንታዊ የእስልምና ባህል እና ቅርሶች መገኛ አገር መሆኗን በስፋት የማስተዋወቅ እድልን እንደሚፈጥርም እየተገለጸ ቆይቷል።
የጉዳዩን ተደራሽነት በተመለከተ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ዝግጅቱ መልካም እንደሆነ ገልጸው፤ ጥሪ የተደረገላቸውን አካላት ከመጡ በኋላ ሆቴል አምጥቶ ሲጋብዙ መዋል ብቻ እርባና የለውም ነው ያሉት።
እንደ አደም ገለጻ ከሆነ፤ ጥሪ የተደረገላቸው ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ቢጎበኙ፤ ቅርሶችን የክርስቲያኑንም ሆነ የሙስሊሙን ጥንታዊ ቦታዎችና ቅርሶች ቢያውቁና ቢያስተዋውቁ ይበልጥ የተሻለ ነው ሲሉ የግል አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል።
ረመዳንና የገበያው ውሎ
ማንኛውም በዓል ሲቃረብ ጀምሮ የገበያው ድባብ ላይ የዋጋ ወከባ ይስተዋልበታል። ማንኛውም አስቤዛ በተለይም በበአላት ወቅት ዋጋቸው ሲጨምር እንጅ ሲቀንስ አይታይም። ታዲያ የረመዳንን ጾም አስመልክቶም ለጾመኞች ማፍጠሪያ የሚያስፈልጉ አስፔዛዎች ከጥቃቅን ነገሮች ጀምሮ የዋጋ ንረት ማሳየታቻው ብዙዎችን አማርሯል።
በርካቶችን ያማረረው የዋጋው ጭማሪ ብቻ ሳይሆን በዓላትን ተንተርሶ የአስቤዛ ዋጋን በመጨመር በነጋዴዎች በኩል የሚስተዋለው ገንዘብን ከሰው በላይ የማፍቀር ስግብግብነት ከመንፈሳዊነት የራቀ ተግባር መሆኑም ጭምር ነው።
በመሆኑም የረዳንን በዓል የገበያ ውሎ አስመልክቶም ብዙዎች ቅሬታ እያነሱ ነው። በተለይም ተፈናቅለው ያሉ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን ነገሮችን ገዝተው በዓላትን ማክበር እንዳልተቻላቸው በተደጋጋሚ ያወሳሉ።
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል ሰይድ አደም የተባሉ በኦሮሚያ ክልል አንገር ጉትን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃይ በስደት ላይ በዓል አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቤታቸውን ከነ ሙሉ ንብረታቸው አስረክበው የተፈናቀሉ ከ45 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎች እንዳሉ የጠቆሙት ሰይድ፤ ቤቱን የለቀቀና ንብረቱን የተዘረፈ ሰው እንኳን የዋጋ ጭማሪ እያለ በተመጣጣኝ ዋጋም ቢሆን ለመግዛት መቸገሩ የማይቀር ነው ሲሉ ሐሳብ ሰጥተዋል።
ታዲያ የዋጋ ንረቱ እየጨመረ ያለው በእስልምና እምነት ተከታዮች የበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ወቅታቸውን ጠብቀው በሚከበሩ በሁሉም ሃይማኖታዊ በዓላትም ጭምር ነው።
ነጋዴዎች አስፔዛዎችን እያከማቹ አቆይተው የበዓል ወቅት ሲደርስ አውጥተው በውድ ዋጋ ይሸጣሉ የሚሉት የጥናትና ምርምር ባለሙያው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ናቸው።
አደም አክለውም፣ እውነት ይሄ ስግብበግብነት በእኛ ብቻ ሳይሆን በነብዩ መሐመድ ትዕዛዝ መሰረት አንድ ሰው የሚሸጥን ነገር ዋጋ ለመጨመር በማሰብ ደብቆ ማስቀመጥ በፈጣሪው በኩል ተጠያቂ እንደሚያደርግና ኪሳራ እንደሚያስከትልበት ይደነግጋል ሲሉ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
በዘንድሮው የረመዳን ጾም ዶሮ ከአንድ ሺሕ ብር በላይ በሚሆን ዋጋ ገዝተው አከማችተው እንደቆዩ አንስተው፤ እነዚያ ነጋዴዎች ግን በመጨረሻ ከ500 ብር በታች በመሸጥ ኪሳራ እንደገጠማቸው ነው የተመለከቱትን የተናገሩት።
በዚህም እስከ 40 እና 50 ሺሕ ብር የከሰሩ ነጋዴዎች አሉ ያሉት አደም፤ ስግብግብነት የኢትዮጵያ ባህልም ወግም አለመሆኑን ከዚህ ከሳራ ልንረዳ ይገባል ነው ያሉት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፤ ገበያ ላይ የዋጋ ጭማሪ እየተስተዋለባቸው ያሉት አስፔዛዎች ከአገር ውጭ የሚገቡ ምርቶች ብቻ ሳይሆኑ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችም ጭምር መሆናቸውን ነው።
ይህን በተመለከተም አደም ከውጭ አገር የሚገቡ ምርቶችስ መቼም የዋጋ ጭማሪ ቢደረግባቸውም የዶላር ጉዳይ እንደ ምክንያት ሊነሳ ይችላል ብለው፤ ቅቤው የተወደደበት ምክንያት ግን ምን ይሆን ሲሉ ጠይቀዋል።
አስከትለውም ከከብት እርባታ በአፍሪካ ውስጥ ኹለተኛውን ደረጃ ትይዛለች በምትባል አገር አንድ ኪሎ ቅቤ 800 ብር መሸጥ አግባብነት የሌለው ስግብግብነት ነውና ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የዘንድሮው ረመዳን ምን የተለየ ነገር አለው?
ረመዳን በየዓመቱ የሚከበር፣ በእስልምና ሃይማኖት የተቀደሰ ወቅት ተብሎ የሚጠራ በዓል ነው። ታዲያ ምንም እንኳ ሁሌም ዓመቱን ጠብቆ የሚከበር በዓል ቢሆንም የ2014 ረመዳን ጾም ግን ለየት የሚያደርገው አንዳንድ አስደሳች ዜና እንዳለ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት አደም ካሚል ተናግረዋል።
እንደ አደም ገለጻ ከሆነ፤ ለዘንድሮው የረመዳን በዓል አስደሳች ዜና የዓባይ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመር በግብጽና በኢትዮጵያዊያን የእስልምና እምነት ተከታዮች በኩል ታላቅ ዋጋ እንዳለው ነው።
የዓባይ ግድብ ተገድቦ ለኹለተኛ ሙሌት መብቃቱ ለ2014 የረመዳን ጾም መልካምና በዓሉን ሞቅ ደመቅ ለማድረግ የሚያግዝ ዜና ነው የሚሉት አደም፤ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የግብጽ ሙስሊሞች ለኢትዮጵያዊያን የእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም አመለካከት ስለሌላቸውና ዓባይ ለግብጽ ከሰማይ የወረደ ስጦታ አድርገው የማሰብ ራስ ወዳድነታቸው በመክሸፉ ነው።
አደም በተያያዘም ‹‹60 በመቶ የሚሆነው የግብጽ ሕዝብ አቋሙን የሚያንጸባርቀው ዓባይ ለግብጽ ከሰማይ የወረደ ስጦታ ነው ብሎ ነው። ህጻን ልጅ ሲወለድ እንኳ ትምህርት የሚሰጠው ስለ ዓባይ ሕይወቴን እሰዋለሁ በማለት ነው።›› ብለዋል።
ግብጻዊያን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በመንቀፍና ዓባይን የግላቸው ስጦታ በማደርግ 105 ጥናቶችን አካሂደዋል የሚሉት አደም፤ አሁን ላይ ግን ግድቡ ስለሞላና ኃይል ማመንጨት ስለጀመረ እናፍርስ ቢሉ በቀን 20 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በጎርፍ ስለሚጠፋባቸው አይሞክሩትም ነው ያሉት።
በመሆኑም የዓባይ መገደብ የእስልምና እምነት ተከታዮች ለሚያከብሩት የ2014 ረመዳን ጾም ታላቅ ዋጋ እንዳለው ነው ያብራሩት።
ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014



