የኢትዮጵያ አርበኞች የድል ቀን ሲታወስ

0
2376

ከዛሬ 86 ዓመት በፊት 1928 ጣሊያን ኢትዮጵያን በመውረር፣ በዚያው ዓመት ሚያዚያ 27 ማርሻል ባዶሊዮ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በማስወረድ የጣሊያን ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀል ማድረጉን ታሪክ ያወሳል።
ጣሊያን በ1888 በተካሄደው የአድዋ ጦርነት ጊዜ የደረሰባትን አሰቃቂ ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ከፍተኛ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታ፣ ለኹለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን በ1928 መውረሯ የሚታወቅ ነው።

ሞሶሎኒ በብዙ ረገድ በአፍሪካ ቁልፍ ቦታ ያላትን ኢትዮጵያን በመውረር የጣሊያን ቅኝ ግዛት አንድ አካል ለማድረግ ብሎም የአገሩን ሥም ለማደስ ጥንቃቄ የተሞላ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርግ መኖሩም በታሪክ ይጠቀሳል።

ለዚህም ይረዳው ዘንድ ከ300 ሺሕ ያላነሱ ወታደሮች፣ ከ330 እስከ 500 የሚደርሱ ተዋጊ አውሮፕላኖች እንዲሁም 500 ገደማ ታንኮችን በ1928 መጀመሪያ ጣሊያን ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንድትከፍት በሚል በምጽዋ በኩል ለማርሻል ዴ ቦኖ መላኩ ተመዝግቦ ይገኛል።

በታሪክ ጸሐፍት ዘንድ ሰፍሮ እንደሚገኘው፣ ጣሊያናውያን ከአፍሪካ ነጻነቷን አስጠብቃ በመኖር የምትታወቀውን ታላቋን አገር ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን በጀግኖች የኢትዮጵያ አርበኞች ምክንያት ጠቅላላ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የታሪክ መምህር ሳሙኤል ነጋሽ፣ በየዓመቱ ሚያዚያ 27 የሚከበረው የድል በዓል፣ ለጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በጣሊያን ተደፍሮ ስለነበር፣ ያንን ለማስመለስ የተደረገውን ትግልና በመጨረሻ የተገኘውን ድል ለማስታውስ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጣሊያኖች የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ከገቡ በኋላ በቆዩባቸው አምስት ዓመታትም በርካታ ቦታዎችንና ከተሞችን መቆጣጠር በመቻላቸው፣ የጣሊያን ገበሬዎችና ሠራተኞች ወደ ኢትዮጵያ በማስመጣት ምርጥ ምርጥ መሬቶችን እንዳከፋፈሏቸው ነው የሚገለጸው።
ኢትዮጵያውያን በእውቀትና በጥበብ እንዳይጎለምሱም ትምህርት ቤቶችን ከመዝጋት ጀምሮ ታዋቂ የኃይማኖት አባቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና አርበኞችን ይገድሉ ነበር። ይህም ኢትዮጵያውያን የነጻነት ትግላቸውን አጠናክረው ለመቀጠል እንዳስገደዳቸው ይነሳል።

በተለይ ደግሞ የካቲት 12/1928 አዲስ አበባ ውስጥ ማርሻል ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገ ሙከራ፣ ጣሊያኖች በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ማካሄዳቸው የአርበኞችን ትግል እንደብረት ያጠነከረና መላው የኢትዮጵያን ሕዝብም ለነጻነቱ አምርሮ እንዲታገል ማድረጉ በብዙዎች የሚነገር ነው።

ጣልያኖች ወረራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ በአዲስ አበባ፣ በመላ አገሪቱ እንዲሁም በጦር ሠራዊቱ ውስጥ በርካታ ሰላዮችን በመሰግሰግ ኢትዮጵያን ድል ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም፣ ሕዝብ ያስገበሩበት፣ እንዲሁም ተረጋግተው ሰላማዊ አስተዳደራዊ ሥራዎችን የከወኑበት አንድም ዓመት እንደሌለ አያሌ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ።

በወቅቱ አርበኞች ላይ ጥቃት እንዲደርስ ከሚያደርጉና የፋሽስቶች ቆይታ እንዲራዘም አብረው ከሚሠሩ ባንዳዎች በቀር፣ ጀግኖች በዱር በገደሉ በቆራጥ ጀግንነት ለነጻነታቸው ተፋልመዋል። ሴቶች አርበኞችም ስንቅ ከማዘጋጀትና ከማቀበል በዘለለ በጦርነት በመሳተፍ፣ ሕጻናትም እድሜና የአካል ጥንካሬ ሳይገድባቸው ለነጻነታቸው የከፈሉት ዋጋ የሚካድ አይደለም።

መላው አፍሪካ በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ በነበረበት በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ ከዓለም ሉዓላዊ አገሮች አንዷ በመሆኗ የዓለም መንግሥታት ማኅበር አባል መሆኗ ይታወሳል። ይህን መሠረት በማድረግም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችውን ወረራ እንዲሁም በሕዝቡ ላይ እየፈጸመች ያለውን ዘግናኝ ግፍ ለዓለም መንግሥታት በማሳወቅ መፍትሄ አመጣለሁ በሚል ወደ ጄኔቭ አቅንተው ነገሩን ቢያስረዱም ሰሚ ሊያገኙ አልቻሉም።

ስለሆነም፣ ንጉሠ ነገሥቱ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ሰሚ የለም በማለት እጃቸውን አጣጥፈው እንዳልተቀመጡ ነው የሚነገርላቸው። ምንም እንኳን ከጣሊያን ዘመናዊ መሣሪያ እና የተደራጀ ጦር አንጻር ሲታይ የእርሳቸው ሠራዊት እጅግ ኋላ ቀር የነበረ መሆኑን ጠንቅቀው ቢረዱም፣ በስደት አገር ሆነውም አርበኞች እምቢ አልገዛም በማለት ጣልያንን እንዲወጉ ሥራቸውን ይሠሩ ነበር የሚሉ አሉ።

የታሪክ መምህሩ ሳሙኤልም ንጉሠ ነገሥቱ ከአገር በውጣታቸው ልዩነት ቢኖርም፣ በአገራቸው የድል ቀን እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አንስተዋል። እንደ ቀድሞ የኢትዮጵያ ነገሥታት የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ነበረባቸው በማለት ከአገር መውጣታቸውን የሚቃወሙ ወገኖች ቢኖሩም፣ ‹አይ! መሄዳቸው ጥቅም አለው።› የሚሉም በርካቶች ናቸው ብለዋል።

በዚህም ‹‹በመንግሥታቱ ፊት ቀርበው ያደረጉት ንግግር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሥረት ምክንያት ነው።›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ሦስተኛው ለሚባሉ የዓለም አገራት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሐሳብ አቅርበዋል።›› ነው የሚሉት።

ቀድሞ ሲቀልዱባቸው የነበሩ አውሮፓውያንም በኋላ የኹለተኛው የዓለም ጦርነት ሰለባ ሲሆኑ እርሳቸውንና ኢትዮጵያን እንዲያስታውሱ አድርገዋቸዋል ባይ ናቸው። ‹‹ይህም እኛ ኢትዮጵያውያን ወድቀንም ቢሆን አሸናፊነታችን የማይቀር ነው የሚል ትምህርት ይሰጣል።›› ሲሉ አስገንዝበዋል።

ብዙዎች የካቲት 12/1928 ግራዚያኒን ለመግደል የተሸረበውን ሴራ ማን ጠነሰሰው በማለት ይጠይቃሉ። ሆኖም ይህን ሐሳብ ያመጡትና በጠቅላላው ያቀነባበሩት ንጉሠ ነገሥቱ መሆናቸውን አስረግጠው የሚናገሩ አሉ።

በግራዚያኒ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ ቢሳካም ባይሳካም በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ እልቂት ሊያስከትል እንደሚችል ቀድመው አስልተውት የነበረ ቢሆንም፣ ምንም ነገር ከነጻነት የሚበልጥ አይደለም በሚል ተፈጻሚ እንዲሆን አድርገዋል ነው የሚባለው።
በመቀጠል፣ በዓለም ላይ ሊቀሰቀስ በነበረው ኹለተኛው የዓለም ጦርነት የኢትዮጵያ አርበኞች የድል ቀን እንዲፋጠን አበርክቶ እንዳለው ይነሳል።

የወቅቱ ኃያላን እንግሊዝና ፈረንሳይ፣ ኢትዮጵያ መሣሪያ እንዳትገዛ ሲከለክሉ የቆዩ ቢሆንም፣ ጣልያን ከጀርመን ጋር ትብብር በማድረጓ፣ እንግሊዝ የኢትዮጵያ አርበኞች የሚያደርጉትን ተጋድሎ በመደገፍ ጣልያንን ለመውጋት እቅድ እንድትይዝ አደረጋት። በዚህም ወታደራዊ ድጋፍ በማድረግ ኃይለ ሥላሴ ወደ አገራቸው እንዲገቡ መቻላቸውን መዛግብት ይነግሩናል።

በእንግሊዛዊው ጀኔራል ካኒንግሂም የሚመራ ጦርም ከኬንያ ተነስቶ ወደ መሀል አገር ሲገሰግስ፣ በጄኔራል ፕላት የሚመራ ጦር ደግሞ ከሱዳን ተነስቶ በአስመራ በኩል ወደ መሃል አገር እንዲንቀሳቀስ መድረጉን የታሪክ ሰነዶች ያመላክታሉ።
በንጉሠ ነገሥቱ የሚመራ የኢትዮጵያ አርበኞች እና እንግሊዛውያን አማካሪዎች ያሉበት ጦር ደግሞ ከሱዳን በጎጃም አድርጎ ወደ መሀል አገር ለመግባት መገስገሱ ተመዝግቧል።
ከዚያ በኋላም ትግሉ ተፋፍሞ በመቀጠሉ፣ ኹለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጣልያኖች አዲስ አበባን ለቀው እንደወጡ ነው የሚታወቀው።

ከኬንያ ተነስቶ ወደ መሀል አገር የሚገሰግሰው ጦርም በአርበኞች እገዛ ጭምር፣ አዲስ አበባ መጋቢት 28/1933 ቀድሞ መግባቱ ይነገርለታል።

ይህን ተከትሎም የአርበኞች የድል መታሰቢያ ቀን መጋቢት 28 ነው ብለው የሚናገሩ ቢኖሩም፣ ከዚህን ዕለት ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 27 ቀን ድረስ ንጉሠ ነገሥቱ ጎጃም ስለነበሩ እና ዙፋናቸው ላይ አለመቀመጣቸውን በማንሳት የተሟላ የድል በዓል ነው ሊባል እንደማይችል የሚያነሱ አሉ።

ንጉሠ ነገሥቱ ለአንድ ወር ጎጃም የቆዩበት ምክንያት እንግሊዞች አርበኞች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ባለመፈለጋቸው ነው የሚሉ ማሳያዎች ይገኛሉ።

የታሪክ መምህሩ የድል በዓሉ መከበር ያለበት መቼ ነው የሚሉ ጭቅጭቆች እንደነበሩ አንስተው፣ የመጀመሪያው እንግሊዞች ጣሊያንን አስወጥተው አዲስ አበባ በገቡበት ይሁን የሚል ነው። ሌላው ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ በገቡበት ነው መከበር ያለበት የሚል አለ። ዋናው ግን ድሉ ነው ብለዋል።

እንግሊዞች አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ያደረጉትን ወደ ጎን በመተውም፣ እነሱም ተሳትፎ ባያደርጉ ኖሮ ድሉ ይፋጠን ነበር ወይ ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ሆኖም በአዲስ አበባ የነበሩ አርበኞች ይህን በመቃወማቸው እንግሊዞች በዚህ ሐሳባቸው እንዳልገፉበትና ሚያዝያ 27/1933 ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በከፍተኛ አጀብ እኩለ ቀን ገደማ ከታላቁ የዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት አደባባይ ላይ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መልሰው እንደሰቀሉት በታሪክ የሚነገር ነው።

በዕለቱም ‹‹ይህ የምትሰሙት ድምጽ የእኔ የንጉሣችሁ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነው።›› በማለት በጀመሩት ንግግር፣ ጣልያን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ጦርነት መክፈቷን ለዓለም መንግሥታት አቤቱታ ማቅረባቸውን፣ የኢትዮጵያ አርበኞች የባህሪያቸው በሆነው ጀግንነታቸው እንዴት ጠላትን እንደተፋለሙ በመጥቀስ ዕለቱ በአምስት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲደርስበት ከቆዬው አሰቃቂ ግፍ የተላቀቀበት ታላቅ የደስታ ቀን መሆኑን አብስረዋል።

በጥቅሉም ኢትዮጵያውያን ከንጉሠ ነገሥታቸው ጀምሮ እስከ ሕጻናት ድረስ ለነጻነታቸው ያደረጉት ተጋድሎ፣ ጣሊያን ከአምስት ዓመት ያልዘለለ ያልተረጋጋ ቆይታ እንዲኖራትና ኢትዮጵያም ነጻነቷን ዳግም አስጠብቃ እንድትዘልቅ እንዳስቻላት ይጠቀሳል።

የድል በዓሉ ፋይዳ
የድል በዓሉ ኢትዮጵያ በዓለም ያላትን ተሰሚነት ያጠነከረ እንዲሁም ለነፃነቱ የማይደራደር አሸናፊ ሕዝብ ባለቤት መሆኗን ያስመሰከረ ነው። ከዛም አልፎ የሚመጣው ትውልድም የአሸናፊነት መንፈስን ተላብሶ በኩራት እንዲኖር የሚያድርግ ትልቅ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የተለያዩ የታሪክ ጸሐፊዎችና ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

ሆኖም ብዙ የድል በዓሎች የሚገባቸውን ትኩረትና ክብር እያገኙ አይደለም ሲሉ የሚገልጹት የታሪክ መምህሩ ሳሙኤል ነጋሽ ናቸው።

እንደርሳቸው ገለጻ፣ ከታሪክ ጋር ካለ ጸብ እንዲሁም በታሪክ የተገኙ ክስተቶችን አንኳሶ ከማየት በተለይ ባለፉት ሦስት ዐስርት ዓመታት የድል በዓላት ከነሙሉ ክብርና ሞገሳቸው ሲከበሩ እንደማይታይ ጠቁመዋል።
ቀኑ ሲድርስ እንደነገሩ ለማክበር ከሚደረግ ነገር ውጭ፣ ተገቢውን ክብርና ቦታ ለመስጠት ፍላጎትና ተነሳሽነት ባለመኖሩ በየጊዜው የሚሰጣቸው ትኩረት እየቀነሰ መሆኑን ነው ያነሱት።

ይህ ሁኔታ በአሁኑ ወቅትም እንዳልተሻሻለ ጠቅሰው፣ ‹‹ያስከፈለን ዋጋ አልታየም፣ ከታሪክ ለመማር ቁርጠኝነት ካለመኖሩም በላይ የታሪክን ጠቀሜታ ማስተማሪያ መንገዶችም እንደተገፉ ናቸው።›› በማለት አክለዋል።
አካሄዳችን ዋጋ እያስከፈለንና እየጎዳን ነው ያሉት መምህሩ፣ በዚሁ ከቀጠልን ምን ሊገጥመን እንደሚችል አሁን ላይ የምናያቸው አንዳንድ ነገሮች ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።

ከታሪክ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች በተለይ ከዐስር ዓመታት በፊት በዓለም ላይ ባሉ አገራትም ችግር እንደነበር ገልጸዋል። ሆኖም ከዐስር ዓመታት ወዲህ ግን በርካታ የአፍሪካ አገሮችም ሳይቀር ለታሪካቸው ዋጋ በመስጠት መነቃቃት እያደረጉ መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህም ታሪክ ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባና ይህም ለአንድነት፣ እድገትና ልማት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ያስገነዘቡት።

‹‹ጊዜው ካለፈው ትውልድ ለተረከብናቸው ድሎች ተገቢ ክብር በመስጠትና በመማር የሚመጣውን ትውልድ ከፍ ባለ የአገር ፍቅር ስሜትና አንድነት የምንቀርጽበት ሊሆን ይገባል።›› ሲሉም አሳስበዋል።
ለዚሁ የድል ቀን መታሰቢያ ሐውልት በአዲስ አበባ አራት ኪሎ የሚገኝ ሲሆን፣ የዘንድሮው የአርበኞች ቀን ለ81ኛ ጊዜ ይከበራል።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here