መነሻ ገጽአንደበትእርዳታ ፍትህን ያመጣል

እርዳታ ፍትህን ያመጣል

የባቡል ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሀናን ማህሙዳ

በ2012 መጀመሪያ ላይ ነው፣ በ16 በጎ ፈቃደኛ ሴቶች የተቋቋመው፤ ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት። ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ጓዳኞቻቸውን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን በማስተባበር መሥራች የሆኑት ሀናን ማህሙድ ናቸው።
ባቡል ኸይር ሲመሠረት የሚያስፈልገውን ግብዓት ለማሟላት የመጀመሪያውን ርምጃ የወሰዱትም ራሳቸው ናቸው፤ ጌጣጌጦቻቸውን ሁሉ በመሸጥ። እርሳቸውን ተከትሎም አብረዋቸው ያሉ ጓደኞቻቸው እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ጌጦቻቸውን ሸጠዋል፤ ከየቤታቸው ያላቸውን አዋጥተዋል።

የመልካም በር የሚል ትርጉም ያለው ባቡል ኸይር፣ በየእለቱ ድግስ ያለበት ይመስላል። በቀን ከአራት ሺሕ በላይ ዜጎች የሚመገቡበት፣ የተቸገሩ የሚጠጉበት፣ አቅም ያላቸው ሠልጥነው ራሳቸውን የሚችሉበት ነው። በሀይማኖት ሳይለይ፣ ሰውነትን ቋንቋው አድርጎ የተቸገሩትን ሁሉ እያስጠጋ ይገኛል። ሆኖም በመንግሥት በኩል ትኩረት ያገኘ አይመስልም። እናም ተመልከቱን እያለ ድርጅቱ ጥሪ እያስተላለፈ ይገኛል። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ከድርጅቱ ምሥረታ፣ አሁን ያለበትን ሁኔታና ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት ከድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሀናን ማህሙድ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

ባቡል ኸይር ምሥረታውና መነሻው ምን ነበር? በበኩልዎ ድርጅቱን ከመመሥረትዎ በፊትስ እንዲህ ያሉ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ሠርተዋል?
ባቡል ኸይር የተመሠረተው በኹለት ልጆች ምክንያት ነው። የ12 እና የ13 ዓመት ልጆች ናቸው። በትምህርት ሰዓት የሆነ ቤት ገብተው ከብዙ ወንዶች ጋር ሲመገቡ ዐየሁ። በዚህ ሰዓት ምን ትሠራላችሁ፣ ዩኒፎርም አድርጋችኋል ብዬ ጠየቅኳቸው። እኔ ምግብ አጥተው አልመሰለኝም። በትምህርት ሰዓት ከጎረምሶች ጋር ለመዋል ሌላ ዓይነት ነገር ነው ብዬ ነው ያሰብኩት።

እና ጠብቄ ጠየቅኳቸው። ‹እኛኮ ጠዋት ባዶ አፋችንን ነው የወጣነው። እናታችን እንደምንም ብዬ ምሳ ሰዓት ላይ የሆነ ነገር ይዤ እጠብቃችኋለሁ ብላን ነው› አሉኝ። በዛ ሰዓት አላህ እድሜ ከሰጠኝ፤ ሁሉም ሰው በሰውነቱ ብቻ በእኩልነት በፍትህ የሚመገብበት የመመገቢያ ጣቢያ/ማእከል እከፍታለሁ አልኩኝ።

ከዛ በፊት እንዲህ ፈቃድ አውጥተን በአደባባይ አንሥራ እንጂ አንድ ጀምአ አለን። የሀናን ጀምአ ይባላል፤ ይታወቃል። በየሦስት ወርም ሆነ በየኹለት ወር ገንዘብ እያዋጣን በየቤቱ ምስር፣ ዘይትና የመሳሰለውን እንወስድ ነበር።

ሴቶች ሰብሰብ ሲሉ ቁምነገር አይሠሩም፣ ወሬ ያበዛሉ የሚል ብሂል አለ። እናንተ በተቃራኒው ሴቶች ሲሰበሰቡ ምን መሥራት እንደሚችሉ ዐሳይታችኋል። በዚህ ውስጥ ተመልካች ምን መረዳት ይችላል ይላሉ?
በጣም ቁምነገረኛ ነን [ሴቶች]። እኛ በወር አንድ ቀን ነው የምንሰበሰበው። በዛ መሰባሰባችን ውስጥ በጣም ብዙ ነገር ነው የምንሠራበት። የሕይወት ተሞከሮውን የሚያቀርብ አለ፤ በዚህ ወር እንዲህና እንዲያ ገጠመኝ ብለን እናወራለን። ብዙ ነገር ይነሳል። በዛም ላይ ሁሌም ብር ይዋጣል። ያም ተሰብስቦ በጣም መረዳት አለባቸው ለምንላቸው ሰዎች ነው የምናደርገው።

ብዙ ሰው እናሳክማለን፣ የግል ሆስፒታል ገብቶ የሚከፍለው አጣ ሲባል ስንሰማ፣ ለዛ እንከፍላለን። ብዙ ነገር ነው የምንሠራበት። እንደውም በአንድ ቀን ፕሮግራም ላይ ነው፣ ይህን ተቋም መክፈት አለብን ስላቸው ሁሉም ተስማምተው ያዋጡት፤ እዛው ነው የተዋጣው።
ሴቶች ሰብሰብ ሲሉ ብዙ የመሠራት አቅም አላቸው፤ እኛም ያንን በጣም ዐይተናል። እውነት ለመናገር እንዳልኩሽ ብዙ ሰው እናሳክማለን፤ በአካባቢያችን ችግር ሲኖርም እንደዛው። ክርስትያን ሙስሊምም አንልም። ከበፊትም ኹለት ጓደኞቼ አሉ፤ ማርታና ቃልኪዳን ይባላሉ። እነሱም ጀምአ ናቸው፤ አዋጥተን በጋራ ነው የምንሠራው።

የሆነ ሰው የሚከፍለው አጣ፣ ታመመ ወይም የሆነ ችግር ገጠመው ሲባል፤ የሰፈር ሰው ራሱ በተለይ ጎረቤት ላይ ያሉ ጓደኞቼ እነ ሀናን ጋር ሂዱ ነው የሚባለው። ‹እስቲ ሂዱ እነ ሀናንን ጠይቁ!› ተብለው እኛ ጋር ይመጣሉ። ሴቶችማ ብዙ ቁምነገር እንሠራለን። የባቡል ኸይር ውጤትንም ተመልከቺ።

በየጊዜው በ‹ዙም› ስብሰባ አለን፤ ዓለም ላይ ካሉ ጓደኞቻችን ጋር እንሰበሰባለን። በዛም ቁምነገር ነው የምናነሳው፣ ብዙ ነገር እንማማራለን። ባለሞያዎች እንጋብዛለን፣ ከአገር ውስጥም ከውጪም። የምንጋብዘውም ሙስሊምም፣ ክርስትያን የኦርቶዶክስም የፕሮቴስታንትም ቢሆን፤ እውቀት ያለውን ሰው እንጋብዛለን። ብዙ ሐሳብ ይንሸራሸርበታል።

የተለያየ ሀይማኖት ያላችሁ ጓደኛማቾች በጋራ ለዚህ ድርጅት ዓላማ መሳካት እየሠራችሁ እንደሆነ አንስተዋል። ይህ የሀይማኖት ልዩነት አግዟችኋል ወይስ ፈትኗችኋል?
ኧረ በፍጹም ፈተና አልሆነብንም። በነገራችን ላይ ሀይማኖትን በጣም ማጥበቅ አልወድም። ለምሳሌ ልንገርሽ፤ አንድ ኦርቶዶክስ ጓደኛዬ አለችና ነፍሰ ጡር መሆኗን አላውቅም ነበር። ሌላ ጊዜ እኔ ጋር ረቡዕ ወይ አርብ ስትመጣ ሽሮ ወይ የሆነ ነገር ሠርተሸ ጠብቂኝ ነው የምትለኝ። እና አንድ ቀን ኬክ ሥሪልኝ አለችኝ። በጣም ደነገጥኩኝ። በጣም ጾመኛ ናት።

አሁን ምን መጥቶ ነው ኬክ በረቡዕ ቀን የምትበላው ብዬ፤ ባትበይ ጥንቅር ትያለሽ እንጂ በረቡዕ ቀን ኬክ አልሠራልሽም። ካልጾምሽ ምን ልትሆኚ ነው አልኳት። ነፍሰ ጡር መሆኗን አላወቅኩም ነበር። እርሷም ‹ቆይ! ጓደኛዬ ጳጳስ ናት!? ብላ ሳቀች።
እኔ የትኛውም ጓደኛ ይኑረኝ፣ ፕሮቴስታንትም ኦርቶዶክስም የሆኑ ምርጥ ጓደኞች አሉኝ። የሚገርምሽ ነገር ግን በሀይማኖታቸው በጣም ጠንካራ ናቸው። እንደውም ዝም ብሎ ሀይማኖት የሌለው ሰው ነው እኔ የምፈራው። ሀይማኖቴ ብሎ ሀይማኖቱን የሚያከብር ሰው የሰዎችን ድንበር አያልፍም ብዬ ነው የማምነው።

ስታውቂ በጣም ትከባበሪያለሽ። አሁን በተለያየ ፕሮግራም እርስ በእርስ ስንጠራራ፣ እኔ ካለሁ እስክወጣ ድረስ ሙዚቃ አይከፍቱም። እኔም ጋር ሲመጡ ቁርዓን አልከፍትም። አንቺ ሀይማኖትሽ ለራስሽ ነው፣ ሌሎች ላይ የምትጭኚው ነገር አይደለም።

እኔ ሰፈር ውስጥም አብዛኛው ሙስሊም ያልሆነ ነው። ግን የሰፈር ውስጥ ኮሚቴ መሪ ነኝ። ትልልቅ አባቶች ናቸው ያሉት፣ ግን እኔን መርጠውኛል። እና ለእኔ ምንም ነው። አሁን እንኳን ለረመዳን በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡት ክርስትያኖቹ ናቸው። ወሩን ሙሉ የሚመጣውን ሕዝብ ሲያስተናግዱ ነበር። ‹እናንተ ጾመኛ ናችሁ፣ ይደክማችኋል› ብለው ያዝኑልናል።

ድርጅቱን ስትመሠርቱ ጌጣጌጦቻችሁን ሁሉ ሸጣችኋል?
አዎን! እንዳልኩሽ የጓደኛ ስብስብ ነበርን። መጀመሪያ ከራሴ ነበር መጀመር የነበረብኝ። እኔ ሙስሊም ነኝ። በእስልምና ደግሞ ሰደቃ የሚጀመረው ከአንቺ ከራስሽ ነው። እና እኔም ያገባሁበትን ወርቅ አምጥቼ ሰጥቻለሁ አልኩኝ፤ ትልልቅ ወርቅ ነው አልጠቀምበትም ነበር። ስለዚህ ሁሉም ወርቅ ያለው ወርቅ አዋጣ። ብር ያለውም ደግሞ ብር አመጣለሁ አለ። እዛው ላይ አሰባሰብን።

ቁሳቁስ እቃ ያለው ያንን ይሰጣል። እናቱ የሞተችበት የእናቱን እቃዎች፣ ድስት የመሳሰለውን ይሰጣል። እናቶቻችን ደግሞ ትልልቅ ድስት ነበራቸው። እንደዛ ነው የተዋጣው።

- ይከተሉን -Social Media

አሁን ላይ በአገራችንም በየከተማው እለት እለት ችግሮች እየጨመሩ ነው። ችግሩ ሲበዛ ስትመለከቱ ፍርሀትና ስጋት ተሰምቷችሁ አያውቅም?
ትሰጊያለሽ፤ ያለ ነገር ነው። እኛ ደግሞ ምገባ ላይ የምንሠራ ስለሆነ ወጪያችን ብዙ ነው። እኛ ሥራ ጀምረን በአጭር ጊዜ ኮቪድ ተከሰተ። ኮቪድ ደግሞ ብዙ ሰው ተቸግሮ ቤት የተቀመጠበት ሰዓት ነው። ባለሀብቶችም ቤት ቁጭ ብለዋል። እኛ ደግሞ የከፈትንበት ሰዓት በጣም ብዙ ቻሌንጅ ነበር። ጦርነትም ነበር እንደሚታወቀው።

ግን እንደዛም ሆኖ እንደምንም ተፍጨርጭረን እዚህ ደርሰናል። እንደውም አማራ ክልል ወደ ደሴ፣ ባህር ዳር የመሳሰለው ጋር ድጋፍ እያሰባሰብን ስንልክ ነበር።

እንዲህ ከባድ ፈተና ሲኖርና ሲያጋጥም ጽናት የሚሆናችሁ፣ የሚያበረታችሁ ምንድን ነው?
አንደኛ ነገር የሰዎቹ ደስታ ነው። እናቶች ሁል ጊዜ ሲወጡ ዐይተሸ ከሆነ ሙስሊሙ ዱዐ አድርጎ ነው የሚወጣው፣ ኦርቶዶክሱም ጸሎት አድርሶ ነው የሚወጣው፤ ያቆይልን ብለው። በጣም ያሳዝናሉ። በእርግጠኝነት በወጣትነት ጊዜያቸው ብዙ ነገር ያሳለፉ እናቶች ናቸው። ለአገራቸውም ብዙ ጠቅመው ሊሆን ይችላል።

የአንዳንድ ሰዎችን ታሪክ ስትሰሚ አንቺ ራስሽ ነገ እንደዛ የማልሆንበት ምንም ምክንያት የለም ትያለሽ። እንደውም ልጆቻቸው ቤታቸውን ሸጠውባቸው ጎዳና የወጡ በጣም ብዙ ሰዎች አሉ። ሕይወት እንደምናስበው አይደለም። እኛም ባቡል ኸይርን ስንከፍት በዚህ ደረጃ ይገጥመናል አላልንም። እንደው ሰው መብላት አለበት ብለን እንጂ በዚህ ደረጃ ሰው ይቸገራል ብለን አይደለም። ግን ቤት ይቁጠረው፣ በጣም ያሳዝናል። እንደውም ምን እናድርግላችሁ ብለሽ ነው የምትጣጣሪው።

እርዳታ ፍትህን ያመጣል። በሰዎች መካከል ፍቅርን ይፈጥራል። ሰዎች በብዙ ጥላቻ ውስጥ ሲያልፉ አንቺ የሆነች ነገር እዚህ ጋር ስታደርጊ በመካከላቸው የሚጨምረው ደስታና ፍቅር አለ። ያም ምንም ዓይነት ዋጋ እንድትከፍይ ነው የሚያደርግሽ።
ለውጣቸውን ስታይ እንደዛው ነው። አንቺ ጋር ሲመጡ እንዴት ሆነው ነው የገቡት፣ ከዛ አገግመው ተቀይረው ስታይ ምንም ዓይነት መስዋዕትነት ልክፈል ትያለሽ።

አሁን ያሉ ቁጥሮችን እናንሳ። ምን ያህል ሰዎችን በቀን እየመገባችሁ ነው? ወጪያችሁስ ምን ያህል ነው?
በአሁን ሰዓት ለረመዳን ኹለት ሺሕ ሰው ነው ያስፈጠርነው። ምክንያቱም በድርቅ ምክንያት ከክፍለ አገር ወደዚህ የመጡ አሉ፣ ተፈናቅለው መጥተውም ያልተመለሱ ሰዎች አሉ። የተለያዩ፣ መንገድ ላይ ልጆች ይዘው በየድልድዩ ስር የተቀመጡም ብዙ እናቶች አሉ። ባቡል ኸይር ደግሞ 80 በመቶ ተረጂዎች እናቶች ናቸው። እነሱን ሁሉ ሰብስበን ነው ያስፈጠርነው።

ዋናው ግን 1500 ነው በአባወራ፤ ከነልጆቻቸው 4100 ናቸው በቀን እኛ ጋር የሚመገቡት። እኛ ለአንድ አባወራ በልጆቹ ልክ ነው ምግብ የምንሰጠው። ምግባችን ደግሞ በጣም ጥራቱን የጠበቀ ነው፣ ሆቴል ራሱ ሄደሽ የምታገኚው ዓይነት አይደለም።

ወጪያችንን በሚመለከት፤ አሁን በኪራይ ቤት ነን። ሌላም ስቶር አለን። ለዚህኛው ቤት መጀመሪያ ስንከራይ ቤተሰብ ነበረና፤ አስቀድሞ አከራይቶበት ከነበረው 70 ሺሕ፤ ለእኛ ያከራየን በ35 ሺሕ ነው፤ ሰደቃ ብሎ። አሁን 50 ሺሕ አደረገብን። ለስቶር ደግሞ 35 ሺሕ እንከፍላለን። በወር እስከ 85 ሺሕ እናወጣለን። ቤቱ ግን ከዛም በላይ ያወጣ ነበር። የምንሠራውን ሥራ ዐይቶ ስለምንግባባውም፣ እናንተ እየለፋችሁ የእኔ አስተዋጽኦ ምንድን ነው ብሎ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

አሁን ውጡ ተብለን ነበር፣ በረመዳን መጀመሪያ። ከዛ ሲያይ የሚሆን ነገር አይደለም፣ መንግሥትም ያደረገልን ነገር የለም። ስለዚህ ‹ያው መቀጠል አለባችሁ፤ እነዚህን ሁሉ እናቶች ምን አደርጋለሁ› ብሎ አስቀጠለን።

እና አሁን ያለው ነገር ከባድ ነው፤ መንግሥት ቢተባበረን ጥሩ ይሆናል። ዝም ብለው መሬት ወይም የጠየቅነውን ይስጡን ሳይሆን ሁሉንም ያውቁታልና መጥተው ምን እየሠራን እንደሆነ ይመልከቱ። ሳይነግሩንም መጥተው ቢጎበኙን፣ ምን እንደሚያስፈልገን ራሳቸው ያውቃሉ። እንደ አገርም የሚያኮራ/የሚኮራበት ድርጅት ነው።

እንዲህ ያሉ ድጋፎች ሲደረጉ ጥገኛነት ይፈጠርና የተረጂነት ስሜት ይጠነክራል የሚል እምነት አለ። ይህ እንዳይፈጠር ምን እየሠራችሁ ነው?
ይህን ነገር እኛም በጣም እናስባለን። እስከ አሁን ባቡል ኸይር ራሱን ችሎ ወደ 101 ሰዎችን አሠልጥኖ አውጥቷል። የልብስ ስፌት ሥልጠና እንሰጣለን፣ ከዚህ ቀደምም አስመርቀናል። አሁን ደግሞ ከኢድ በኋላ ይመረቃሉ። በጣም ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ነው ያመጣነው። ለምሳሌ እናቶች ቤት ውስጥ ሆነው ማሰሻ እንዲሠሩና እንዲሸጡ አድርገናል። አንድ ማሰሻ 50 ብር ነው የምንሸጠው። ኢትዮጵያ ብዙ ሰው እንጀራ ተመጋቢ ስለሆነ ፍላጎት አለ።

እና በቀን 4 ማሰሻ ብትሸጡ 200 ብር ነው። ያ በወር ስድስት ሺሕ ይመጣል እንላቸዋለን። ቺፕስ ራሱ በደንብ ንጹህ አድርገው እንዲሠሩ፣ እንዴት ምርጥ አድርገው ማቅረብ እንዳለባቸው እናሠለጥናቸዋለን። እኛ ጋር የሠለጠኑት እንደውም ሰው በሰልፍ ነው የሚገዛቸው። ወንዶቹንም የጫማ ሥራ እናስተምራቸዋለን።

የወደፊት የባቡል ኸይር እቅድ ምንድን ነው? ምንስ የምታስተላልፉት መልዕክት አለ?
ከኢድ በኋላ ትልቅ ማሠልጠኛ ተቋም አቃቂ ቃሊቲ ላይ እናስመርቃለን። ከስደት ተመላሾችን ነው እንቀበላለን ያልነው። ኢንሻአላህ! ብዙ እቅዶች አሉን። ወጣቶች የተለያየ ሥልጠና ወስደው ሥራ ላይ እንዴት በቀላሉ እንደሚሠማሩ ለማስቻል ነው። ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ወጥተውም ሥራ የሌላቸው አሉ። ግን እኛ አዳዲስ ነገሮችን ከውጪም ያየነውን ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ለማሠልጠን ወስነናል። አላህ ካለ ከኢድ በኋላ ይሆናል።

እኛ የምንለው እርዳታ ፍትህን ያመጣል፣ ፍቅርን ይጨምራል፤ እንደ አገርም ራህመት ይወርዳል ነው። በሰደቃኮ እንደ አገር የሚመጣ ችግር ይጋረዳል። በእኛ እምነት ውሃ እሳትን እንደሚያጠፋ ሁሉ ሰደቃ አበሳን ይጋርዳል። ስለዚህ እንደ አገር ራሱ የሚመጣብንን ፈተና በሰደቃ መጋረድ ይቻላል፤ ለምስኪኖች ከተረባረብን።

የማስተላልፈው መልዕክት ደግሞ፤ መሬት የለንም። ተከራይተን ያለንበት ቦታ በጣም ጠባብ ነው። በዛች ጠባብ ቦታ ታፍነን ነው ያለነው። በቦታ ጥበት ምክንያት ብዙ ያልሠራናቸው ግን በቀላል መሥራት የምንችላቸው ነገሮች አሉ። እና መንግሥት ትኩረት ቢያደርግ።
በጣም ሰው በዝቶብናል፣ ወጪው በጣም ከፍተኛ ነው። እኛ ደግሞ ሴቶች ብቻ ስለሆንን እናዝናለን። በጣም ነው ዋጋ እየከፈልን ያለነው። መንግሥት ግን ለባቡል ኸይር በዛ ደረጃ ትኩረት አልሰጠውም። መሬት ያስፈልገናል። እንዲሀ ጥሩ ነገር ይዞልሽ የመጣን ድርጅት ደግሞ አንቺ ማበረታታት ነው ያለብሽ።

መንግሥት አሁን ያለውን ነገር ለብቻው የሚወጣው አይደለም። መንግሥት ላይም ጣት መቀሰር አይሆንም። ማኅበረሰቡ በመሥራትና አዲስ ነገር በመፍጠር ራሱን መለወጥ እንጂ መንግሥት ብቻውን አይሆንም። ምንም ማድረግ አይችልም። መንግሥት እንደ እኔ ዕይታ እንዲህ የሚሠሩ ሰዎችን እንዲያበረታታ ሰዎችም ደግሞ ራሳቸውን ለማውጣት ቢሞክሩ፣ እንጂ ይህ በመንግሥት ብቻ የሚፈታ አይደለም።

- ይከተሉን -Social Media

እና እኛ በጣም ቦታ መሮናል፤ ዝናብ ሲመጣ በጣም ያሳዝናል። ለአንድ ምግብ ብለው ዝናብና ፀሐይ ይመታቸዋል። በጣም ብዙ ነገር እየተፈራረቀባቸው ነው። በቅርብ ሰው ተገጭቶብናል። ረጅም ሰልፍ ነበርና አንዲት እናት ተሰልፈው ታች ሲጠብቁ መኪና ገጭቷቸዋል። ደግሞ ግፍም ነው። የምንሠራው ለኅብረተሰቡ ነው። ቢያንስ ቦታ የተሻለ ያስፈልጋል። እውነት ለመናገር ለወደፊትም ለማኅበረሰቡ የሚጠቅም ብዙ እቅድ አለን።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች